ስለመንግስት ባለስልጣናት ስናነሳ በመጀመሪያ ከእዝነ ልቦናችን የሚገባው የክብራቸው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ አንድን የከተማ ማህበረሰብ ለመምራት ስልጣን ስለተሰጠው አንድ ከንቲባ ስናነሳ የሚጓዝበት ተሽከርካሪ ዘመናዊነት፣ ስለስልጣናቸውና ክብራቸው፣ ስለተሻለ ኑሮአቸውና በተለያዩ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሀብቶች ተከበው የሚያደርጉት ንግግር ወይም አጀባቸው ይታሰበናል ይሆናል፡፡ ሰሞኑን ከወደሜክሲኮ ስለአንድ ከንቲባ የተሰማው ዜና ግን ከዚህ ነባራዊ እውነታ ያፈነገጠ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ካርሎስ ቴና በሜክሲኮ ቺሁዋቹዋ ግዛት የምትገኘው ቹሃትሞች ከተማ ከንቲባ ናቸው፡፡ ከንቲባው በሚመሯት ከተማ ታዲያ አልፈታ ያለ አንድ ችግር አለባቸው፡፡ ችግሩም በከተማዋ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ቅሬታ ነው፡፡ እነዚህ ቅሬታ ያላቸው አካል ጉዳተኞች በከተማዋ በአብዛኛው በጎዳና ላይ የሚኖሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ አካል ጉዳተኞች ከመንግስት የተለያዩ ድጎማዎችን እንዲያገኙ አስተዳደሩ በህግ ቢያስቀምጥም እነሱ ግን ህጉና መሬት ላይ ያለው ነገር አንድ አይደለም፤ መንግስትም ቃሉን እየጠበቀ አይደለም የሚል ቅሬታ ዘወትር ያሰማሉ፡፡
ከንቲባ ቴና ይህንን ጉዳይ እንዲጣራ ከቅርብ የስራ አጋሮቻቸው ጀምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላትን ወደነዚህ ዜጎች ቢልክም የዜጎቹ ቅሬታና የባለስልጣኖቻቸው ምላሽ ተቃራኒ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ማንን ልመን በሚል ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ነገር ግን ጭንቀታቸውን በሆዳቸው ይዘው አንድ ነገር ለመስራት ያስባሉ፡፡ አስበውም ወደተግባር ገቡ፡፡ በዚህ መሰረት ችግሩን በተግባር ለመፈተሽ አሰቡ፡፡
በዚህ መሰረት ከንቲባ ቴና ማንንም ሳያማክሩና ማንም ሳያያቸው ሱፎቻቸውን ቀይረውና ቡትቶ ልብስ ለብሰው ከትልቁ ፅህፈት ቤታቸው ወደ ጐዳና ወጡ፡፡ ከንቲባው ጐዳና የወጡት ደግሞ በዊልቸር ላይ ተቀምጠውና የኤሊ ቆዳ የመሰለ አንገተ ሙሉ ሹራብ ለብሰው፣ ከፊል የፊታቸውን ገጽታ ቀይረው እና ጥቁር ኮፍያ ለብሰው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከፊል ጆሮአቸውን በባንዴጅ ሸፍነውና ሙሉ ለሙሉ አካል ጉዳተኛ መስለው በዚያም ላይ ማንም እንዳይጠረጥራቸው ጥቁር መነፅር አድርገው ነው፡፡ ከዚያም ተሽከርካሪ ወንበራቸውንም እየገፉ ወደ ከተማዋ የማህበራዊ ልማት ዳይሬክቶሬት አቀኑ፡፡ እዚያም መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሊደረግላቸው የሚገቡ ማህበራዊ ድጋፎችን ጠየቁ፡፡
በአገሪቱ ህግ መሰረት አካል ጉዳተኞች ነፃ የምግብ አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት ወደ ዳይሬክቶሬቱ ሄደው ምግብ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ነገር ግን እንኳንስ በህጉ የተቀመጠውን ምግብ ሊያገኙ ቀርቶ በአግባቡም ያስተናገዳቸው አልነበረም፡፡ ከዚያም አልፎ አገልግሎት ሰጪዎቹ አንቋሸሿቸው፡፡
በመቀጠል እራሳቸው ወደሚመሩት ከንቲባ ፅህፈት ቤት አመሩ፡፡ በዚያም ከንቲባውን ለማነጋገር እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ነገር ግን ከንቲባው እንደሌሉ ተነገራቸው፡፡ እሳቸውም ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ፀሐፊ ጋር ለማውራት እንደሚፈልጉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እዚህ የገጠማቸው ግን ያልጠበቁት ነበር፡፡ የሚፈልጉት ሰው ባለመኖሩ ለሚቀጥለው አንድ ሰዓት ተኩል በአዳራሹ ውስጥ እንዲቆዩ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ከንቲባው አንድ ነገር አረጋገጡ፡፡ አካል ጉዳተኞቹ ያቀረቡት ቅሬታ እውነት ነው፡፡
ከዚህ በላይ ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ሳይስፈልጋቸው እዚያው ሰራተኞቹ ባሉበት ከዊልቸራቸው ላይ ተነስተው ለሁሉም የቢሮው ሰራተኛ ራሳቸውን አሳውቀው ወደፅህፈት ቤታቸው ገቡ፡፡ ሁሉም ሰራተኛ በድንጋጤ ተዋጠ፡፡
ከንቲባው ይህንን ያደረጉት ከሰራተኞቻቸውና ከአካል ጉዳተኞቹ ትክክለኛው የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ነበር፡፡ ከድርጊቱ በኋላ ከንቲባው ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች እንደተናገሩት ማንን ማመን እንዳለብኝ ቸግሮኝ ነበር፡፡ አካል ጉዳተኞችን ወይስ አብረውኝ የሚሰሩትን ሰራተኞች? ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወደዚህ ውሳኔ የገባሁትም እውነትን ፍለጋ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ኤልቬሴሮ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ እንደዘገበው ቴና ለዓመታት የሚታወቁት የተቸገሩትን በመርዳትና ከደካሞች ጎን በመቆም ጭምር ነው፡፡ በተለይ በማህበራዊ አገልግሎት ፍትህ የተጓደለባቸውን ዜጎች ለመርዳት ስልጣናቸው በፈቀደው አቅም ሁሉ ይሰሩ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
ቴና እንደተናገሩት በሙከራቸው ወቅት ከአንዳንድ የቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ጭምር ከፍተኛ እንግልትና ማግለል ደርሶባቸዋል፡፡ ይህም ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል፡፡ በርግጥ ሁሉም ተመሳሳይ ፊት አላሳዩአቸውም፡፡ ጥቂት ለእውነት የቆሙ የስራ ባልደረቦቻቸውም ነበሩ፡፡
በመጨረሻም ከንቲባው ጠበቅ ያለ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ “ከዚህ በኋላ በአስተዳደራቸው ስር አላግባብ የሚጉላላ ወይም ከህግ ውጭ የሚንገላታ ባለጉዳይ ማየትም ሆነ መስማት አልፈልግም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በሚገኝ ማንኛውም ሰራተኛ ላይ ጠንካራ እርምጃ እወስዳለሁ” ብለዋል ከንቲባ ቴና፡፡
የከንቲባ ቴና ተግባር እጅጉን የተወደሰና ልዩ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ መልካም ስራ መሆኑን ብዙዎች ድጋፋቸውን አቅርበዋል፡፡ በተለይ ህዝብን የሚያጉላሉ በርካታ ባለስልጣናትና አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች ባሉበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ እንዲህ አይነት ተግባራት ትክክለኛ ስራ የሚሰሩና የማይሰሩትን ለመለየት ጠቃሚ በመሆኑ የሚበረታታ ነው፡፡ በተለይ የውሸት ሪፖርት ትልቅ ፈተና በሆነበት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የከተማችን ከንቲባ ወርደው ቢመለከቱ ስንቱን ኃላፊና የመንግስት ሰራተኛ ይታዘቡት ይሆን?
አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011
ወርቁ ማሩ