ሎስ አንጀለስ ከተማ “የስደተኞች መጠለያ” እሆናለሁ ስትል አወጀች

በአሜሪካ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የሆነችው ሎስ አንጀለስ “የስደተኞች መጠለያ ነኝ” ስትል አስታወቀች። ከተማዋ ከተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስደተኞች ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ልትገባ ትችላለች እየተባለ ነው። የከተማዋ ምክር ቤት “መጠለያ ከተማ” የተሰኘ ረቂቅ አፅድቋል። ይህ ረቂቅ የፌዴራል መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት በከተማዋ ሀብት እንዳይጠቀሙ ያግዳል።

የሎስ አንጀለስ ትምህርት ቤቶች ለሰነድ አልባ ስደተኞች እና ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ተማሪዎች “መጠለያ” ይሆናሉ ስትልም ከተማዋ አውጃለች። ከሁለት ወር በኋላ በዓለ ሲመታቸው የሚፈጸመው ትራምፕ በርካታ ስደተኞችን ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ ቃል ገብተዋል።

የትራምፕ ቀኝ እጅ የሆኑት ቲም ሆማን የፌዴራል መንግሥት ስደተኞችን ለማስወጣት የሚያደርገውን ጥረት በሚቃረን መልኩ “የስደተኞች መጠለያ እንሆናለን” የሚሉ ከተሞችን አስጠንቅቀዋል። እነዚህ ከተሞች ስደተኞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ መግታት እንደማይችሉም ከዚህ ቀደም አስታውቀዋል።

ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋር ከቀናት በፊት ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ስደተኛ ወንጀለኞችን ወደ መጡበት እንዳንመልስ የሚያስቆመን ነገር የለም። ብታግዙንም ባታግዙንም ሥራችንን እንሠራለን” ብለዋል። “መጠለያ ከተሞች” ለፌዴራል መንግሥቱ የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሚሰጥ ገንዘብን ይገድባሉ።

ቦስተን እና ኒውዮርክን ጨምሮ ሌሎችም ግዛቶች ሀብታቸው በፌዴራል መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት ጥቅም ላይ እንዳይውል ገደብ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል። የትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ብዙ ትምህርት ቤቶች ለስደተኞች “መጠለያ” መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ከሜክሲኮ ድንበር 225 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የሎስ አንጀለስ ከተማ የትምህርት ቤቶች አካባቢ ፀረ ስደተኞችና ፀረ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ያላቸውን ውሳኔዎች የሚገዳደሩ ሕጎች አሏት። እነዚህም በዚህ አካባቢ ያሉ ተማሪዎችና ወላጆችን የሚጠብቁ እንዲሁም ለስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት የሚሰጥ መረጃን የሚገድቡ ናቸው።

የከተማዋ ምክር ቤት አባል ኒታያ ራማን “በፍርሃት አንሮጥም። በሁሉም ዓይነት መንገድ እንታገላችኋለን” ማለታቸውን ኤልኤ ታይምስ ዘግቧል። በዚህ ውሳኔ ከተማው ከትራምፕ ጋር መጋጨቱ አይቀርም። ትራምፕ ከሥልጣን ዘመናቸው መነሻ አንስቶ ስደተኞችን ለማባረር ቃል ገብተዋል።

ሎስ አንጀለስ በሕግነት የሚቀበለው ረቂቅ፣ ስደተኞችን ለማስወጣት ጥቅም ላይ የሚውል ገንዘብ ከከተማዋ እንዳይወሰድ ያደርጋል። ከፌዴራል መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት ጋርም ከተማዋ አትተባበርም።

የከተማዋ ምክር ቤት አባል ኒታያ ራማን ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ “የከተማዋን ግብዓት ተጠቅመው ስደተኞችን ማስወጣት አይችሉም” ብለዋል። የከተማዋ አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚጋሩት መረጃ ላይም ገደብ ይጥላል። የከተማዋ ከንቲባ ካረን ባስ ከፈረሙበት በኋላ በይፋ ይፀድቃል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You