አዲስ አበባ:- አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ተኪ ምርቶችን በማምረት በሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጳውሎስ በርጋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ማሽኖችን ጨምሮ ከውጭ ሀገር ይገቡ የነበሩትን የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ጀምረዋል፡፡
ኢንተርፕራይዞቹ የሚያመርቱት ማሽኖች በተለይም ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ የሚያገለግሉ፣ ለጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ እና የቆዳ ምርትን ለማምረት የሚውሉ ማሽነሪዎችን ጭምር ማምረት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በትግበራውም በሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም አቶ ጳውሎስ አመልክተው፤ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ሀብት፣ ሕዝብ እና የገበያ ሁኔታ አኳያ የኢንተርፕራይዞቹ ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ ይህንን መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አብዛኞቹ ኢንተርፕራይዞችም መንግሥት ባደረገው ምቹ ሁኔታ ከለውጡ በኋላ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው በርካታ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው፣ ሥራ የሚፈጥሩ ወጣቶች መውጣት እንደሚቻል መመልከት ተችሏል ብለዋል፡፡ በቀጣይም የበለጠ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠይቅም ነው የጠቆሙት፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል የውጭ ሀገርን ተሞክሮ በማጥናት በሊዝ ፋይናንስ አማካኝነት አዲስ ሥርዓት ተዘርግቷል ያሉት አቶ ጳውሎስ ፤ ሥርዓቱ የማሽነሪውን 20 በመቶ ብቻ በመቆጠብ፣ ቤት ከተከራዩ የኪራይ ውል ብቻ በማቅረብ ማሽን የሚያገኙበት እና በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እየሰሩ የማሽን ግዢ የወሰዱትን እዳቸውን የሚከፍሉበት ሁኔታ የተመቻቸላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሥራ ማስኬጃ ሌላው ትልቁ ችግራቸው መሆኑን በማንሳትም፤ ችግሩ አሁንም አለ፤ በተለይም የባንኮች የማበደር መስፈርቶች ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች አመቺ አይደሉም ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ኢንተርፕራይዞቹ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል እንዲያገኙ መደረጉን አንስተው፤አዳዲስ ወደእዚህ ዘርፍ ለሚገቡ ጀማሪ እንደመሆናቸውና ሀብት ገና ለማፍራት የሚንደረደሩ በመሆኑ እንዳይቸገሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
የሚጠየቁ መስፈርቶች የማስያዣ ችግር እንዳይፈጠርባቸው መቅረፍ እንደሚያስፈልግ መንግሥት በልማት ባንክ በኩል አዲስ ሥርዓት የሚጀመር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የማስያዣ የሚጠየቀውን በተወሰነ መልኩ መንግሥትም ኃላፊነቱን የሚጋራበት አሰራር እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
ከማምረቻ ቦታ አኳያ፣ የብድር አሰጣጥን ቀለል በማድረግ፣ ባንኮች ከትርፍ በዘለለ በተመጣጣኝ ወለድ ኢንተርፕራይዞቹን የሚደግፉበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
ከማምረቻ ቦታ ጋር ተያይዞም በተለይ የግል ባለሀብቶች እንደሪል እስቴት ወደዘርፉ ገንብተው የሚያከራዩበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡ የበለጠ ቢታገዙ የበለጠ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት እድል ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ አነስተኛ እና መካከለኛ አንተርፕራይዞች አሉ፡፡ በአጠቃላይ 74 ቢሊዮን ብር አካባቢ ያንቀሳቅሳሉ፤ በቀጥታ አንድ ሚሊዮን አካባቢ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ አምራቾቹ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና በተወሰነ መልኩ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መላክ ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡
ለኢንተርፕራይዞቹ የቴክኒክ፣ የማምረቻ ቦታ፣ የማሽነሪ አቅርቦት፣ ብድር እና ግብአት የሚያገኙበትን ሁኔታ በሚመለከት የተሟላ ድጋፍ እንደሚደረግም አመልክተዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም