አዲስ አበባ፡– አምና በዓመት ያላገኘውን የወርቅ ምርት ዘንድሮ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ማግኘት መቻሉን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ፡፡
በዘንድሮ በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 548 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉን ጠቁሟል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ሩብ ዓመት 413 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ታቅዶ ፤ 548 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል፡፡ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመታዊ እቅድ አንጻር ሲታይ በእጅጉ ለውጥ አሳይቷል፡፡
በባለፈው በጀት ዓመት ወደ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት 274 ኪሎ ግራም መሆኑን ያስታወሱት አቶ አድማሱ፤ ዘንድሮ በሩብ ዓመቱ ብቻ የተገኘ የወርቅ ምርት በእጥፍ ብልጫ ያለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የወርቅ ምርት ላይ ለውጥ ለመምጣቱ ዋንኛው ምክንያት አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሆኑን አንስተው፤ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በመጨመሩ ምክንያት ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚገዛበትን ዋጋ ማሻሻያ ማድረጉ ወርቅ በሕጋዊ መንገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ምክንያት መሆኑን አመልክተው፤ በተጨማሪም በክልሉ ሕገ ወጥነት ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በመሥራቱ ለውጦች መመዝገባቸው አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አስረድተዋል።
አቶ አድማሱ እንዳሉት፤ በክልሉ የወርቅ ክምችት ያላቸው ስምንት ወረዳዎች አሉ፡፡ከእነዚህም መካከል በአሶሳ ዞን ፣ በከማሼ እና መተከል ያሉ ወረዳዎች ወርቅ አምራችነት ይጠቀሳሉ፡፡ በክልሉ ወርቅ የማምረትና የማዘዋወር ፍቃድ የወሰዱ ባህላዊና ልዩ አነስተኛ 421 ማህበራት አሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንድ በከፍተኛ ደረጃ ወርቅን የማምረት ፈቃድ ያለው አምራች ያለ ሲሆን፤ አምራቹ በሩብ ዓመቱ ለማምረት ካቀደው 13 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ፣ ሁለት ኪሎ ግራም ብቻ ማምረቱንና ከዝናብ ጋር ተያይዞ ለማምረት እንዳላስቻለው ጠቁመዋል፡፡
አብዛኛውን በሩብ ዓመቱ የተገኘው የወርቅ ምርት ከባህላዊና ከልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ማህበራት የተገኘ መሆኑን አውስተው፤ በተለይ ወርቅ ለሕገ ወጥነት የተጋለጠ እንደመሆኑ በሕገ ወጥነት ሲፈተን እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
ቀደም ሲል የወርቅ ዋጋ ልዩነት መኖሩ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባውን የወርቅ መጠን እንዲቀንስ ሲያደርገው እንደነበር አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ የወርቅ ዋጋን መንግሥት እየተቆጣጠረው ነው ማለት የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም የወርቅ ምርት በአግባቡ ወደ ባንክ እንዲገባና ለውጦች እንዲመጡ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በወርቅ ዙሪያ ከሚነሱ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የወርቅ አምራቾች ሆኑ አዘዋዋሪዎች በሕገወጥ መንገድ የሚያደርጉት ዝውውር ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ አለመቻሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ያመረቱትን ምርቶች ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት ላይ አሁንም ክፍተቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ከግብረ ኃይሉ ጋር በመሆኑ የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገም የሚደረጉ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ኅዳር 11 ቀን 2017 ዓ.ም