የሄዝቦላህ የሚዲያ ኃላፊ መሃመድ አፊፍ እስራኤል በመዲናዋ ቤይሩት በፈጸመችው ጥቃት መገደሉን ታጣቂው ቡድኑ አረጋገጠ።
ሕዝብ በሚበዛበት ራስ አል ናባ በተሰኘው ሰፈር የሚገኘውን የባዝ ፖለቲካ ፓርቲ ዋና መስሪያ ቤት እስራኤል በአየር ጥቃት መምታቷን የሊባኖስ መንግሥታዊ ሚዲያ ዘግቧል። የሀገሪቱ ጥበቃ ሚኒስቴር አራት ሰዎች መሞታቸውን ቢገልጽም የሰለባዎቹን ስም ዝርዝር አልጠቀሰም።
ከሄዝቦላህ ከቀሩት ጥቂት ባለስልጣናት እና ከፓርቲው ፊት አንዱ የሆነው አፊፍ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ቡድኑ መቀመጫውን ባደረገበት በቤይሩት ደቡባዊ አካባቢ ሰኞ እለት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው። ኃላፊው መሞቱ ሪፖርት ከተደረገ ከሰዓታት በኋላ ሄዝቦላህ እሁድ አመሻሹ ላይ መሞቱን አረጋግጧል።
በጥቃቱ የሊባኖስ ቅርንጫፍ የሆነው የሶሪያ ባዝ ፓርቲ ዋና መስሪያ ቤት አብዛኛው ህንጻው ክፍል ወድሟል። የነፍስ አድን እና የሲቪል መከላከያ አባላት በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው የነበሩ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ሲሰሩ እንደነበር የሀገሪቱ የዜና አገልግሎት ዘግቧል። የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተገደሉት አራት ሰዎች በተጨማሪ 14 ሰዎች መቁሰላቸውንም አስታውቋል።
የሊባኖስ ባዝ ፓርቲ በሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ የሚመራው የሶሪያ ባዝ ቅርንጫፍ ፓርቲ እና የረዥም ጊዜ የሄዝቦላ አጋር ነው። በሊባኖስ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው በመዲናዋ ቤይሩት በሚገኝ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ በሚጨናነቅበት ማዕከላዊ ስፍራ ላይ ነው።
ይህንንም ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ከሄዝቦላህ ባለስልጣናት ባለፈ ጥቃቷን እያሰፋች ነው የሚል ስጋት እንዳለ የቢቢሲ የመካለኛው ምስራቅ ዘጋቢ ሊና ሲንጃብ ትናገራለች። ሄዝቦላህ በፓርላማ ተወካዮች እና በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ሚኒስትሮች ያሉት የፖለቲካ ፓርቲ ነው።
“ይህ ጥቃት ሁኔታውን የሚያባብሱ ወይም መፍትሄ የመሻት ምልክቶች እንደሌሉ ለበርካቶች የማንቂያ ደወል ነው። ይልቁንም የበለጠ እየተባባሰ እና እስራኤል በሊባኖስ እያደረገችው ያለው ኢላማ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል” ብላለች።
ህዳር 8 ቀን 2017 ዓ.ም በማዕከላዊ ቤይሩት በማር ኤሊያስ ጎዳና ላይ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 13 ተጨማሪ ሰዎች መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አክሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም