የሠራተኞች እጥረት ያጋጠማት ጀርመን ተጨማሪ 200 ሺህ የሥራ ቪዛዎችን አጸደቀች

ከፍተኛ የሠራተኞች እጥረት ያጋጠማት ጀርመን በተለያየ ሙያ ለሰለጠኑ ባለሙያዎች 200 ሺህ የስራ ቪዛ ልትሰጥ መሆኑን አስታውቃለች።

የሠራተኞች ፋላጎትን ለማሟላት የቪዛ አሰጣጥ ስርአቷን ቀለል ባደረገችው ጀርመን ዘንድሮ ይሰጣል የተባለው የሰለጠነ የሰው ሀይል ቪዛ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ10 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

በርሊን ባለፈው አመት ከካናዳ የተዋሰችው “ኦፖርቹኒቲ ካርድ” በመባል የሚታወቅው አሰራር ለባለሙያዎች እና ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲማሩ እና ስራ መፈለግ ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል። ይህም ሆኖ በሀገሪቱ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሠራተኞችን የሚፈልጉ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የስራ ዘርፎች ክፍት ሆነው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከአውሮፓ ውጪ የሚገኙ ሙያ ያላቸው ሠራተኞች የሙያ ማረጋገጫ ማቅረብ ሳይጠበቅባቸው ለቪዛ እንዲያመለክቱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ሶስት የጀርመን የመንግሥት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ባወጡት መግለጫ በአመቱ መጨረሻ ከተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ 200 ሺህ የስራ ቪዛ አመልካቾችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

መግለጫው አክሎም አመልካቾች በጀርመን ለመማር እና ለመስራት ሲያመለክቱ ተጨማሪ የሙያ ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸው ገልጿል፡፡የአውሮፓ ህብረት ላልሆኑ ሀገራት ተማሪዎች የሚሰጠው ቪዛ በአሁኑ ወቅት በ20 በመቶ ጨምሯል፡፡

የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፋዘር “ ምስጋና ለኦፖርቺኒቲ ካርድ ይግባውና ባለሙያ ወጣቶች ስልጠናቸውን እና ትምህርታቸውን በጀርመን በቀላሉ ማጠናቀቅ ይችላሉ፤ ልምድ እና አቅም ያላቸው ሰዎች አሁን ተስማሚ ስራ በፍጥነት እና በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ” ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አናሊና ባርቦክ በበኩላቸው፤ “ጀርመን በየዓመቱ 400ሺህ ብሩህ አእምሮዎች እና ሀገራችንን ጠንካራ የሚያደርጉ ተጨማሪ እጆች ይጎድሏታል፤ ይህ ኢኮኖሚያችንን እንዲያዘግም ምክንያት ሆኗል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ይህን ለመቅረፍ በአውሮፓ እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የኢሚግሬሽን ህግ ፈጥነን ተግባራዊ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡

“ኦፖርቹኒቲ ካርድ” (የቪዛ እድል ካርድ) ምንድን ነው?

በርሊን ከካናዳ የወሰደችው የእድል ቪዛ ካርድ ተሞክሮ አንድ ሰው በብቃት፣ በእውቀት እና ልምዱ መሰረት ለቪዛው ብቁ መሆኑን ለመወሰን የሚረዱ ነጥቦች የሚፈተሸበት ነው፡፡

የሙያ ሁኔታዎች ፣ እድሜ፣ የጀርመን እና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ እንዲሁም ከጀርመን ጋር ቀደም ሲል የነበረ ግንኙነትም ለቪዛው ብቁነት መገምገሚያነት ከተቀመጡ መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የሚያመለክቱ ሰዎች በጀርመን በሚቆዩበት ጊዜ በወር አንድ ሺህ ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ በባንክ ሂሳባቸው ውስጥ ሊኖር ይገባል፡፡

ጀርመን ባለፉት አምስት አመታት ወደ 1ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ስራዎችን የፈጠረች ሲሆን ከዚህ ውስጥ 89 በመቶ የስራ መደቦች በውጭ ዜጎች የተያዙ መሆናቸው የዶቼቬለ ዘገባ አመልክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You