-10 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ተከፍሏል
አዲስ አበባ:- ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉንና 10 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ መከፈሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።ማሻሻያው የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሀገራዊ ዕቅዶችና አፈጻጸሞች ዙሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ፕራግማቲክ ካፒታሊዝም እየተሸጋገረ ነው፡፡ባለፉት ስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል፡፡10 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ ተከፍሏልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን አንስተው፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ፣ኢንዱስትሪ. ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ያስፈልጋል ያሉት ፍጹም (ዶ/ር)፤ የተሻለ ተቋምና የተፈጥሮ ሀብት ያለው ሀገር ውጤታማ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት አለበት ብለዋል።
መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለአንድ ሀገር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ አምራች ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂ ልህቀት፣ በተማረ የሰው ኃይል መደገፍ ለዘላቂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ፕራግማቲክ ካፒታሊዝም እየተሸጋገረ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት 10 ቢሊዮን ዶላር የውጪ እዳ እንደተከፈለ ተናግረዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በትግበራ ላይ የሚገኘው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወቅቱን፣ ሁኔታዎችንና ሕዝብን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውም የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት የሚበረታታበት፣ በወሳኝ ዘርፎች ላይ የመንግሥት ተሳትፎ የሚታይበት መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጡ መንግሥት በቀጣይነት ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን የሚያስችሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጉን ጠቅሰው፤ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በቂ ኢነርጂ በማቅረብ፣ ግብርናን በማዘመን፣ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ አቅም በማጎልበት፣ የማዕድንና የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት፣ በቱሪዝም፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ላይ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ባለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካኝ 4 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን በመግለጽ፤ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም በአማካይ አንድ ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ጨምሮ የፋይናንስ ዘርፉና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም