የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ሁሌም የሁሉም አጀንዳ ነው። አካባቢው ያላነጋገረበት ጊዜ ስለ መኖሩ ማስረጃ እንደ ሌለ ሁሉ፤ ስለ አካባቢው ጉዳይ ችላ ያለ አካል ካለም ራሳቸው፤ የአካባቢው ሀገራት እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።
አካባቢው በማንኛውም ፀጋ ተፈጥሮ አብዝታ ያደለችው ፣ ግን ደግሞ ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ፀጋ በአግባቡ መጠቀም ካልቻሉ የዓለማችን አካባቢዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። እያላቸው የሌላቸው ከሆኑ ሀገራት ሁሉ ፊት መሪው ይኸው የቀንዱ አካባቢ እንጂ ሌላ ሊሆን አልቻለም።
አላዋቂነቱን ባለማወቅ አዋቂ መስሎ እርስ በእርሱ ላለመተዋወቅ የሚጥር ትንግርተኛ አካባቢ ካለ እሱ የቀንዱ አካባቢ እንጂ ሌላ ሆኖ አያውቅም። “ተፈጥሯዊ መነሻና ምክንያት ያለውን ‘ሰጥቶ መቀበል’ መርህ መቀበልም ሆነ መለማመድን የተጠየፈ ከባቢ ይኖር ይሆን?”
ለጥያቄው መልሱ ያለ ምንም ማወላወል “አዎ” ይሆንና፤ ማብራሪያውም፣ ዝቅ ብለን የምንመለከተው እንዳለ ሆኖ፣ “የአፍሪካ ቀንድ” የሚል ከመሆን አያመልጥም። ይህንን የሚጠራጠር ካለ እሱ አካባቢውን የማያውቅ ነውና ልናልፈው ግድ ይሆናል።ይህ ሁሉ ውርጅብኝ መሰል ሀቲት “ለምን?” የሚል ጥያቄን ካስነሳ ምክንያቱን እንደሚከተለው እናመላከታለን።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን ያካተተው፤ በበርካታ የጂኦ-ፖለቲካ ፍጥጫዎች የተሞላው ከፊል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የሚያካትተው የአፍሪካ ቀንድ በየጊዜው የሰላ አስተያየት ከሚሰጥባቸው ቀጣናዎች መካከል ቀዳሚው ነው።
አብዛኞቹ አስተያየቶች ደግሞ አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ገፅታም ሆነ አንድምታ የላቸውም። ሁሉም በሚባል ደረጃ አካባቢው በተለያዩ (በአብዛኛው) ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲታመስ የኖረና እየኖረም ያለ አፍሪካዊ ክፍል ነው።
በዚሁ ዓመት (ጥር 2024) “ፈንድ ፎር ፒስ” የተባለው ተቋም እንደገለጸው፤ በዓለማችን መረጋጋታቸው በቀላሉ ሊናጋባቸው ከሚችሉ ቀጣናዎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የአፍሪካ ቀንድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያልቁባቸውን ጦርነቶች የሚያስተናግድ ቀጣና ነው።
በዜጎች መብት ጥሰት ስማቸው በክፉ የሚነሱ ሀገራት መሪዎች መገኛ ከሆኑ አካባቢዎች መካከልም አንዱ የአፍሪካ ቀንድ ነው። አካባቢው ውጥረት የማያጣውና በሀገራት ውስጣዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሀገራቱ በራሳቸው መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት መሻከርም የሚታወቅ ነው።
በሚሊዮኖች የሚፈናቀሉበት ፣ በመቶ ሺዎች ህይወታቸው የሚቀጠፍበት ፣ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት የሚወድምበት ቀጣና ነው። ያሳዝናል።አካባቢው ተፈጥሮ ባደለችው ፀጋ ምክንያት ሌሎች አንድ ሆነው ሊቀራመቱት ሲመጡ እሱ ለራሱ አንድ መሆን ያቃተው አካባቢ ነው።
እራሱን ለተቀራማቾች እያመቻቸ ዓመታትን በቀውስና ግጭት ውስጥ እንደ ሰጠመ የሚገኝ ነው፤ አንድ ሆኖ እርስ በርሱ በመረዳዳት ሊያገኝ የሚችለውን የጋራ ጥቅም ለሌሎች “እነሆ በረከት” ማለትን የመረጠ ታሪከኛ አካባቢ ነው።
ሰሞኑን (ጥቅምት 30) ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው አቶ ዳኛው ገብሩ ተስፋው እንደነገሩንም ሆነ እኛም እንደምናስተውለው የቀንዱ ሀገራት አንድ የመሆን፤ አንድም ሆኖ በጋራ የመሥራትና የመጠቀም ችግር ይስተዋልባቸዋል።
ይህ ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ አሁን እየታየ ያለ እውነት ነው።ቀይ ባህርን ዋቢ አድርገው የአካባቢውን ሀገራት የሚወቅሱት አቶ ዳኛው እንደሚሉት፤ ቀይ ባሕር፤ 24 ሰዓት የማያንቀላፉ፣ 24 ሰዓት የሚያንቀላፉና ችግር ጠማቂዎች ያሉበት ቀጣና ነው። እንዲህ ሲባል አንደኛ 24 ሰዓት አፍጥጠው የሚከታተሉ ሀገሮች አሉ።
እንደሚስተዋለውም ሁሉም በሚያስብል ደረጃ ተረባርቦ በቀይ ባሕር አካባቢ ከጂቡቲ እስከ ሶማሊያ ድረስ ወደብና የጦር ሰፈር እየተከራየ የተቀመጠበት ሁኔታ አለ። [•••] አፍሪካንና የኢስያን ኢኮኖሚ ሊቀራመቱ፣ ሰፊ የሆነውን የሰው ጉልበት ሊበዘብዙና ገበያውን ሊጠቀሙ የሚችሉ ሀገሮች 24 ሰዓት አይናቸውን ከቀይ ባሕር ላይ አይነቅሉም፤ አያሸልቡምም።
ሁለተኛው ደግሞ 24 ሰዓት የሚተኙት ናቸው፣ እነዚህም የአካባቢው ሀገሮች ናቸው ማለት ይቻላል። ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ የመንም እንቅልፋሞች ናቸው። እነዚህ የአካባቢው ሀገራት እንቅልፋም ባይሆኑ ኖሮ፤ በተናጠል ጥቅማቸውን ማስከበር ባይችሉም፤ ሕብረት በመፍጠር ጥቅማቸውን ያስከብሩ ነበር።
አቶ ዳኛው የቀንዱን ሀገራት በሌላም ጉዳይ ይወቅሷቸዋል። የ”ሰጥቶ መቀበል” መርህን ያለመቀበላቸውን በማንሳት፤ ይህንንም ሀገራችን ሰጥቶ በመቀበል መርህና ፍትሐዊ በመሆን ጥቅም የምታምን ናት። ጎረቤቶቻችንም ሰጥቶ መቀበልን መለማመድ አለባቸው።
ጎረቤቶቻችን ከእኛ የሚያገኙት ብዙ ነገር አለ። በዚያው ልክ ልናሳጣቸውም የሚያስችለን በርካታ ነገር አለ። ለምሳሌ ሶማሊያን ብንወስድ ሕልውናዋ የተመሰረተው በኢትዮጵያ ወንዞች በዋቤ ሸበሌና በገናሌ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ገና በእነዚህ ወንዞች ላይ ያልተጠቀመች ናት።
የሶማሊያ ሕልውና በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ ሳለ፤ ሶማሊያዎች እኛን ባሕር ሊከለክሉን አይገባም። ሰጥቶ መቀበል ካቃታቸው እኛም ያለመስጠት መብታችን የተጠበቀ ነው ይላሉ። አንድ ሆኖ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት የጋራ ተጠቃሚ መሆን እየተቻለ፤ የቀንዱና የሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ከዚህ ውጪ ሆኖ ማፈንገጥን በተመለከተም ራስ ገዟ ሶማሌላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ሰጠች ተብሎ የዚያን ያህል ማለቃቀስ አያስፈልግም ባይ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ስለተዋዋለች የተለያዩ ጠላቶችን በዙሪያቸው እየጠሩ የሚያሰባስቡና ኅብረት የሚፈጥሩበት አካሄድ እራሳቸውን አንቀው እንደመግደል የሚቆጠር መሆኑን ሊረዱ እንደሚገባም አመልክተዋል። የዚህ ጽሑፍ አቢይ ጉዳይም ይኸው ነው ።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በጋራ ጉዳይ ላይ አንድ ሆነው ሊቀራመቷቸው የሚቋምጡትን ሁሉ በማሳፈር የጋራ ተጠቃሚ መሆን ሲችሉ፤ ጭራሽ በአካባቢው ጎላ ብላ የምትታየውን ኢትዮጵያ ከሰጥቶ መቀበል መርህ እንድታፈነግጥ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው የመታየታቸው ጉዳይ የማይጠቅማቸው መሆኑን ማሳየት ነው።
ዘፋኞቹ “ሁሉም ቢተባበር / የት ይደረስ ነበር” እንዳሉት፤ የቀንዱ ሀገራት ከተዘፈቁበት የእርስ በርስ ሽኩቻ በመውጣት አንድ ሆነው በአንድነት ለጋራ ተጠቃሚነት ቢሰሩ የት በደረሱ ነበር፤ በርግጥ አሁንም አልመሸም እውነታውን በቅን ልቦና ተረድተው፤ ለጋራ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት አብረው በመስራት የድህነት እና የኋላ ቀርነት ታሪካቸውን መለወጥ፤ የሕዝቦቻቸውን ብሩህ ነገዎችን መፍጠር ይችላሉ !?
መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም