የሰው ልጅ ብቻ ተግባር ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ፖለቲካ ነው፡፡ ፖለቲካ ሰውን ከእንስሳ የሚለይ ልዩ የሰው ልጅ መገለጫ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሰው ከፖለቲካ ውጪ ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የእለት ተዕለት ህይወታችን በፖለቲካ መጠመድ አለበት ማለት እንዳልሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የሰው ልጅ የሚያልፍባቸው በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚዊና የመዝናኛ ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አሁን ይህ ያልተፃፈ ህግ ተጥሶ ህይወታችን ሁሉ ፖለቲካና ፖለቲካ ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
የመጀመሪያው የፖለቲካ መዋያ ስፍራ ማህበራዊ ሚዲያው ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያው የሚወጡ ጉዳዮችን ስንመለከት በፖለቲካ የተጠመዱ ናቸው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁሉም ነገር ፖለቲካ መሆን መቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ የአገራችን እግር ኳስ ከጨዋታው ይልቅ ፖለቲካዊ ሚዛኑ አይሎ ከጨዋታ በኋላ ከፌስቡክም ሆነ ከደጋፊዎች የምንሰማው ፖለቲካዊ ጨዋታውን ነው፡፡ ይህንን እንድል ካደረጉኝ ምክንያች ውስጥ አንዱ ባለፈው ሳምንት የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነው፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ለዋንጫ ሲጠበቁ የነበሩት ሶስት ክለቦች ነበሩ፡፡ ፋሲል ከነማ፣ መቐለ 70 እንደርታና ሲዳማ ቡና፡፡ የአጋጣሚ ነገር ሆኖ እነዚህ ክለቦች ከሶስት ክልሎች የተገኙ ናቸው፤ ከትግራይ፣ ከአማራና ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፡፡ እነዚህ ክለቦች እየተጫወቱ ታዲያ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይ በፌስቡክ ሲተላለፉ የነበሩ ልዩ ልዩ መልዕክቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ መልዕክቶች ደግሞ በአብዛኛው ስለጨዋታው አልነበረም፤ ስለአገራችን ወቅታዊ ሁኔታና በእግር ኳሱ ውስጥ ስለሚንጸባረቁ ፖለቲካዊ እንድምታዎች እንጂ፡፡ በርግጥ ይህ እግር ኳሳችን በፖለቲካዊ ንፋስ ለመወሰዱ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በሌላም በኩል በተለያዩ የመዝናኛና የማህበራዊ ህይወት መከወኛ ስፍራዎችም ቢሆን ፖለቲካ ትልቁን ስፍራ መያዝ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በተለይ ወንዶች ሰብሰብ ሲሉ ዋነኛ አጀንዳዎቻቸው ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ጡረታ የወጡ አዛውንቶችም በአብዛኛው ሲገናኙ ዋነኛ የጨዋታ አጀንዳቸው ፖለቲካ ሆኗል፡፡ በመጠጥ ቤት፣ በየመንገዱና ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ስፍራዎች ሁሉ ፖለቲካ የየእለት መነጋገሪያና መዋያ አጀንዳ ነው፡፡ የሚገርመው የሚወራው ፖለቲካ ደግሞ በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ ሳይሆን በፌስ ቡክ ወሬ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው፡፡
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ዋነኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተው በአገራችን በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጄኔራሎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነበር፡፡ እንደሚታወቀው እነዚህ ጥቃቶች የአብዛኛውን የአገራችንን ህዝብ አንገት ያስደፉና ያሳዘኑ ክስተቶች ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን እነዚህን ክስተቶች መነሻ በማድረግ በየመንደሩ የተፈጠሩ “ተንታኞች” የመሰላቸውን ሃሳብ እየፈበረኩ ሲተነትኑ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶቹ “ተንታኞች” ድርጊቱ ሲፈፀም እዚያው በቦታው ላይ ያሉ ይመስላሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በዚህ ዙሪያ የተዛቡ መረጃዎችም ሲተላለፉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ሰዎቹ የሞቱት ቀደም ብሎ ነው፤ መንግስት ከግድያው ጀርባ እጁ አለበት፤ ወዘተ የሚሉ ያልተጨበጡ ወሬዎች የፌስቡክ አጀንዳ ከመሆን አልፈው ህብረተሰቡ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡
“እከሌ እኮ በወቅቱ እንዲህ ሲያደርግ ነበር፤ እከሌ አሰላለፉ ከዚህ ጋር ነው” ወዘተ የሚሉ ደመነፍሳዊ ቅንብሮችም ህዝቡ ውስጥ ሲሰራጩ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ለነዚህ አካላት ዋነኛ ምንጫቸው ደግሞ ፌስ ቡክ ነው፡፡ አብዛኞቹ እንዲህ አይነት ትንታኔ የሚያቀርቡ ሰዎች መረጃውን ከየት አገኛችሁት ቢባሉ ከማህበራዊ ሚዲያ የዘለለ መልስ የላቸውም፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ምንጭ የተሳሳተ ሊሆን እንደሚችል አንዳችም ጥርጣሬ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ ለነሱ በፌስ ቡክ የተነገረ ወሬ ሁሉ እውነት ነው፤ ወይም ፌስቡክ ለወሬያቸው ትክክለኛ ምንጭ መሆን ይችላል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ አዲስ አጀንዳ ተገኝቷል፤ የሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄ፡፡ ይህ ጥያቄ ለዓመታት የቆየና አንዴ ሲነሳ ሌላ ጊዜ ሲከስም የቆየ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም ለውጡን ተከትሎ ጥያቄው ጎልቶ በመውጣት አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምዷል፡፡ ከዚህ ውጭ በፌስቡክ የሚራገቡት አጀንዳዎች ግን አሁንም የፌስ ቡክ የፈጠራ ወሬዎች ናቸው፡፡ በተለይ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ክልል መሆናችንን እናውጃለን በሚለው ኃይልና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን የሃሳብ ልዩነት መነሻ በማድረግ በየቦታው ወሬውን የሚራግቡ አካላት በዝተዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ዋነኛ የወሬ ምንጫቸው ደግሞ ፌስቡክ ነው፡፡
አሁን አሁን ፌስቡክን የሚያዘወትሩት ደግሞ በአብዛኛው ስለመረጃም ሆነ ስለቴክኖሎጂ ምንም አይነት እውቀትና ግንዛቤ የሌላቸው ናቸው፡፡ አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ የቤት ሰራተኛቸው ከሱ በተሻለ ሁኔታ የፌስቡክ የዘወትር ተጠቃሚ ናት፡፡ አብዛኛውን ጊዜዋንም የምታሳልፈው ፌስቡክ በማንበብና በመላላክ ነው፡፡ ከትምህርት ገበታ ከራቁ ዘመናት ያስቆጠሩና ስማቸውን አስተካክለው ለመፃፍ የሚቸገሩ አንዳንድ የፊደል ፀበኞችም ፌስቡክን ሲያመልኩና የፌስቡክ ቋሚ ተሰላፊ ሲሆኑ ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡
እንደው ግን በአሁኑ ወቅት ሁሉም ለሙያው ክብር ቢሰጥ መልካም አይደለም ትላላችሁ? በተለይ ሁሉም እየተነሳ የፖለቲካ ተንታኝ የሚሆንበትን መንገድ ብንቀንስ ጥፋቶችንም እንቀንሳለን ባይ ነኝ፡፡ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያን ምንጭ እያደረግን የምናወራው የፖለቲካ ወሬ አገራችንን እንዳያበጣብጥ ብንጠነቀቅ መልካም ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎች በአብዛኛው የውሸት ፋብሪካ ውጤቶች መሆናቸው መገንዘብና ከማየት በዘለለ ባንጠቀምባቸው መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምንጩን ሳናውቅ በፌስቡክ ያገኘነውን መረጃ እየያዝን በዚህ አካባቢ እንዲህ ሆነ፣ እከሌ እንዲህ አደረገ፣ እዚህ አካባቢ እንዲህ አይነት ችግሮች ይፈጠራሉ፣ ወዘተ የሚሉ መረጃዎችንም እየለቃቀምን ህዝባችንን ባናደናግር መልካም በመሆኑ ሁላችንም ብናስብበት መልካም ነውና እናስብበት፡ ፡ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም በነዚህ የማህበራዊ ሚዲያዎች የምናገኛቸው መረጃዎች ሁሉ ትክክል ላይሆኑ ይችላሉና ቆም ብለን እናስብበት እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሀምሌ 8/2011
ወርቁ ማሩ