የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ የሆኑ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑባት ነው፡፡ ከተማዋ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚያበቋት የተለያዩ መሠረተ ልማቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ፡፡
ሆኖም እንደስሟ አዲስ እየሆነች የመጣችው አዲስ አበባ ከዕድገቷ ጎን ለጎን በጸጥታ ችግርና በሕገወጥ ተግባራት መበራከት በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ ሕገወጥ ተግባራት ውስጥ ደግሞ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው በመርካቶ የሚስተዋለው ሕገወጥ ንግድ እና ግብይት ዋነኛው ነው፡፡
የሀገሪቱ ዋነኛ የንግድ ማዕከል በሆነው መርካቶ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ይስተዋላሉ፡፡ ለአብነትም የሽያጭ መጠንን ዝቅ በማድረግ የሚፈጸም ግብር መሰወር፣ ግዢን ዝቅ በማድረግ የሽያጭ መጠን እንዲቀንስ እየተደረገ የሚፈጸም የግብር ስወራ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ የተለያዩ የማስከፈያ ምጣኔዎች ያለአግባብ በማቀያየር የሚፈጸም የግብር ስወራ፣ የተሰበሰበን ታክስ (VAT) ከሕዝብ ላይ ቢቀነስም ለመንግሥት አለመክፈል፣ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በሕገወጥ መንገድ በማስገባት ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስቀረት፣ ሀሰተኛ የታክስ ተመላሽ መጠየቅ፣ በሀሰተኛ ደረሰኝ ገቢ መሰብሰብ እና የመሳሰሉት የግብር ሥራዎችና ማጭበርበሮች ይከናወናሉ። ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም እስከ 80 በመቶ የሚደርሱት በመርካቶ የሚካሄዱ ግብይቶች በሕገወጥ መንገድ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡
በዚህ ሒደት ውስጥ ጥቂት የሚባሉ ነጋዴዎች ሕጋዊውን የግብይት ሥርዓት የሚፈጽሙ ቢሆኑም አብዛኞቹ ነጋዴዎች የግብይት ሥርዓታቸውን የሚያካሂዱት በሕገወጥ መንገድ በመሆኑ መንግሥት መሰብሰብ የሚገባውን ከፍተኛ ግብር በማሳጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ተግባራት በየዓመቱ የሚፈጸሙ የግብር ማጭበርበሪያ ስልቶች ስለሆኑ እንደሀገር የተቀየሱ ዕቅዶች በአግባቡ ተግባራዊ እንዳይሆኑ በማድረግ ዕድገትን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው፡፡
ግብር መክፈል ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንጻር አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር፤ በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ግብር መክፈል ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ይህንም ተግባራዊ አለማድረግ ደግሞ የወንጀልና አስተዳደራዊ ቅጣቶችንም ያስከትላል፡፡
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ ግብር አስፈላጊነትና ግዴታ ከተደነገገው በተጨማሪ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116 እና በተመሳሳይ ድንጋጌዎች ግብርን አለመክፈል፣ ማጭበርበር፣ ግብር መሰወር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ማጭበርበር እና በጠቅላላው ከታክስ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎች በእስር እና እንደየወንጀሉ ክብደት በብርም የሚያስቀጡ ናቸው፡፡
በልማት ግስጋሴ ውስጥ የምትገኘው የኢትዮጵያ ዕድገት እና ብልጽግናዋን ለማሳካት በቂ የገንዘብ ምንጭ ያስፈልጋታል፡፡ ዋነኛው የገቢ ምንጭ ደግሞ የሀገር ውስጥ ገቢ ነው፡፡ ዘንድሮ እንደ ሀገር የተያዘው የገቢ ዕቅድ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ እቅድ ሀገሪቱ በ2016 በጀት ዓመት ካገኘችው ጠቅላላ ገቢ ከሁለት እጥፍ በላይ ነው፡፡
ስለዚህም የተያዘው ዕቅድ ግዙፍ ከመሆኑ አንጻር ከወትሮው በተለየ መልኩ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እና ሕገወጥ ተግባራትን መከላከል ይጠይቃል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ዜጎች እንዲሠሩ በማበረታታት የታክስ መሠረቱን ማስፋት እና በታክስ ማጭበርበር ላይ የሚታዩ ሕገወጥ አካሄዶችን እየተከታተሉ ማረም ይገባል፡፡
በዚህ ረገድ መንግሥት በመርካቶ ሕጋዊ ግብይት እንዲሰፍን እያደረገው ያለውን ጥረት ለማደናቀፍ የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑ ታይቷል፡፡ ይሄ ለነጋዴው ራሱ የማይጠቅም፣ ሀገርን የሚጎዳ እና ትውልድ የሚገድል አጉል ተግባር በመሆኑ መንግሥት ሕግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ርምጃ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም በመርካቶ ሕጋዊ የገበያ ሥርዓት እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ ሀገር የሚጸናው በዜጎች ባለቤትነትና ተሳትፎ ነውና ስለሀገራቸው የሚቆረቆሩ ዜጎች ሕገወጥ ተግባራትን በማውገዝና በሕግ ማስከበሩ ተግባር አጋር በመሆን የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም