እአአ 2014 እስከ 2015 በነበረው ክሪሚያን የመቀራመት ጉዞ ከመምጣቱ በፊት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የነበራቸው ተቀባይነት ወደ 86 በመቶ ነበር። ነገር ግን ክሪሚያን ከወሰዱ በኋላ የፑቲን ተቀባይነት እየቀነሰ መጥቷል። የፑቲን ተቀባይነት ከነበረበት ወደ 66 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን እንዲህ አይነት ሁኔታም እአአ 2012 እስከ 2013 ድረስ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ያስታውሳል።
ይህ ሁኔታ የመጣው ሩስያ ገጥሟት በነበረው የኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት የህዝቡ ገቢ እየቀነሰ በመምጣቱ ነው። ይህ ጉዳይ የፑቲንን ተቀባይነት እንዲቀንስ ያደረገ ሲሆን እአአ 2018 ላይ ጡረታ የመውጫ እድሜ እንዲጨምር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ሁኔታው እየተባባሰ የመጣው ዋነኛ የፖለቲካ ኢንስትቲዩሽን በሆኑት ተቀባይነት እያጡ በመምጣታቸው ሲሆን ሁለት ሶስተኛው ዜጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሜትሪ ሜድቬዴቭን አንቀበልም ማለቱ ተሰምቷል። በተጨማም ሩስያውያን የአካባቢ አስተዳደሮችና የአገሪቱን ፓርላማ ላይ ያላቸው እምነት እየቀነሰ መጥቷል።
በሩስያ ውስጥ አስተዳደሩ ከህዝቡ ጋር ያለው መቀራረብ እየቀነሰ መጥቷል። አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የተባበሩት ሩስያ ፓርቲ መሪ ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ ተቀባይነታቸው ቀንሷል። በቀጣይ በፈረንጆቹ መስከረም ወር በሚደረገው የከተማ ምክር ቤት ምርጫ እጩዎች በግዳጅ በግላቸው እንዲወዳደሩ ትዕዛዝ ተላልፏል። አሁን በስልጣን ላይ የሚገኙ አመራሮች ተቀባይነት መቀነስ በአገሪቱ የሚገኙት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋፊ ለማግኘት በሚያደርጉት የቅስቀሳ ስራ ይረዳቸዋል ማለት አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በሩስያ ከፍተኛ የሆነ ቅስቀሳ ለማድረግና ነፃ የሆነ ምርጫ ለማከናወን ህጋዊና ቢሮክራሲያዊ የሆኑ አሰራሮች እንቅፋት ይፈጥራሉ። የተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች ለከተማ ምክር ቤት ለመወዳደርና ለማሸነፍ በተለያዩ ህጎችና በተቀመጡ መስፈርቶች ምክንያት ቀድመው እንዲወድቁ ይደረጋል።
በቀጣይ በሚኖረው ምርጫም ይህ ሁኔታ እንቅፋት እንደሚፈጥር ይጠበቃል። የተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች በግል እንዲወዳደሩ የተነገራቸው ሲሆን በፓርቲ ደረጃ መወዳደር እንደማይችሉ ቀደም ተብሎ በተቀመጠው ህግ ተከልክለዋል። የአገሪቱ ዋነኛ ተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ የሆነው አሌክሲ ናቫኒሊ ዘጠኝ ጊዜ ፓርቲ ለመመስረት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎበታል። በሩስያ ምርጫ ህግ የግል ተወዳዳሪዎች ለምርጫው ለመቅረብ የግድ ከሚወዳደሩበት አካባቢ ሶስት በመቶ ድምፅ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
እንደ ሊኦኒድ ቮልኮቭ ናቫሊኒ ገለጻ፤ በሩስያ ምርጫ ህግ ላይ የተቀመጠው የመወዳደሪያ መስፈርት በምንም አይነት የሚሳካ አይደለም። ከህዝቡ የሚገኘውን ድምፅ ለክረምት እረፍት ከአገሪቱ የሚወጡት፣ ለተመራጮች በራቸውን የሚዘጉ ዜጎች፣ አጠራጣሪ ለሆኑ ዶክመንቶች የሚፈርሙትን፣ ለመምረጥ ለሚደረገው ምዝገባ የሚያስፈልጉ ዶክመንት የሌላቸውና ጭራሽ መምረጥ የማይፈልጉ ዜጎች ቁጥር ሲቀነስ ከሶስት በመቶ በታች እንደሚሆን አብራርቷል።
በተግባር ይህን ቁጥር ማግኘት መቻል ተአምራዊነት ነው። ምክንያቱም ለተወዳዳሪ ሰዎች የድጋፍ ፊርማ የሚያሰባስቡ ሰዎችን መደብደብ፣ የግል ፋይሎች ኮፒ ሲደረጉ እንዲሳሳቱ ማድረግ እና የምርጫ ኮሚሽን አመራሮች ተወዳዳሪ ሰዎችን በማባረር አለቆቻቸው እንዲወዳደሩ የማድረግ ሁኔታዎች አሉ። በዚህ የከተማ ምክር ቤት ለመወዳደር የመራጭ ፊርማ ማግኘት ከባድ ነው። እንደ ሊያ ዮሺ አይነት ታዋቂ ተፎካካሪ ተወዳዳሪ አይነቶች ካልሆኑ በቀር የተቀሩት ተወዳዳሪዎች እንኳን ለማሸነፍ ለመወዳደር የመቅረብ እድላቸው አነስተኛ ነው። ነገር ግን ህጋዊና ቴክኒካል እንቅፋቶች ለተፎካካሪዎች የሚጋፈጡት በጣም የገዘፈ ችግራቸው አይደለም። እንደውም የሩስያ ህዝብ ለፖለቲካ ያለው ትኩረት ማነስና በቀጣይ የሚመጡት ለውጦች ያሰጓቸዋል።
እአአ 1980 ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ በሩስያ ህዝቡን ወደ ፖለቲካው ውስጥ ለማስገባት እና የኑሮ ደረጃውን እንደ ምዕራባውያን ለማድረግ በተሰራው ስራ አሁን አብዛኛው ህዝብ ቀደም ብሎ ከነበረበት የተሻለ ኑሮ ላይ ይገኛል። ሩስያ ከቀድሞ ሶቪየት ህብረት አገራት የተሻለ ኢኮኖሚ ላይ የምትገኝ አገር ናት። ለዚህ ደግሞ ምዕራባውያን ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር የሰሜን ቃል ኪዳን አገራት(ኔቶ) እና አውሮፓ ህብረት ድርሻ ከፍተኛ ነበር።
የፑቲን አስተዳደር በአሁኑ ወጣቶች አዕምሮ እየተረሱ የሚገኙ መሪ እየሆኑ ነው። የኢኮኖሚ እድገት ማህበራዊውንና መልካምድራዊውን የሚቆጣጠር በመሆኑ አብዛኛውን ህዝብ ይነካል። በአሁን ወቅት የኢኮኖሚ እድሎች የተመቻቹ በመሆናቸው ሩስያውያን በአገራቸው ወይም ሌሎች አገራት ሄደው የመኖር መብት አላቸው። በሶቪየት ህብረት ወቅት ግን ይህ ሁኔታ አይፈቀድም ነበር። የቀድሞ ሶቪየት ህብረት ነዋሪዎች ከአገራቸው ወጥተው መንቀሳቀስ ህልም ይሆንባቸው ነበር። በአሁን ወቅት ያለው የኢኮኖሚ ችግር ፖለቲካዊ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። ነገር ግን ሩስያ ከጎረቤቶቿ ጋር ስትወዳደር በተወሰነ መልኩ አምባገነናዊ ስርዓት ትከተላለች በዚህም ህዝብ ላይ ጫና የመፍጠር ሁኔታዎች ይስተዋላሉ።
በሌላ አነጋገር በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ምክንያት እየመጡ ያሉ ሰብዓዊ ጥሰቶች ከቀጠሉ እንደ እአአ 1980 የፖለቲካ ችግር ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን አሁን ላይ ለሩስያ መንግስት ትልቅ ጠላት ሆና ያለችው ዩክሬን ብቻ ናት። ዩክሬንን በምሳሌነት በሩስያ ፓርላማ ውስጥ በማንሳት ለአምስት ዓመታት ያክል ፕሮፓጋንዳ ሲሰራ ነበር። ፕሬዚዳንት ፑቲን የአገር ውስጥ ችግሩን ወደ ውጭ በማላከክ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት ችለዋል።
በሌላ በኩልም ፑቲን ለዜጎቻቸው ማንኛውንም ተቃውሞ ቢያደርጉ ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችል አሳይተዋል። በተጨማሪም የማድያን ህዝባዊ ተቃውሞ በዩክሬን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን በዚህ ብዙ ሩስያውያን ተጎድተዋል። በዚህ ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ማህበራዊ ትስስሮች እንዲላሉ አድርጓል። በሩስያ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም የመንግስት ተቃዋሚ ሰዎች በተቻላቸው አቅም ህጉን ጠብቀው ለመንቀሳቀስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ነገር ግን ጥረቱ ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት እያስከፈላቸው ቢሆንም ተቃዋሚ መሪዎች እጅ መስጠት አልፈለጉም። ቀደም ብሎ ይህ ጥረታቸው ትንሽ አሸናፊነት አስገኝቶላቸው ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት ተቃዋሚዎች 17 አውራጃዎች ላይ አሸንፈው ነበር። በአብዛኛው ዋና ከተማዋ በታጠቁ ሀይሎች የተከበበ ነበር።
በቀጣይ በሚኖረው ምርጫ ቢያንስ አምስት የተቃዋሚ እጩዎች ለውድድር ይቀርባሉ። ተወዳዳሪዎቹ የሚፈለገውን የድጋፍ ፊርማ ያገኙ ሲሆን የምርጫ ኮሚሽኑ እንዲወዳደሩ ፈቃድ እስኪሰጣቸው ይጠብቃሉ። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ እአአ 2017 ተደርጎ በነበረው የአካባቢ ምርጫ ላይ ያገኙትን ድል መድገም የሚችሉ ከሆነ የሩስያ ፓርላማ ጥቅሙንና ጉዳቱን በመለየት በአሁኑ እንዲወዳደሩ ሊፈቅድ ይችላል። ነገር ግን ቀጣይ በፈረንጆቹ መስከረም 9 የሚደረገው ምርጫ የሚወስነው ይሆናል። በሩስያ ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ በጣም አዝጋሚ እየሆነ መምጣቱ መረዳት ይቻላል።
እ.አ.አ. በ2000 ዓ.ም. የሩስያ ፕሬዚደንት ሆነው ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ቪላድሚር ፑቲን በሀገሪቱ እንዲሁም በዓለም ፖለቲካ ዑደት ላይ የጎላ አሻራ ማሳረፍ ችለዋል። ፑቲን እንደ ምልክት ከሚታዩት ዲሚትሪ ሜድቬድቭ ስልጣን በድጋሚ ከወሰዱ በኋላ የሀገሪቱን መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ቁጥጥር ውስጥ አዋሉ። የተቃዋሚ ወገኖች ሀይልም እየተዳከመ መምጣት ጀመረ። ብሔርተኝነት በሩስያ በሀይለኛው መሰበክ ያዘ። የምዕራቡን ዓለም የሚያጥላሉ መልዕክቶችም መደመጥ ጀመሩ።
በተለይ ደግሞ እ.አ.አ. በ2014 በሩስያ የሚደገፈው የዩክሬን መንግስት በአውሮፓ መንግስታት በሚደገፈው ተቃዋሚ ሀይል ከተናጠ በኋላ ፑቲን ያሳዩት መረር ያለ ምላሽ ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር። ሩስያ ክሬሚያን ከዩክሬን ከወሰደች በኋላ የፑቲን ተቀባይነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየወረደ መምጣት ጀመረ። በምስራቃዊው የሩስያ ክፍልም አመፅ መቀስቀስ ጀመረ። የፑቲን ወዳጅ የሆኑት የሶሪያው በሽር አል-ኣሳድን በመደገፍ እንዲሁም በሶሪያ የሚገኘው የሜዲቴራኒያን ባህር ሀይላቸውን ለመከላከል በሚል አየር ሀይላቸው የሶሪያ ሽምቅ ተዋጊዎችን እንዲያጋይ ላኩ።
ፑቲን ራሳቸውን ሩስያን ከ1990ዎቹ ምጣኔ ሀብታዊ፥ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውስ በማውጣት ለዚህ ያበቃሁ ነኝ በማለት ያሞካሻሉ። በማከልም የሩስያን ፍላጎት በማስጠበቅ ከምዕራባዊያን ጫና ያላቀቅኩ ጠንካራ መሪ ነኝ ሲሉም ይደመጣሉ። በዚህ በኩል ደግሞ ተቺዎቻቸው ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ከፊውዳሊዝም ያልተናነሰ ስርዓት በመገንባት ገበያውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዳይመጣ መንገዱን ዘግተዋል በማለት ይወቅሷቸዋል። ምንጭ፡- አልጀዚራና ቢቢሲ
አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011
መርድ ክፍሉ