– የንግድ ግብይቶች በደረሰኝ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጧል
አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሶስት ወራት ሁለት ሺህ 780 ቤቶች ተገንብተው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች መተላለፋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ግንባታቸው የተጓተተ የመሰረተ ልማት ስራዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ እና የንግድ ግብይቶች በደረሰኝ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡም ተመላክቷል፡፡የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን ትናንት አካሂዷል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ በዓመት የሚሰሩ ስራዎች በሩብ ዓመት ተከናውነዋል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ሁለት ሺህ 780 ቤቶች ተገንብተው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች መተላለፋቸውን አውስተው፤ግንባታቸው የተጀመረ ከአራት ሺህ በላይ ቤቶች በመንግሥት በጀት እና በአጋር አካላት ድጋፍ በማጠናቀቅ ለኮሪደር ልማት ተነሺዎች መሰጠቱን ጨምረው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ባለሀብቶችን በማስተባበር ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የክረምት ወጪ መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት።
በጤና መድህን፣ በማዕድ ማጋራት፣ በገበያ ማእከላት፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎች መከናወቸውን አስረድተዋል።የንግድ ሥርዓቱን በሚመለከት በከተማዋ የሚደረጉ ግብይቶች በደረሰኝ እንዲከናወኑ አቅጣጫ መቀመጡን አመላክተዋል፡፡
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመርካቶ ላይ በተደረገው ጥናት የእቃው ምንጭ ከየት እንደሆነ ያለመታወቅ ችግር መኖሩ ተረጋግጧል። ግብር የሚሰበስቡ አካላት ትኩረት የሚያደርጉት ፊት ለፊት የሚሸጡት ላይ እንጂ የእቃው ምንጭ ከየት ነው የሚለውን አያረጋግጡም ።
ግብር ማስከፈል እና ደረሰኝ ማስቆረጥ የመንግሥት ግዴታ በመሆኑ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን ገልጸው፤ በውይይቱም ግብር መክፈል ግዴታችን አይደለም ያለ ነጋዴ ሳይሆን ያጋጠመን ግብር የማይከፍሉ እንዳንድ ነጋዴዎች መኖራቸውን ነው የተገነዘብነው ብለዋል፡፡
ግብር ለማስከፈል እና ግብይቶችን በደረሰኝ ለማስደረግ መርካቶ በሚገኙ መጋዘኖች ሲኬድ እቃ ሊወረስ እና ሊዘረፍ ነው የሚሉ ውዥንብሮች መከሰታቸውን እንዲሁም በሌሊት እቃዎችን በማስጫን መጋዘኖችን ባዶ ሲያደርጉ እንደነበር ገልጸው፤ ይህ ተግባር ትውልድን የሚጎዳ በመሆኑ ማረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ግብር ማስከፈል እና ደረሰኝ ማስቆረጡ ግዴታ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ አካላት ላይ ህጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል የተጓተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት የማከናወን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት፣ ለልማት ተነሺዎች ተገቢውን ካሳ የመስጠት ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
ከ10 ዓመት በፊት የተገነባው የአራዳ ክፍለ ከተማ የስብዕና መገንቢያ ማዕከል በሰዎች ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል የጥራት ችግር እንዳለበት በጥናት መረጋገጡን ገልጸው፤ ችግሩን በማረም እና ስታንዳርዱን ጠብቆ በጥራት በመገንባት ወጣቶች እንዲገለገሉበት ይደረጋል ብለዋል፡፡ምክር ቤቱ የተለያዩ አዳዲስ ሹመቶችን በማጽደቅ እና የአመራር ቦታ ለውጥ በማድረግ ተጠናቋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም