ወዲያም ወዲህም የፖለቲካው ወግ ደርቷል። «ትልልቅ ሰው ሲያወራ ጣልቃ አይገባም…ሂዱ ወደ ጓዳ» እንደሚባሉ ትንንሽ ልጆች፤ ሌላው ርዕሰ ጉዳይ የተባረረ ይመስላል። ይሄ ፖለቲካ ደግሞ እዩኝ እዩኝ ማለት ይወዳል ልበል! በእርግጥ ሁሉም ነገር ይመለከተኛል፣ እኔ የሌለሁበት ነገር የለም፣ አድራጊ ፈጣሪ እኔ ነኝ ወዘተ ማለት ይቀናዋል። ፖለቲካ የሌለበትን ጉዳይ ብናነሳስ ምን ይለናል!
አዎን! ስለዣንጥላ እናነሳ። ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በቀር ዣንጥላ ማለት ከዝብናም፣ ከፀሐይ የሚያስጥል መጠለያ፣ መከለያ ማለት ነው። ዣንጥላ ከሌለ ምን እንሆናለን? ከዝናብ የሚያስጥለን ከፀሐይ የሚገላግለን መጠለያ አይኖረንም። ሮጠን ክፍት ካገኘነው የገበያ ማዕከል ካልገባን ዛሬ «ቤት የእግዚአብሔር ነው» የሚልም ብዙ አይገኝም። ሌባው በየት በኩል እንድንተማመን ያደርግና!
ብቻ የዣንጥላ ዋጋ ቀላል አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዣንጥላ ጠላሁ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? ወንዶችስ እሺ፤ ቀድሞውንም ዣንጥላ የመያዝ ልምዳቸው እዚህ ግባ የሚባል ስላይደለ ሊገባቸው ይችላል። እህቶቼ ግን ስሙኝ! እውነት እላችኋለሁ ዣንጥላ መያዝ ጠላሁ።
ለምን? በነፍስ ወከፍ ዣንጥላ እየያዝን በየት በኩል እንሂድ? በተለይ ግርግር የሚበዛባቸው መንገዶች ላይ ዝናብ እየጣለ ዣንጥላ ይዞ መሄድን የመሰለ አስጨናቂ ነገር የለም። አጠር ያለ ሰው ከፊቱ ረዥም ሰው ሲመጣ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል፣ ከጎን የሚያልፈው በዣንጥላው ወጨፎ እንዳያበሰብስ መጠንቀቅ አለ፣ ከፍ ዝቅ እያደረጉ ወደግራና ወደ ቀኝ አብረው ዘመም እያሉ አንዳንዴም ከግዴለሹ መጋጨት ያጋጥማል። አንዳንዴማ ዝናቡን ወይም ፀሐዩን ሳይሆን ሰውን የምንከላከል የሚመስልበት ጊዜ አለ።
ምን አለፋችሁ! ሁሉም ሰው በራሱ «ሚኒ» ዣንጥላ ውስጥ ሆኖ ራሱን ብቻ ከመጣበት ዝናብ ሊከላከል ይሞክራል። እሱም በተሳካ አትሉም! የድሮው ዣንጥላ!? እሱማ በምን እድላችን። ሰፊው ጥቁሩ፣ ከዛ ደግሞ የተለያየ ቀለም ያለውና ሁለት የቤት እመቤቶች ከነመላ ቤተሰባቸው ሊያስጠልል የሚችል የሚመስለው ባለግርማ ሞገሱ ዣንጥላ፤ ውል ውል አይላችሁም? ለዚህ ነበር ማስታወቂያ መሥራት!
እንደውም ቀደም ያሉ አዋቂ ሰዎች እነዚህን ዣንጥላዎች እንደ ምርኩዝ ሁላ ይጠቀሙት የለ? መጠለያም፣ ማስጠለያና መደገፊያም ነበር ድሮ፤ ዣንጥላ። «ኑ ተጠለሉ!» ቢሉ የማያሳፍር ነው። በዛ ላይ ሲያዋድድስ… «ነይ ወዲህ ዝናብ አይምታሽ» ብለው እናቶች ፍቅራቸውን ይገልጡበታል። ኧረ «ከዝናብ ልጠለል?» በሚል ሰበብ በአንድ ጎጆ መኖር የጀመሩም ጥቂት አይመስሉኝም።
አሁንስ? እመኑኝ በቦርሳዬ ያለችው ትንሿ ዣንጥላዬ እንኳን ሌላ ሰው ልትጨምርና እኔንም ብቻ ከዝናብም የምታስጥል አይደለችም። እንደውም ኮፍያ በሏት፣ ዝናብ የዘነበ ከሆነ ብዘረጋት ከጸጉሬና ትከሻዬ አልፋ ብዙም አታድነኝም። ግን በቦርሳዬ ለመያዝ ትመቻለች፣ ትልቅ ዣንጥላ ይዞ «አካብዴ…» ከመባል ትታደገኛለች። እንደውም አንዳንዴ ከኔ የባሱትን ትንሽዬ ዣንጥላዎች ሳይ «እንዲህ ቅልል ያለች ትንሽዬ ዣንጥላ ከየት ገዝተውት ይሆን?» ብዬ ገበያውን እጠይቃለሁ።
አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ ያው የፈረደበት ታክሲ ጥበቃ ሰልፍ ላይ ነኝ። ሲያጉረመርም የቆየው ሰማይ ብሶት ያለበት ይመስል ዝናቡን በአንዴ አረገፈው። ከሰልፉ መውጣት ስልጣንን የማስነጠቅ ያህል ከባድ መሆኑን እዚህ ጋር ያዙልኝና ልቀጥል። «ስንት ሰዓት በጽናት ታግዬ ቆሜ የጠበቅኩትን ተራዬንማ ለማንም አሳልፌ አልሰጥም» የሚል መፈክር በተሰላፊ ልቦች ውስጥ ሳይኖር አይቀርም።
ታድያ ያለው አማራጭ በያለንበት ዣንጥላ ማውጣት ነው። በእርግጥ እንጠለል ተብሎ ቢሮጥም ሱቆች እንኳ የራሳቸውን ግንባር ከመከለል አልፎ ሌላ ሰው የሚያስጠልል መጠለያ ኖሯቸው አይደለም። ብቻ ሁሉም ዣንጥላ ሲያወጣ ጥቃቅን ነው። ሰፋ አለ የተባለው ዣንጥላ ከዣንጥላው ባለቤት በተጨማሪ ግማሽ ሰው ብቻ የሚያካትት ሆኖ ተገኘ። ያውም ቁመታቸው የተመጣጠነ የሰልፍ አጋሮች ጋር ነው።
ይሄን ሳይ ነው የአያቴ ዣንጥላ ትዝ ያለኝ። አያቴ በሱ ዣንጥላ ራሱንም እኛን የልጅ ልጆቹንም ከዝናብ አስከልሏል፣ ከፀሐይ ታድጓል፣ ደክሞት እንኳ ደገፍ ብሎ አሳልፎበታል። ዣንጥላው ሲዘረጋ ደግሞ እንደ ጉልላት ከአናቱ ላይ በሚታየው ብረት ሳይቀር ሊነክሰው ከነበረ ውሻ ድኖበታል። እርሱ እግሩ ተሳስሮ ቤት የተቀመጠ ጊዜና እኛ የልጅ ልጆቹ አዋቂ ስንሆን ግን ዣንጥላው ተጣለ፤ አቧራ ጠጥቶ። እቃ ቤት ከዕቃ ማስቀመጫው ሳጥን ላይ በጥግ በኩል ተጋድሟል፤ እጀታው ብቻ አጮልቆ ዛሬን ለማየት የሚጓጓ ይመስል፤ ሳልፍ ሳገድም ይታየኛል።
እድሜ ለቻይና! እድሜ ለስስታምነት! እድሜ ለስንፍና! እድሜ ለ «ኑሮን ቀለል ማድረግ» ይሁንና¡ ኑሮን አቀለልን ብለውን አኗኗራችንንና እኛን አቀለሉን። ሌላው ቀርቶ ቤት የመጣ እንግዳ ዝናብ ይዞት መውጣት ቢቸገር እንኳ ወፍራም ሻርፕ ሰጥተን እንሸኛለን እንጂ ያንን ዣንጥላ ለማውጣት አስበን አናውቅም። እኔም አንዱ «ሚኒ» ዣንጥላዬ ሲሰበርና ሌላ ስገዛ፣ ደግሞ መልሶ ሲሰበር፤ በመካከል እንኳ ዣንጥላ ባጣ የአያቴን ይዞ መውጣት ውል እንኳ አይለኝም፤ ሰው ምን ይለኛል?
ትንንሽ ዣንጥላ በበዛበት ጊዜ ትልቁን ይዞ መውጣት ያሳፍራል? ቆይ ዣንጥላ ዋናው ማስጠለሉ እንጂ ውበት ነው እንዴ? ከሆነስ ሰፋ ያለውና የሚያቀራርበው ዣንጥላ አይሻልም? እንደውም ብዙ ላጤ የበዛው አንድም በዚህ ምክንያት ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው? ጥናት እስኪደረግበት ድረስ በዚህ መስማማት እንችላለን መቼስ!
ሁሉም በየአቅሙ፣ አውቃለሁ በሚለውና ለጆሮው ሽው ባለለት ልክ ፖለቲካን አውቅሃለሁ ይለዋል። ፖለቲካም «ከኔ ውጪ ሌላ ስለምንም አትነጋገሩ» ያለ ይመስላል፤ ዞሮ ዞሮ ከቤት እንዲሉ፤ ጉዳዩ ሁሉ ዞሮ ዞሮ ፖለቲካ ሆኗል። ነገሮችም መጠሪያቸውን «ፖለቲካ» ሳያደርጉ ይቀራሉ ብላችሁ ነው። ይሄ ግን ፖለቲካ አይደለም፤ ስለ ዣንጥላ ነው ያነሳነው።
እኔነት ስለበዛበት ዣንጥላ፣ ብቻዬን ስለበረከተበት የዣንጥላ ያዥ ጎዳና ነው ያነሳነው። ውበት ቀደም ብሎ ክብር ዝቅ ስላለበት አያያዛችን ነው ያወጋነው። ደግሞም አየን፤ የድሮ ዣንጥላ ሰፊ ነበር። አሁን ግን ጠቧል፤ አንሷል፤ ከአንድ ሰው በላይ አይዝም። አዲስ መንገደኛም ሲመጣ የራሱን ጠባብ ዣንጥላ ይይዛል፤ በመንገዱ ይገፋፋል፣ በሰልፉ አንዱ አንዱን ያበሰብሳል፣ ያረጥባል።
ይህ አሁን ፋሽን ነው፤ ዣንጥላውን አጥብቦ ራስን ብቻ ማስጠለል። እኔ ብቻ ብሎ ራስን ማዳን። «ለሌላው ዣንጥላ የምሸከመው ምን ስለሆንኩኝ ነው» በሚል ግለኝነትን ማሰማመር። ይህ አሁን ፋሽን ተብሏል። ዣንጥላ አምራቿ «በርቱ ለእያንዳንዳችሁ ገና የምሠራው ዣንጥላ አለ፤ ተቃቅፋችሁ አትሂዱ፣ ተቀራርባችሁ አትነጋገሩ፣ አብራችሁ አትጠለሉ» ብላለች መሰለኝ።
ያው ዛሬም በቦርሳዬ ትንሿ ዣንጥላ አለች። እናንተ ጋር ያለው ዣንጥላ ምን ዓይነት እንደሆነ አላውቅም። ግን «ኑ ተጠለሉ» የሚል እንጂ «ኧረ ለዚህ ሁሉ ሰው አይበቃም» የሚል ዓይነት «ቅልል» ያለ እንዳይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ወገን! ክረምቱ ረጅም አይደለም፤ ሁለትና ሦስት ወር ናት። ለዚህች አጭር ጊዜ ዣንጥላችንን ሰፋ አድርገን አብረን ተጠልለን ከመጨናነቅ ብንድን አይሻልም። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011
ሊድያ ተስፋዬ