ተስፋው የሚታይና የሚጨበጥ ነው

ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ሀገረ መንግሥት እና ሉዓላዊ ግዛት ባለቤት ነች። በሥልጣኔም ቢሆን በአንድ ወቅት ኃያልና ፊት መሪ ነበረች። ይህንን እውነታ ለማስረዳት ልፋትን የሚጠይቅ፤ ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ የሚያስገባ አይደለም። ዛሬም ህያው ሆነው የቆሙ ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔን ባለቤትና ጥንታዊ ሀገረ ምስረታ ምሳሌ እንደሆነች የሚመሰክሩ ቅርሶችን፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን እና የኪነ ሕንፃ ውጤቶችን መመልከት ብቻ በቂ መልስ ይሰጣል።

‹‹ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ሥልጣኔ ባለቤት ነበረች›› ስንል በባዶ ሜዳና ጥቅም በሌለው እንቶ ፈንቶ እራስን እንደ አረፋ ለመኮፈስ፤ አሊያም ትርጉም አልባ በሆኑ ዲስኩሮች ከንቱ ውዳሴን ለመሻት አይደለም። ‹‹ጥንታዊና ታላቅ ሀገር ባለቤቶች ነበርን፤ የሥልጣኔ ቁንጮና መሪዎችም ጭምር›› የሚል ሃሳብን የምናነሳበት ምክንያት ‹‹ለመሆኑ ምን ነክቶን ይሆን ከሥልጣኔ ፈር ቀዳጅነት ተንደርድረን የኋላ ቀርነት ማጥ ስንዳክር የከረምነው?›› የሚለውን መራር ጥያቄ አስከትለን ለችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ በፍፁም ቅንነት ከሚመነጭ ፍላጎት ለማመላከት ነው።

አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንራመድ የሚያደርገው የትናንት ማንነታችን ሉዓላዊነታችንን አለማስደፈራችን እና ዳር ድንበራችንን በጀግንነታችን ጠብቀን ማቆየታችን ብቻ አይደለም። ከትላንቱ እኛነታችን ውስጥ በእጅጉ የሚያኮሩን አያሌ ጠንካራ ጎኖች ነበሩን። ከእነዚህ መካከል ደግሞ በጊዜው በነበረው የሰው ልጅ ሥልጣኔ እና የእውቀት ልክ ለማሰብ የሚከብዱ ኪነ ሕንፃዎች እና የምህንድስና ጥበብ ሥራዎች በቀዳሚነት ይነሳል። ዛሬም እነዚህ ምስክሮ በዓለም ቅርስነት ተመዝግበው እንደሚገኙ ልብ ይላል።

ቀና ብለን በተጓዝንባቸው ቀደምት ዘመናት አብያተ ክርስቲያናትን፣ ቤተመንግሥቶችን እና ሌሎችም መሰል የግንባታ ውጤቶችን በውበት፣ በጥራት እና በንድፍ እንዲማርኩና የኢትዮጵያውያን ባሕል፣ ታሪክ እና ማንነትን እንዲያንፀባርቁ ተደርገው ይታነጹ ነበር። እነዚህ የሰው ልጅን የሥልጣኔ ልክ የሚገልጹ ውጤቶች በዘመኑ ለነበሩ አያት ቅድመ አያቶቻችን መኖሪያነት ከማገልገል አልፈው ለዛሬው ዘመን ታሪክና የምህንድስና እውቀትን የሚያጋቡ ናቸው።

የኢትዮጵያውያንን ከፍታ የሚያበስረው ይህ ጊዜ ግን ከዚህኛው ዘመን ጋር የተጣላ መስሎ ምዕተ ዓመታትን አሳልፈናል። የያኔው የምህንድስና፣ የሥነ ጽሑፍ እንዲሁም ሌሎች የኃያልነታችን መገለጫዎች ድር አድርቶባቸው አንገታችን አዘንብሎ ነበር። ከሥልጣኔ ተራርቀን፣ የኛ ለሆነው እውቀት፣ ጥበብና ብልሃት ባዳ ሆነን በቁጥር ለማይገለፁ በርካታ ዓመታት በድህነት ዳክረናል። የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ስንፍና፣ መሀይምነት፣ ሙስና እና ለመጭው ትውልድ የሚሻገር ወረት ያለማኖር አባዜ ተጠናውቶን ከራርመናል።

ከፍታ ላይ የሚገኘው ታሪካችን ለዓመታት ሲወቅሰንና ለህሊናችን አሳልፎ ሲሰጠን ከራርሟል። ወጣቶች ከዛሬ ሽሽት ይሁን ትናንትን ፈለጋ ለስደት ተዳርገው በባሕር ማዶ ስደትን መርጠዋል። የኖርንበት የዝቅታ ዘመን ክፍለ ዘመንን የተሻገረ ነው። ማህበራዊ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሹም ሚሊዮኖችን ከድህነት በታች አድርጎ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚም ፈቅ ሳይል፤ ጥቂት ሙሰኞች፣ ሕገወጦች የሀብት ማማ ላይ ያስቀመጠ ነበር።

ቀደም እንዳሉት የሥልጣኔ ዘመናት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ዳር ማድረስ ተስኖን፣ የምህንድስና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የንግድ ቀዳሚነታችን ከሽቅብ ወደ ቁልቁል ተንደርድሮ ነበር። ይህ እውነት ዳግም እስከነቃንበት እስከዚህችኛዋ ቅፅበት ድረስ የጨለማው ዘመናችን ሆኖ ተመዝገቧል።

ዛሬስ?

ዛሬ ከዚህ ቅዥት መሰል መዳከር እየተላቀቅን መሆኑን የሚያመላክቱ ተስፋዎች እያየን ነው። ትናንትን መልሶ ለማምጣት ሳይሆን ከትናንት ተምሮ ወደ ቀደመው ክብር ለመመለስ በሩ በጭላንጭሉም ቢሆን ተከፍቷል። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ባለፉት ጥቂት የሚባሉ ዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ውስጥ እየተመለከተ ያለው የመልማት ጥልቅ ፍላጎት ለዚህ ድምዳሜ አድርሶታል። ለጉዳዩ የሚረዳ ጥቂት ምሳሌዎችን ከዚህ እንደሚከተለው ለማቅረብ ይሞክራል።

በመግቢያው ላይ ለማመልከት እንደተሞከረው ኢትዮጵያውያን በቀደመው የሥልጣኔ ዘመናቸው በሕንፃ ምህንድስና የማይታሰቡ የሚመስሉ ድንቅ ድንቅ ሥራዎችን አበርክተውልን ማለፋቸው እሙን ነው። ይሁን እንጂ ዘለግ ላሉ ዓመታት ከዚህ እውቀት የተኳረፍን ይመስል ከተሞቻችን፤ ተቋሞቻችን፣ መንገዶቻችን የልማት ፕሮጀክቶች ጭምር የዲዛይን፣ የጥራት ብሎም የማራኪነት ጉድለት ይታይባቸው ነበር።

ግንባታዎችን ለማከናወን መሠረተ ድንጋይ ብንጥልም መሠረተ ልማቱ ግን እምጥ ይግባ ስምጥ አይታወቅም ነበር። የመሠረተ ድንጋዮቹ በዳዋ ተሸፍነው ከፖለቲካ ገበያነት የዘለለ ትርጉም አልነበራቸውም። የሚገነቡትም ከፍተኛ የጥራት ችግር ያለባቸው፤ ለትውልድ ለመሻገር ይቅርና ዘለግ ላለ ዓመታት የማያገለግሉ ነበሩ። ይህ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየታዩ ያሉ የምህንድስና ውጤቶች፣ የፕሮጀክት አፈፃፀምና የፖለቲካ ቁርጠኝነት በጭላንጭል የሚታየውን ተስፋ ይበልጥ የሚያጎሉ ናቸው። በአጭር ጊዜ፣ በጥራትና በፍፁም ቁርጠኝነት ከተማችንን፣ የመስህብ መዳረሻዎቻችንን፣ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ ተመልክተናል።

መንገዶች፣ ድልድዮች የቱሪዝም መዳረሻዎች እና ሌሎችም ተጀመሩ ባልንባቸው ወራትና ጥቂት ዓመታት ውስጥ ተገባደው አይተናል። ከዚህ ቀደም ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው እውን ቢሆንም ለመጠናቀቅ ረጅም ጊዜ የሚወስዱ በከባባድ ሙስናና የምህንድስና ጥራት ችግር የሚታሙ ነበሩ። ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ሀብት ለብከነት ከመዳረግ ባሻገር ኢኮኖሚ እድገቱ ዘገምተኛ እንዲሆን ጋሬጣ የሆነ ነበር።

የለውጥ ትግበራ ከተካሄደበት አምስትና ስድስት ዓመታት ወዲህ የቀደሙትን የሥልጣኔ ታሪኮቻችንን የሚያስታውሱ ድንቅ የምህንድስናና የፕሮጀክት አፈፃፀሞችን መመልከት ችለናል። በዚህ ፍጥነትና የሥራ ባሕል የምንቀጥል ከሆነ ዛሬም ድረስ ከሚጎትተን ኋላቀርነት መላቀቃችን አንዳች አያጠራጥርም። ዋናው ቁምነገር የሚሆነው ከተወጋነው ማደንዘዣ እየነቃን መሆናችን ነው።

ለምዕተ ዓመታት የጀመርነውን የማንጨርስ፣ ከእለት ጉርስ የማይሻገር ኢኮኖሚ ላይ የተንጠለጠልን፣ ለመጪው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም መሆን ያቃተን እንመስል ነበር። ዛሬ ይህንን ታሪካችንን ለመፋቅ ቆርጠን የተነሳን መሆናችንን በጥቂት ጊዜ ውስጥ የታዩ ለውጦች ምሳሌ ይሆናሉ። ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን የሚያሳድጉ (የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ የመስኖ እርሻ እና ሌሎችም የግብርና ፕሮጀክቶች) ግድቦችን እያጠናቀቅን ነው።

የምህንድስና ስኬትን ከሚያሳዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ባሻገር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ ለውጦችን፤ ትውልድን በጠንካራ መሠረት ላይ የሚያንፁ የትምህርት ሥርዓቶችን የኢትዮጵያን ገፅታ የሚያሻሽሉ የልማት እቅዶችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ተግባር አስገብተናል። ለስንፍና፣ ለሌብነት ለሕገ ወጥነት በር የሚከፍቱ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና የአሠራር ሥርዓቶች በቁርጠኝነት እየተሻሻሉ ከነበርንበት ጥልቅ እንቅልፍ እየቃን ለመሆናችን ምሳሌ እየሆኑ ነው። የነገውን ምቹ መንገድ ዛሬ ላይ መገንባታችን የሥልጣኔን ጭራ አጥብቀን ለመያዛችን ማስረጃ መሆን ይችላል።

ቀደም ባሉት ዘመናት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ብልሹ አሠራር ከአፍቅሮተ ንዋይ ያልዘለለ እኩይ ምኞት ተጠቂዎች እዚህም እዚያም ተንሰራፍተው ነበር። ተደራጅተው ሀገር የሚዘርፉ ፖለቲከኞች፣ ለተሰማሩበት ሙያ ክብርና ሙያዊ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሠራተኞች፣ ከራስ ጥቅም ያልዘለለ ፍላጎት ያላቸው ተቋራጮች፣ ደካማ የትምህርት ሥርዓት እንደ አሸን የሚፈልሱ ስደተኞች ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ያቆረቆዙና ያዳከሙ ነበሩ።

ዛሬ ይህንን ለመቀየር የሚተጉ ዜጎች ተነስተዋል። የሥራ ባሕል፣ ሥነ ምግባርና አገልጋይነት ባሕል እንዲሆን መንግሥት እየሠራ ነው። እውቀትን፣ ጉልበትንና ገንዘብን በማስተባበር የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገንም ተስፋ ብሩህ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች (የአዲስ አበባና ክልል ከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም የመዳረሻ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኢትዮጵያ ታምርት እና ሌሎችንም ልብ ይላል) እውን እየሆኑ ነው።

ለሁለንተናዊ እድገትና ሥልጣኔያችን መሠረት የሆነው የትምህርት ሥርዓትን ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሁ መልካም ውጤቶች እየታዩበት ነው። ግብርናው፣ ቱሪዝሙ፣ አምራች ዘርፉ፣ ቴክኖሎጂ፣ የተፈጥሮ ሀብትን የማልማትና የመጠበቅ ትግበራው የነገውን መዳረሻችንን ከወዲሁ እያመላከተ ነው።

የነብርን ጭራ አይዙ…

የቀደምት ሥልጣኔ አባቶቻችን ‹‹የነብር ጭራ አይዙ፤ ከያዙም አይለቁ›› የሚል ብሂል አላቸው። ምን ይሄ ብቻ ለያዝከውና ለቆምክበት አላማ አልሰንፍም ሲያስተምሩን ‹‹ብረትን እንደጋለ ነው መቀጥቀጥ›› የሚል ልበ የሚያደርስ ምክርም አላቸው። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም በቀጣይ መደምደሚያው ይህንን እውነታ የሚያጠናክር ምክረ ሃሳብ እንደሚከተለው በማቅረብ ሃሳቡን ይቋጫል።

ከጠልቅ የኋላ ቀርነት እና የድህነት ማደንዘዣ እየነቃን መሆናችን እሙን ነው። ታዲያ ‹‹እየነቃን ነው›› ነው እንጂ ‹‹ነቅተናል›› የሚል ድምዳሜ አለመኖሩን በወፍራሙ ልናሰምር ይገባል። ጀመርን እንጂ አልጨረስንም። ከትናንቱ ደካማ የሥራ ባሕል እና በድህነት ምቾት የመኖር አባዜ ለመላቀቅ ጉዞ ጀመርን እንጂ ከስኬት ጫፍ አልደረስንም።

አይደለም የቀጣዩን ትውልድ ፍላጎት የሚያሟላ የዛሬው ጉድለታችንን የሚሸፍን አቅም አልገነባንም። ነገር ግን ትክክለኛውን መንገድ ጀምረነዋል። ጀምሮ የመጨረስ፣ አድሶ የመሥራት፣ ወጥኖ የማሳካት እሳቤ እና እሴትን እያዳበረን ነው። ይህ ጅምር እንጂ ከዳር የደረሰ ህልም አይደለም።

ለዚህ ነው የአባቶቻችንን ‹‹ብረትን እንደ ጋለ ነው መቀጥቀጥ›› የሚል ብሂል በሀገራዊ የልማት ጅምሮቻችን ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብን። እፎይ ብለን በአንድ ልብ የምናርፈው ወደነበርንበት ታላቅነት፤ የሥልጣኔ መሪነት ስንመለሰ እንጂ አንድ ርምጃን ከተራመድን በኋላ መሆን የለበትም። ዛሬ ያሳካናቸውን ውጤቶች በብዙ እጥፍ ደጋግመን መተግበራችንንና ልናረጋግጥ ይገባል።

ሥልጣኔ፣ እድገትና ታላቅነት አንዴ ብቻ አሳክቶ እፎይ የሚሉበት ባለመሆኑ ዛሬም ነገም ሥራን፣ እውቀትን፣ የሙያ ከብርና ሥነ ምግባርን፣ ሀገር ወዳድነትን እና ጠንካራ ሠራተኝነትን መገለጫችን አድርገን ልንቀጥል ይገባል። ለዚህ የቀደሙት አባቶቻችን ‹‹የነብርን ጭራ አይዙ ከያዙም አይለቁም›› የሚል ከአንጀት የሚደርስ ምክር ስንቃችን ይሁን። ሰላም!!

ሰው መሆን

 አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You