በኅብረ ብሔራዊነት የደመቀች ጠንካራ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ!

ኢትዮጵያ አንድም ብዙም መገለጫ አላት፤ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ በአንድ የወል መጠሪያ ተሰይመው፤ በብዝሃነት ሕብረ ውበት አጊጠው፤ ብዙም አንድም ሆነው የሚገለጥ ማንነት ባለቤት ናቸው። ትናንት በአንድነታቸው ውስጥ አጠንክረው ያነጹት ኢትዮጵያዊነት፤ ዛሬም በብዝኃነታቸው ቀለም አድምቀው የከተቡት የሕብረብሔራዊነት ሰንደቅ አላቸው።

አበው “ድር ሲያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ፤ የበዛው ማንነታቸው የልዩነት ምንጭ ሳይሆን የመተባበራቸው ኅብራዊ ውበት ሆኖ፤ የአብሮነታቸው ደማቅ ግን እንዳይነጣጠሉ አስተሳስሮ የያዛቸው የብዝኃ አንድነታቸውን ገመድ ፈጥሮ ከትናንት እስከ ዛሬ አዝልቋቸዋል። ከዛሬ ባለፈን ነጋቸውን ለመሥራት በሚያስችላቸው ልክ በኅብር እንዲቆሙ ምክንያት ሆኗቸዋል።

ወርሃ ሕዳር ደግሞ፣ የአንድነታቸው ብቻ ሳይሆን የብዝኃነታቸው ዓርማ ደምቆ የታየበት፣ የውል ሰነድ የተከተበበትም ነው። በተለይ ከኢፌዴሪ ሕገመንግሥት መጽደቅ ጋር በተያያዘ፤ የኢትዮጵያ መልከ ብዙነት፤ የኢትዮጵያውያንም ኅብረ-ብሔራዊነት ከእውነትነት ባሻገር ላለው ቅቡልነት መሠረት መጣል ተችሏል።

የትናንት አብሮነታቸው በጽኑ መሠረት ላይ እንዲኖር፤ የዛሬ እውነታቸው እንዲገለጥ፤ የነገ ሕልምና ተስፋዎቻቸው በወል እሳቤያቸው ላይ ይገነባና ይመራ ዘንድ እርሾ ሆኖም እያገለገለ ይገኛል። በዚህም ሕዳር 29ኝ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ብሎ በመሰየም፤ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመግለጥ የተሄደበት አግባብም ነበር።

ይሁን እንጂ ይሄ ሕገ መንግሥታዊ ማረጋገጫ ያገኘው የኅብረ-ብሔራዊ አንድነታቸው ጉዳይ ከወቅቱ የፖለቲካ ሥሪት አኳያ ባልተገባ መልኩ እንዲገለጥ ሆኖ ቆይቷል። ምክንያቱም፣ ሁነትና ሂደቱ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነት ላይ፤ ከመተባበር ይልቅ መነጣጠል ላይ፤ ከሚያሰባስቡ ትርክትና እሴቶች ይልቅ በሚከፋፍሉ አጀንዳዎች ላይ፤… ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ ቆይቶ ነበርና።

ይሄም ከወል ማንነት በላይ ተናጠላዊ ማንነት ገዝፎ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እስኪረሱ በደረሰ መልኩ እንዲፈረጁ ጥረት ተደርጓል። በተወሰነ ደረጃም ባይሆን ጥረቱ ፍሬ ለመቋጠር ደርሶም ነበር። ለዚህም ነው በተለይ በለውጡ ማግስት ችግሮች፣ መፈናቀልና አለመረጋጋቶች፣ እልፍ ሲልም ጦርነቶች እዚህም እዚያም መታየታቸው።

የዚህ ችግሩ ታዲያ፣ ኢትዮጵያዊነት እንዲጠላ፤ የብሔር ማንነት ከፍ ብሎ እንዲወጣ እና በብሔር ጥላ ስር የሀገርነት እሳቤ እንዲያቆጠቁጥ በመደረጉ ነው። በማንነት መብት ስም የመነጣጠል ትርክት ሥር እንዲሰድ በመሠራቱም ነው። ከኢትዮጵያ ይልቅ ለክልል፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ለተናጠላዊ ማንነት ከፍ ያለ ሥፍራ እንዲሰጥ በመሰበኩም ነበር።

ሆኖም ይሄ የተሳሳተ አካሄድ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የትናንት የበዛ የጋራ ታሪክ፣ መንገድና ገድላቸውን እንዳያውቁት፤ በኢትዮጵያ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚናና ድርሻ እንዳይገነዘቡት፤ እንደ ሀገር የወደፊትን ተልሞ እና ተባብሮ የመሥራትን አቅምነት ሳይሆን፣ ለብቻ በመቆም ውስጥ ከፍ ያለ ጥቅም የመገኘቱን አማላይ ግን ከእውነት የተፋታ ትርክት ደ ጋግመው እንዲያደምጡ በማድረግ ውስጥ የተቃኘ ነበር።

ለዚህም ነው ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ታዲያ ይሄንን የተሳሳተ ትርክት የማረም፣ እውነተኛውን እና ለኢትዮጵያም፣ ለኢትዮጵያውያንም የሚጠቅመውን የወል መንገድ፤ በኅብር የደመቀውን አብሮነት፤ ትክክለኛውን ኅብረ-ብሔራዊ ዴሞክራሲ በተግባር መግለጥ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው።

ከተናጠል ይልቅ በጋራ መቆም ያለውን የላቀ አቅም በኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በጋራ ሆኖ የተሠራውን ሥራ ታላቅነት የመግለጥ ሥራ መጀመሩ፤ ከነጣጣይ ትርክቶች ይልቅ ለአሰባሳቢ ሀገራዊ አብይ ትርክቶች ቦታ መሰጠቱ፤ እውነተኛ የኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እቅኝቱ ኢትዮጵያውያን ማንነታቸውን ከፍ አድርገው ደግሞም ኢትዮጵያዊነታቸውን አልቀው በማይጋጭ ማንነት ውስጥ እንዲገለጡ በሚያደርግ መልኩ እየተተገበረና ውጤት እያስመዘገበ መምጣቱ፤… የትናንት ስህተትን ለማረም እንዲቻል ነው።

ይሄ ጅምር የትናንት ስህተትን ማረም ላይ ብቻ ያተኮረም አይደለም። የዛሬን ተጨባጭ ሃቅና እውነት በመግለጥ፤ ከትናንት ጉዳይ አሰላሳይነት (ባለፈ ሁነትና ክስተት ላይ ተቸካይነት) ማላቀቅንም ማዕከል ያደረገ፤ ከትናንት ይልቅ ዛሬ የተሻለ ስለመሆኑ፤ ከዛሬም ደግሞ ነገ በእጅጉ የተሻለ ስለመሆኑ፤ እናም በእጅጉ ለተሻለው ነገ ሲባል ትናንት ላይ ከመቸከል ይልቅ የትናንቱን ረስቶም፣ በይቅርታ ተሻግሮም ለልጆቻቸው መልካም ዕድልን በሚያኖረው ነገ ላይ ማተኮር እንደሚገባም የሚያስገነዝብ ነው።

ይሄ እጅጉን የተሻለው ነገ፣ ለልጆቻችን የተሻለ እድልን የምናቀብልበት ነገ፤ ከትናንት ቁርሾና ንትርክ ነጻ የሚያወጣን ነገ፤ ከመነጠል ይልቅ በኅብር የመቆማችንን ኃያልነት እንድንገነዘብ የሚያደርገን ነገ፤… ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም። ዛሬን መሥራት፤ ዛሬን ዋጋ መክፈል፤ ዛሬን በንጹህ ልብ ሆኖ ቁጭ ብሎ መነጋገር፤ ዛሬን ስለ ትናንት ሳይሆን ስለ መጪው እያሰላሰልን የተሻለ ነገርን የመተለም ልዕልናን ከእኛ ይሻል።

እናም ነገ ይሄን መሰሉ የሰው ልጅ ልዕልና ገንዘባችን እንድናደርግ ይፈልጋል ሲባል፤ ማንነታችንን ይዘን ኢትዮጵያዊነታችንን ከፍ ማድረግ፤ አንድነታችንን አጠንክረን ኅብረ-ብሔራዊነታችንን መግለጥ፤ ታሪካችንን ከተዛባ መስመሩ አውጥተን በትክክለኛና እውነተኛው ትርክት ማነጽና የጋራችን የሆነውን ሃቅ ማኖር፤ ትናንት ልክ ነው ተብሎ በተፈጸመው ችግር ተተብትበን ከመባላት ወጥተን፣ ስለ ልጆቻችን ብሩህ ነገና ዕጣ ፈንታ በወል ሆነን አስበን በወል ሆነን የምንራመድበትን አውድ መሥራት ማለት ነው!

አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You