በጋራ-አካል ጉዳተኛው ስለመብቱ ቀዳሚ እንዲሆን

አካል ጉዳተኞች ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍል እኩል በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። ለዚህ አስቻይ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸው በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባሉ ድንጋጌዎች ውስጥ ተቀምጧል:: አካል ጉዳተኞች ስለመብቶቻቸው የመሟገትና ጥቅማቸውን የማስጠበቅ ሚና ቢኖራቸውም ብዙ ጊዜ ስለመብቶቻቸው የሚከራከሩላቸው ጉዳት አልባ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው:: ከዚህ ይልቅ አካል ጉዳተኞች ግንባር ቀደም የመብቶቻቸው ተከራካሪ መሆን አለባቸው። መብቶቻቸው በምን ያህል እየተከበሩ ናቸው የሚለውን በትክክል የሚያውቀውና ጥቅሙንም ሆነ ጉዳቱን መግለጽ ያለበት ራሱ ባለቤቱ መሆን እንዳለበት ይታመናል።

ወይዘሮ ፋንታዬ ተክሌ በፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር የፕሮጀክት ስራ ሂደት አስተባባሪ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት አካቶነትን በጋራ /together for inclusion project/ በኢትዮጵያ ስራውን የጀመረው እ.ኤ.አ በ2021 ሲሆን፤ መነሻውን ያደረገው በኖርዌይ አስራሶስት የመንግሥት አካላትና መንግሥታዊ ያልሆኑ በአካል ጉዳተኛ ላይ የሚሰሩ ማህበራትን በማካተት ነው:: ፕሮጀክቱ የተጀመረበት ዋነኛ ምክንያትም በአካል ጉዳተኝነት ላይ እስከዛሬ ድረስ ስራዎች ቢሰሩም ብዙ ለውጥ ስላላመጣ መሆኑን ይናገራሉ::

“እስከዛሬ ድረስ አካል ጉዳተኛው አልነበረም ወደፊት ወጥቶ እየተናገረ ወይም መብቱን እየጠየቀ ያለው:: ከአካል ጉዳተኛው ይልቅ መብቱን እየጠየቁለት ያሉት ጉዳት የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው:: ከዚህ አንፃር ጉዳት የሌላቸው ሰዎችም ተካተውበት እና አካል ጉዳተኛውን አብቅተውት ወይም አቅም እንዲኖረው አድርገው አካል ጉዳተኛው የመሪነቱን ሚና እንዲይዝ ታስቦ ነው ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆን የተፈለገው::”

“አካል ጉዳተኛውን የአሽከርካሪው ወንበር ላይ ማስቀመጥ ወይም አሽከርካሪ ማድረግ አካል ጉዳተኛው ራሱ ስለመብቱ እንዲጠይቅና እንዲከራከር ማድረግ ነው የፕሮጀክቱ ዋነኛ የለውጥ ፅንሰ ሃሳብ:: ከዚህ ፅንሰ ሀሳብ በመነሳት ፕሮጀክቱ በስድስት የአፍሪካ ሀገራት ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል:: ኢትዮጵያም ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ ናት::” ይላሉ።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ስራውን ሲጀምር ሰባት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑና በአካል ጉዳተኛ ላይ የሚሰሩ ማህበራት በጋራ ተካተውበት ነበር:: ሁለቱ ስራውን አጠናቀው ወጥተዋል:: ለጊዜው አምስቱ አሁንም ስራውን እያከናወኑ ይገኛሉ:: የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ተጠናቆ ሁለተኛው ምእራፍ እ.ኤ.አ ከ2021 ጀምሮ ሲሰራበት ቆይቶ አሁን በታህሳስ 2024 ይጠናቀቃል::

አስተባባሪዋ እንደሚናገሩት ፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫውን ያደረገው በሶስት ጭብጦች ላይ ነው:: አንደኛው አካል ጉዳተኛው ሰብአዊ መብቱን እንዲጠይቅ፣ ሰብአዊ መብቱን አውቆ እንዲሞግት ነው:: ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው በርካታ የሰብአዊ መብት ሰነዶች አሉ:: ከነዚህ መካከል የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት ኢትዮጵያ ከፈረመች አስራ አራት ዓመት ሆኗታል:: ሰነዱ 50 አንቀፆች አሉት:: በሰነዱ የተካተቱ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን ማሳወቅም የፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫ ነው ::

ከዚህ በተጨማሪ የሕፃናት መብት ሰነድ፣ የአፍሪካ ቻርተርና ኢትዮጵያ የምትከተላቸው የዘላቂ የልማት ግቦች አሉ:: እነዚህንና የኢትዮጵያ የህግ ማሕቀፎች ብሎም የስራ ስምሪትና የመሳሰሉትን ሰነዶች ለአካል ጉዳተኞች የማሳወቅ ስራ ነው የሚሰራው:: በሁለተኛ ደረጃ የፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫ ጥራት ያለውና አቅምን ያገናዘበ ፍትሃዊ ትምህርት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው። ለዚህም ተማሪዎች በአካባቢያቸው በሚገኝ ትምህርት ቤት ገብተው የመማር ዕድል እንዲመቻችላቸው ማድረግ ነው:: ሶስተኛው የፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫ አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ማስቻል ነው::

በቀጣይ ግን እ.ኤ.አ ከ2025 እስከ 2029 ፕሮጀክቱ ሁለት ጭብጦችን ይዞ ይቀጥላል:: አንደኛው ጭብጥ ለአካል ጉዳተኞች አካታች የሆነ የጤና ተደራሽነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አካታች አየር ንብረት ነው:: በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ አምስት ጭብጦችን ይዞ እ.ኤ.አ እስከ 2029 ይዘልቃል::

ከዚህ በፊት በሶስቱ ጭብጦች ውስጥ ስራዎች ሲከናወኑ በነዚህ ጭብጦች ስር ማሕቀፎች ነበሩ:: የመጀመሪያው ለአካል ጉዳተኛው መድረስ፣ አቅሙን ማጎልበት፣ ያሉትን ነገሮች ማሳወቅ ነው:: ነገር ግን አካል ጉዳተኛው ይህን ሁሉ ብቻውን ማድረግ ስለማይችል ቤተሰብ፣ ማህበረሰብና ሀገር ሊደግፈው ይገባል:: ስለዚህ በአካል ጉዳተኛው ዙሪያ ያሉትን ሁሉ ማሳተፍ ያስፈልጋል:: ድጋፉ ደግሞ የሚጀምረው ከቤተሰብ ነውና ቤተሰብን የማብቃት ስራ ይከናወናል:: ሁለተኛው ማሕቀፍ የሚያተኩረውም ቤተሰብን በማብቃት ላይ ነው::

ሶስተኛው ማሕቀፍ ደግሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተለይም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት ነው:: ከትምህርት፣ ጤና፣ ኢንዱስትሪ፣ ስራ ስምሪትና ከሌሎችም አካላት ጋር መስራት ያስፈልጋል::

አስተባባሪዋ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አራት አመት አስቆጥሯል:: በእነዚህ አራት አመታት ውስጥ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያላቸው ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውን አውቀዋል:: በተለይ ለአካል ጉዳተኞች መብት በማሳወቅ ዙሪያ ፕሮጀክቱ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል:: ከዚህ ባለፈ ኢኮኖሚን በማሻሻል ረገድ የታየው ለውጥ ከፍተኛ ነው::

ከዚህ በፊት አካል ጉዳተኞችን በማህበር አደራጅቶ ስራዎች እንዲሰሩ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነበር:: ይሁንና አሁን ላይ በሃዋሳ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር እና በአዲስ አበባ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ጋር በማደራጀት የተለያዩ ሙያ ነክ ትምህርቶችን እንዲማሩ ማድረግ ተችሏል::

ለምሳሌ ጉዳት የሌለባቸው ተማሪዎች በሶስት ወር የሚያጠናቅቁትን የሙያ ትምህርት አካል ጉዳተኞች በስድስት ወር እንዲያጠናቅቁ ተደርጓል:: ለዚህም መንግሥት ቦታ ሰጥቷቸው በአዲስ አበባና በክልሎች በቆዳ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በከብት ፣ በዶሮ እርባታ እና በሌሎችም ስራዎች ተደራጅተው የራሳቸውን ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ:: ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደርና የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ማህበር ደግሞ ሌሎች የሚታዩ ስራዎችን አከናውነዋል:: በተለይ በወላጆች የገቢ ማሻሻያ ላይ ጥሩ ስራ ሰርተዋል:: ልጆቻቸው ተደራራቢ ጉዳት ያለባቸውና አልጋ ላይ የዋሉትን ልጆቻቸውን እያዩ እዛው ጋር የሚሰሩት ስራ ለምሳሌ እንጀራ መጋገር፣ ጠላ መሸጥና ሌሎችንም ስራዎች የሚሰሩበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You