አዲስ አበባ፡- የነገውን ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ብሎም ሀገርን ሙሉ ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ የሕፃናት መብትና ጥቅም የሚያስከብር ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን “ሕፃናት የሚሉት አላቸው፤ እናዳምጣቸው” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ሁነቶች ዛሬ ይከበራል፡፡
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ተስፋዬ፤ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀንን አስመልክተው ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን የባለድርሻ አካላት፣ የማህበረሰቡ ተሳትፎና ግንዛቤ በማሳደግ የሕፃናት መብት ለማስጠበቅ ባለመ መልኩ ይከበራል ብለዋል፡፡
የነገውን ሀገር ተረካቢ ብቁ ዜጋ ለማፍራት ብሎም ሀገርን ሙሉ ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ የሕፃናትን መብትና ጥቅም የሚያስከብር ማህበረሰብ መፍጠር ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
ሕፃናትን ማዳመጥ ማለት መብቶቻቸውን ከማክበር ጎን ለጎን ማግኘት ያለባቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው ያሉት ወይዘሮ እመቤት፤ ከሕፃናት መብት ደህንነት ጋር በተያያዘ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ወይዘሮ እመቤት ፤ ቢሮው በተለይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው ሊያስቀሯቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮችን በመለየት እየሰራ እንደሚገኘ ገልጸው፤ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣የጤና አገልግሎት፣ከቤተሰብ የተለዩ ሕፃናት ቤተሰብ እንዲያገኙ ማድረግና የቀዳማይ ልጅነት እድገት እየተሰሩ ከሚገኙት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሕፃናት የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎዎች በመሆናቸው በአካላዊም ሆነ በስነ ልቦናዊ የጠነከሩ ለማድረግ እንዲቻል በከተማው ከ10 ሺህ 800 በላይ እናቶችና ሕፃናት በቀዳማይ ልጅነት አልሚ ምግብ እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ እመቤት ገለጻ፤ የሕፃናትን መብቶች ማሳደግና ጥቅም ማስጠበቅ፤ተግዳሮቶችን መሞገት፤ መንግሥት በዘርፉ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ማበረታታት እንዲሁም ሕፃናትን በአእምሯዊና በአካላዊ ማብቃት የበዓሉ ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው፡፡ ሕፃናት ፍላጎታቸውን፣ ሃሳባቸውን፣ ህልሞቻቸውን እንዲሁም ተሳትፏቸውን በማሳደግ የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ መወሰን እንዲችሉ ለማድረግም ነው፡፡
በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት ደህንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ታፈሰ በበኩላቸው፤ የሕፃናትን ጥቃት ለመቀነስ ማህበረሰቡ ስለ ሕፃናት ጥቃት ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ ከጎናቸው ቆሞ መሞገት አለበት ብለዋል፡፡
አቶ አንዱዓለም፤ የሕፃናት ጥቃት ከአካላዊ ጋር ብቻ ሳይሆን ከስነ-ልቦናዊም ጋር አያይዞ መመልከት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ልጆች የወላጅ ወይም የቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆኑ የማህበረሰቡና የሀገር በመሆናቸው ማንኛውም ዜጋ የሚደረጉ እኩይ ተግባራት ሲያይ አያገባኝም በሚል ስሜት ማለፍ እንደሌለበት መክረዋል፡፡
በከተማው በ2016 ዓ.ም በትምህርት ቤቶች በተሠራ የዳሰሳ ጥናት አንድም ትምህርት ቤት ከሕፃናት መድሎ ነጻ ትምህርት ቤት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበር በዓል ነው ተብሏል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም