ኮሚሽኑ በ615 ወረዳዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ማጠናቀቁን አስታወቀ

 – በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በቅርቡ ይጀመራል

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 615 ወረዳዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመርም ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሚሽኑን አፈጻጸም ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የምክክር፣ የአጀንዳ ልየታ እንዲሁም ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን በአሠራር ሥርዓቱ ማስመረጥ፣ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም ሀረሪ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራውም በአብዛኛው ተጠናቋል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ በቅርቡ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚጀመር የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ለዚህም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑንና በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አመላክተዋል፡፡

በአማራ ክልልም በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተባባሪዎችን የመለየትና ሥልጠና የመስጠት ሥራ ቀደም ብሎ መከናወኑን አስታውሰው፤ ክልሉ ላይ አስቻይ ሁኔታ ሲኖር አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራው የሚጀመር ይሆናል፡፡

የምክር ቤት አባላት በትግራይ ምክክር መጀመር የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል፡፡

በክልሎች ከሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ በተጨማሪ የፌዴራል ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሂደት በቀጣይ እንደሚከናወን ገልጸው፤ በጥቅሉ አራት ሺህ የሚሆኑ ተሳታዎች በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ እንደሚሳተፉም ጠቅሰዋል፡፡

ዳያስፖራዎች በምክክር ሂደቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥራዎች ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አመላክተው፤ አስር የውይይት መድረኮች በበይነ መረብ አማካኝነት ተካሂደዋል፡፡ በዚህም በርካታ ጠቃሚ ምክረ ሃሳቦች ተገኝተዋል፤ በሂደቱ ላይም ግልጽነት መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋቅራዊ የሆኑና ከትናንት የወረስናቸው በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን ችግሮች በምክክር ይፈታሉ ብሎ ያምናል፡፡

ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የምክር ቤት አባላትም እንደሀገር ሀገራዊ ምክክር ጉዳይ የጋራ ግንዛቤና መግባባት ኖሮን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት ከኮሚሽኑ ገለልተኝነት፣ የሥራ ጊዜው መጠናቀቅ፣ የሴቶችና የሌሎችም ባለድርሻዎች ተሳትፎ እና በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላትን ወደ ምክክር ለማምጣት የተደረጉ ጥረቶች ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በሰጠው ምላሽ ሥራውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በገለልተኝት እያከናወነ መሆኑን፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ለማሳተፍ እየሠራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላትን የማደራደር ሚና ባይኖረውም እነዚህ ወገኞች አለን የሚሉትን ጥያቄ ይዘው ወደ ምክክሩ እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ መቆቱን አመላክቷል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You