ድጋፉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው

አዲስ አበባ፡- የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ለማድረግ ያደረገው የግማሽ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን የአሜሪካ አምባሳደር ገለጹ፡፡

የአሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዘጠኝ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ ለማድረግ የሚያስችል የግማሽ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ እንደገለጹት፤ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርጉትን ሂደት ለመደገፍ ያደረገው የ522 ሺህ ዶላር ድጋፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው፡፡

ድጋፉ አሜሪካ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን አመልክተው፤ በዚህም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱን ብቁና ተወዳዳሪ በማድረግ ዓለም አቀፍ ብቃት ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል፡፡

አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች 120 ዓመታት ያስቆጠሩ መሆኑን አምባሳደሩ አንስተው፤ የተደረገው ድጋፍም የሁለቱን ሀገራት የረጅም ጊዜ አጋርነት የሚያሰፋ እና የሚያጠናክር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዓለም ላይ ከሚገኙ ቀዳሚ ተመራጭ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙባቸው ሀገራት መካከል አሜሪካ በቀዳሚነት የምትጠቀስ መሆኗን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም ይህንኑ አላማ ለማሳካት ለምታደርገው ጥረት የአሜሪካ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በላይ ካሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ የማድረግ ተግባርን እየተገበረች ይገኛል ብለዋል፡፡

ድጋፉ በሀገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ለመሆን የሚያደርጉትን እንደ መመሪያ ፣ ሕግና ደንብ የመሳሰሉ ቅድመ ዝግጅቶች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁና እና አንድ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማሟላት የሚጠበቅበትን መስፈርት እንዲያሟላ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ ለ9 ለሚሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ በራሳቸው መስፈርት ተማሪን አወዳድረው የሚቀበሉና ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የተማረ የሰው ኃይል መስክ በመለየት በራሳቸው ሥርዓተ ትምህርት ለመስጠት እንዲችሉ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በራሳቸው በጀት ሠራተኛ የመቅጠርና ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም የማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ብሎም ብቁና ተወዳዳሪ በማድረግ የትምህርት ጥራት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በአሜሪካ የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ በመሆናቸው ጥሩ የልምድ ልውውጥ የሚገኝበት መሆኑንም ፕሮፌሰር በላይ አስታውቀዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You