ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ሊሰጡ እንደሚችል ተገለጸ። የቀድሞ የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስትር ሰር ጋቪን ዊሊያምሰን በቀይ ባህር ላይ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ ስላላት የሶማሊላንድ ይፋዊ እውቅና ከትራምፕ የፖሊሲ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ለኢንዲፔንደንት ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ትራምፕ በመጪው ጥር ስልጣን በያዙበት ፍጥነት ለሀርጌሳ እውቅናን ሊሰጡ ይችላሉ ነው ያሉት።
በ1991 ከሶማሊያ የተገነጠለችው ሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድታገኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩት የቀድሞ ሚኒስትር ከትራምፕ የፖሊሲ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው እንደነበር ገልጸዋል።
በውይይቱም ለሀርጌሳ እውቅና መስጠት በቀጣናው ባሉ የውሃ አካላት እና አካባቢው ላይ ሊኖር የሚችለውን በጎ ተጽዕኖ ማስረዳታቸውን ነው የተናገሩት።
ትራምፕ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከወሰኗቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች መካከል የአሜሪካን ጦር ከሶማሊያ ማስወጣት የሚለው አንዱ ነበር፤ ሆኖም ይህ ውሳኔ በባይደን አስተዳደር ተሽሯል።
የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው ሶማሊላንድ ከብሪታንያ ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት ያስቀጠለች ሲሆን፤ የሀገርነት እውቅናን ለማግኘት የተለያዩ ባለስልጣናትን እንደምትጠቀም ይነገራል። የቀድሞ ሚኒስትር ለኢንዲፔንደንት እንደተናገሩት፤ ትራምፕ እውቅናውን የሚሰጡ ከሆነ የቀጣናውን ጂኦፖለቲካ የሚቀይረው ይሆናል።
የሞቃዲሾን የሶማሊላንድ ይገባኛል ጥያቄ የሚደግፉት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እውቅና እንዲሰጣት የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገውታል። ምንም እንኳን ሶማሊያ የዓለም አቀፍ የባህር ላይ ወንበዴ እና የሽብርተኝነት ማዕከል ብትሆንም፤ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ይህንን አቋም አስቀጥለዋል።
ትራምፕ በ2020ው ምርጫ ከመሸነፋቸው በፊት ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና ለመስጠት ተቃርበው እንደነበር ያስነበበው የእንግሊዙ ጋዜጣ፤ ትራምፕ እውቅና የሚሰጡ ከሆነ ብሪታንያንም ተመሳሳዩን እንድታደርግ ሊያስገድዱ ይችላሉ ብሏል።
በኤደን ባህረ ሰላጤ እና በቀይ ባህር በተለያዩ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ የሚገኙት ሃውቲዎች፤ ለሶማሊያው አልሸባብ የከፍተኛ ጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ንግግር ላይ መሆናቸውን የአሜሪካ የስለላ ተቋማት አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም ትራምፕ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ያላትን ሶማሊላንድ ማጠናከር እና እውቅና መስጠት አማራጭ አድርገው ሊወስዱ ይችላሉ ነው የተባለው ሲል አል አይን ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም