የዛሬው የዘመን እንግዳችን ረዳት ፕሮፌሰር ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር) ይባላሉ:: የሚያስተምሩት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ነው:: ጥላሁን (ዶ/ር)፣ ያጠኑት የቅየሳ እና ካርታ ሥራ ምህንድስናን ነው:: እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የሰሩትም በዚሁ ዘርፍ ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳሉ የጂኦግራፊ እና ታሪክ መምህር በመሆን ያገለገሉ ናቸው::
በአሁኑ ወቅት የሚያስተምሩት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ሲቪል ኢንጂነሪግ አርክቴክቸር ጂኦማቲክስ ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ውስጥ ነው:: እንግዳችን ከባሕር በር ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥናቶችንም አካሂደዋል:: በቅርቡም “የግብጽና አጋሮቿ ጠላትነት እስከ መቼ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመው ለአንባቢያን አቅርበዋል:: አዲስ ዘመንም እኚህን አንጋፋ ምሁር የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ አቅርቦላችኋል::
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለይዞታነት የሚገለጸው እንዴት ነው?
ጥላሁን (ዶ/ር)፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት እኛ ብቻ ሳንሆን ምዕራባውያንም ምሥራቃውያንም ብሎም ዓለም በሙሉ የሚያውቀው ነው:: ችግሮች እየተከሰቱ የመጡት አውሮፓ በበርሊን ስምምነት መሠረት አፍሪካን የመቀራመት አጀንዳ ከጸነሱ በኋላ ነው:: የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ የሆነ ከመሆኑም በላይ ቀደም ሲል ከባሕር በር ባለፈ ኢትዮጵያ የውቅያኖስም ባለይዞታነቷ የሚታወቅ መሆኑ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ::
ቀደም ባሉ ጊዜያት በኢትዮጵያ ዙሪያ በጣም ብዙ ቅኝ ገዥዎች ነበሩ፤ ይሁንና አንዳቸውም ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው የራሳቸው ርስት ማድረግ አልቻሉም:: ብዙ የአውሮፓ ሀገራት በአፍሪካ ብዙ ሀገሮችን በቅኝ የገዙ ቢሆንም ኢትዮጵያን ግን ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም:: ለምሳሌ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆኑትን ሀገራት ብናይ ግማሹ የተገዛው በጣሊያን ሲሆን፣ ግማሹ ደግሞ በእንግሊዝ፣ ገሚሱም በፈረንሳይ ነው::
ስለዚህ እነዚህ ቅኝ ገዥ ኃይሎች ወደጎረቤት ሀገራት ከመጡ በኋላ አንድ የቀድሞ የአፋር ሱልጣን፣ ለአንድ ዓሳ አሳጋሪ ጣሊያናዊ አሰብ አካባቢ ያለውን 18 ሺ አካባቢ በሚገመት ብር ከሸጡላቸው በኋላ ጣሊያኖች በዚያች አድርገው ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ቀስ በቀስ መጠጋት ቻሉ:: ዓሳ አሳጋሪው በመጨረሻ ሮባቲኖ ለሚባል ድርጅት ሰጠ:: ከዚያም ደግሞ ድርጅቱ ለጣሊያን መንግሥት ሰጠ:: በዚህ ሁኔታ የጣሊያን መንግሥት ልክ አጼ ምኒልክ እንዳሉት እንደፍልፈል ግዛት እየቆረሰ ሙሉ ኤርትራን የተቆጣጠረበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ:: ከዚያ በኋላ ከጂቡቲ ድንበር አካባቢ አሰብ ከሚገኝበት ጀምሮ እስከ ላይ ራስ ቄሳር እስከሚባለው ድረስ በጣሊያን እጅ በአጋጣሚ የወደቀ እንጂ በጦርነት ከኢትዮጵያ የወሰዱት አልነበረም:: የኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠልን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ላይ የውጭ አካል እጁን ያስገባ መሆኑ የሚታወስ ነው::
ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት በዓለም የመጨረሻ ትልቋ ሀገር ናት:: ትልቅ ሕዝብ ይዛ ወደባሕር መውጫ በር የተነፈገች ሀገር መሆን ችላለች:: ከዚያ በፊት ግን ሌላው ቀርቶ ከአፍሪካ በስተ ምዕራብ ያለው አትላንቲክ ውቅያኖስ ራሱ የጥንታዊ ግሪካውያን አሳሾች “ኢቲዮፒክ ኦሽን” የኢትዮጵያ ውቅያኖስ ብለው ካርታ የሰሩለት መሆኑን ድርሳናት ያመለክታሉ::
ኢትዮጵያ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን ሕንድ ውቅያኖስን ተሻግራ የዛሬ የመንና ኦማን መሰል ሀገሮችን ከቀይ ባሕር አልፋ አስተዳድራ ታውቃለች:: ሕንድ ውቅያኖስ ጭምር የራሷ እንደነበር ታሪክ ያሳውቃል::
ኤርትራ ነፃ በምትወጣበት ሰዓት የባሕር በር ጥያቄ በትክክል መነሳት የነበረበት ነው:: ነገር ግን በጣም የሚያሳዝነው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፈጸሙት ስህተት ዛሬ የባሕር በር እንድናጣ አድርጎናል:: በዚያን ሰዓት የትኛውም የዓለም ሀገር ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት ሀገር ትሁን የሚል አቋም አልነበረውም:: ሕወሓት ከሻዕቢያ ጋር ስለማይስማማ ብቻ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተነጥላ እንድትሰቃይ ከመፈለግ የመጣ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ:: ይህ ውሳኔያቸው ግን ለኢትዮጵያውያንም ለኤርትራውያንም የሚጠቅም አልነበረም:: ምክንያቱም የሁለቱ ሀገራት ሕዝብ ተለያይቶ ሊለያይ የማይችል ሕዝብ ነው:: ወደፊትም አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ስለ ባሕር በር አስፈላጊነት ላይ ሕዝቡ መምከር አለበት ስትል ወደመድረክ ካመጣች አንድ ዓመት አስቆጥራለች፤ ከዚህም አለፍ ሲል ደግሞ የባሕር በር ማግኘት የሚያስችል ስምምነት ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር ከተፈራረመችም እንዲሁ ዓመት ሊሞላው ነውና የባሕር በር ለማግኘት መደረግ ያለበት ምንድን ነው ይላሉ?
ጥላሁን (ዶ/ር)፡– የባሕር በር ለማግኘት ዋናው ቁም ነገር የመንግሥትና የሕዝብ መተባበር ነው:: ከምንም በላይ በአሁኑ ወቅት አንድነት ያስፈልገናል:: በምንም ተዓምር የባሕር በር ሳይኖረን መዝለቅ የምንችል ሀገር አይደለንም:: ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትልቅ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት፤ እንዲያውም የሕዝቧ ቁጥር በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ 150 ሚሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል እየተተነበየ ይገኛል:: ይህ ቁጥር ማለት ደግሞ ከራሽያ ሕዝብ ቁጥር እኩል እንደሚሆን ነው:: ስለዚህ የብዙ ሕዝብ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ ከባሕር በር አርቆ ማኖር አይቻልም::
አንደኛ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የግብርና ውጤት በመሆኑ የባሕር በር ማግኘት የግድ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከምትልከው ምርት ውጭ፤ ገቢ ምርቶቿ የሚበልጡ ናቸው:: ስለሆነም ይህን ሁሉ ምርት በአውሮፕላን አጓጉዘን የምንዘልቅ ባለመሆኑ የባሕር በር ማግኘት የግድ ነው:: ስለሆነም የባሕር በር አስፈላጊነቱ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጥር አይኖረውም:: ተወደደም ተጠላም፤ ፈጠነም ዘገየም የባሕር በር ለኢትዮጵያ የግድ ነው::
ስለዚህ የባሕር በር ለመያዝ መንግሥት ኅብረተሰቡን ከጎኑ ማሰለፍ መቻል አለበት:: እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግራም ነፈሰ በቀኝ የባሕር በር ለማግኘት ቆርጦ መነሳት መቻል አለበት:: በዚህ ሰዓት የመንግሥት ሚና መሆን ያለበት ሕዝብ ከመንግሥት ጋር እንዳይለያይ የውስጥ ሰላምን አስፍኖ እያንዳንዱን ዜጋ ከመንግሥት ጎን በማሰለፍ ረገድ ሰፊ ሥራ መሥራት ነው:: እንዲህ ከሆነ በግድም ሆነ በውድ የባሕር በር የማናገኝበት ምክንያት አይኖርም::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ያስፈልገኛል በሚል መንቀሳቀስ የጀመረች ቢሆንም፤ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ጠላቶች ጉዳዩን ለማሰናከል ጥረት እያደረጉ ነው ፤ ይህንን እኩይ ተግባር እንዴት መጋፈጥ ይቻላል?
ጥላሁን (ዶ/ር)፡– መጋፈጥ ይቻላል:: እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማወቅ ያለበት ኢትዮጵያን ሊያሰጋት የሚችለው የራሷ የውስጥ ችግር ብቻ መሆኑን ነው:: የትኛውም የዓለም ኃይል ኢትዮጵያን የባሕር በር ከማግኘት አያግዳትም፤ ሊኖርም አይችልም። ኢትዮጵያውያንም ይህን አሳምረው ያውቃሉ፡፡ እኛ የቀይ ባሕር ባለይዞታዎች ነን፡፡ በቀይ ባህር ላይ የባህር በር የማግኘት መብታችንን የሚከለክለን የለም፡፡
እኛን ብዙ ጊዜ ጠልፎን እየጣለ ያለው የውስጥ ችግሮቻችን ናቸው:: በተለይም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የገባው የዘር ፖለቲካ ቋንቋን፣ ዘርን፣ ጎሳን፣ ክልልን መሰል ነገሮችን ተገን በማድረግ የሚንቀሳቀስ ነው:: የሚያስፈራው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከፋፈል ጉዳይ ብቻ ነው:: ይህን ሕዝብ አንድ ማድረግ ከተቻለ ገፍቶ ሊጥለው የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል አይኖርም::
ነገር ግን ለምንድን ነው የሚገፉን የሚለውን ስንፈተሽ በሀብቶቻችን መጠቀም እንዳንችል ነው:: ገንዘባችን በወደብ ግዥ እንዲባክን ለማድረግ ነው:: ምክንያቱም ዛሬም ለወደብ እየከፈልን ነው:: ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ክፍያ እንድትከፍል የተደረገችው ‹‹የራሷ ልጆች ›› የነበራትን የባሕር በር ስላሳጧት ነው:: እንዲያም ሆኖ የባሕር በር አጥተን መቀጠል አንችልም::
ግብጽና የግብጽ አጋሮች አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገሮች እና ከጀርባ ያሉ አንዳንድ የአረብ ሀገራት ጭምር ወደ ባሕር በር እንዳንመጣ የመግፋት አዝማሚያ ያሳዩናል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ሴራቸውን ተገንዝቦ አንድ እስከሆንን ድረስ ምንም የባሕር በር ሊያሳጣን አይችልም:: ምናልባትም ኢትዮጵያን የባሕር በር እናሳጣታለን የሚሉ አካላት እንዲሁ ሲጮኹ ሊኖሩ ይችላሉ እንጂ ኢትዮጵያ ታላቅ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ይዛ የባሕር በር የምታጣበት ምክንያት አይኖርም::
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት ዋናው የውስጥ ሰላም ነው፤ ነገር ግን የባህር በር ጥያቄውም ምላሽ እንዳያገኝና እንዳይሳካ በግብጽና መሰሎቿ የሚመራው የተልዕኮ ጦርነት አለ፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያውያን ሚና ምን መሆን አለበት?
ጥላሁን (ዶ/ር)፡- መንግሥት የራሱ ሚና አለው:: ለምሳሌ ግብጽ ወደሱማሊያ ለመምጣት መጀመሪያ በሱዳን በኩል የሕዳሴ ግድቡን ለማፍረስ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ሲሆን፣ ጦርነትም ስትለማመድ ነበር:: በዚያው በሕዳሴ ግድባችን በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ላይ ከሱዳን ጋር በተዋጊ ጄቶች ጭምር ልምምድ ስታካሂድ ነበር:: እሱ ሁኔታ ምን እንደሆነ በውል ባይታወቅም ሱዳንን ችግር ውስጥ እንድትሆን አድርጓታል::
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር የገባነውን የባሕር በር መውጫ የውል ስምምነት ተገን አድርጋ ግብጽ ወደሱማሊያ ስትመጣ ለተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤ በመጻፍ ነው:: ‘ኢትዮጵያ እኔ ሳልስማማ ከእኔ እውቅና ውጭ ለአምስተኛ ጊዜ ውሃ የሞላች ስለሆነ የፈለኩትን ርምጃ ልወስድ እችላለሁ’ የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ነው::
እኔ በወቅቱ እከታተል ስለነበር ኢትዮጵያ ማድረግ የምትችለው ምንድን ነው? ግብጽ በርቀት ላይ በመሆኗ ኢትዮጵያን መውጋት አልቻለችም:: ምክንያቱም ያለው ርቀት አይፈቅድላትም:: ልትመታ የምትችለው አውሮፕላን ነው:: እሱ ደግሞ ፈታኝ ነው:: ስለዚህ ግብጽ የግድ ድንበር ትፈልግ ነበር፤ ሱዳንን ይዛ ድንበር ስትፈልግ ሱዳን ውስጥ ክፍፍል በመፈጠሩ ጦርነት ተነሳ:: ስለዚህ የእኛን የባሕር በር ጥያቄ ተንተርሳ ዞራ በሶማሊያን በኩል ብቅ አለች::
እኔ በወቅቱ የነበረኝ አቋም የትኛውም የግብጽ አውሮፕላን ጥርት ባለ መረጃ ላይ ተመርኩዘን ሞቃዲሾ እንዳያርፍ ማድረግ ነው የሚል ነበር:: ምክንያቱም ግብጽ ሱማሊያ ገብታ የሱማሊያን አካባቢ ልክ እንደ እኛ መውጫውንና መግቢያውን ካወቀች የሚታየኝ ሁለት አደጋ ነው:: አንዱ የተቆጣውን የሱማሊያን ሠራዊት ይዛ ልትወጋን ትችላለች:: ለዚህ ግን የምሰጠው ዝቅተኛ ግምት ነው:: ትልቅ ግምት የምሰጠውና ራስ ምታትም የሆነብኝ ነገር ግን ሌላ የአልሽባብና የአልቃይዳ፣ የአልታሃድ ዓይነት አደራጅታብን በዚያ ሁሉ ረጅም ድንበር እድሜ ልክ እንድናለቅስ አድርጋብን የምትወጣ መሆኗ ነው:: ስለዚህ በእኔ በኩል በዚያን ሰዓት ሱማሊያ እስክትረጋጋ ድረስ መጠበቅ አልነበረብንም:: በርግጥ በዲፕሎማሲ እንጨርሰዋለን የሚል ነገር ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን በጣም አስቸጋሪ ነው:: ኤርትራን አስገንጥለዋል::
አሁንም በዚያ በኩል ግብጽ ጽንፈኞችን ልታደራጅ ትችላለች:: ስለዚህ ሱማሊያ ውስጥ እንድትገባ በባሕርም ሆነ በአየር፤ መሳሪያ እንድታጓጉዝ ኢትዮጵያ መፍቀድ አልነበረባትም:: እዚያው ድንበር አካባቢ አስፈላጊውን ርምጃ መውሰድ ነበረባት:: ምክንያቱም ወደ ድንበር አካባቢ የመጣችው ለተባበሩት መንግሥታት ጽፋ ነው:: ልክ እርሷ ከአሁን በኋላ የፈለግኩትን ርምጃ ነው የምወስደው እንዳለች፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ራሴን ለመከላከል ስል ርምጃ ወስጃለሁ:: ብትል ዓለም ለአፍታ ያህል ይንጫጫል እንጂ የሚያመጣው ምንም ነገር አይኖርም::
ኢትዮጵያ ለግብጽ ጥፋት ጥሩ ምስክር የሚሆናት ከመምጣቷ በፊት ወደ ድንበሩ እንደምትሔድ ለተባበሩት መንግሥታት ጽፋ ያስገባችው ሰነድ ነው:: ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ላይ የፈልግኩትን ርምጃ ወስጃለሁ ብላ ሱማሊያ ድረስ መጥታ እና ተረጋግታ እንድትቆይ፣ የኢትዮጵያን ሠራዊት መውጫ መግቢያውን እንድታውቅ፣ የኢትዮጵያን ድንበር እንድታጠና መፈቀዱ ትክክል አልነበረም::
ስለዚህ የኢትዮጵያ ሚና መሆን ያለበት አሁንም እንድትደራጅ አለመጠበቅ ነው:: እያንዳንዱ እንቅስቃሴዋን በጥብቅ መከታተል አስፈላጊ ነው:: መምታት ካስፈለገም ራሷን ሳታደራጅ መምታት ነው:: ራስን መከላከል የሚባል የዓለም ሕግ አለ:: በዚህ መርህ መሠረት ችግር እንዳትፈጠር ማድረግ ወሳኝ ነው:: ከተረጋጋችና አካባቢውን ሀገሯ ካደረገች በኋላ ርምጃ ለመወስድ መሞከሩ አደገኛ ነው::
ሠራዊት የሚሰለጥነውና ራሱን በተለያየ ቴክኖሎጂ የሚያዘምነው በእንዲህ ዓይነት አደጋ ወቅት ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ታስቦም ጭምር ነው:: ደግሞም ጦርነት የሚጀመረው ለራስ ምቹ በሆነ ሰዓት እንጂ ለጠላት ምቹ በሆነ ሰዓት አይደለም:: ከዚህ የተነሳ ጊዜው ሲሰላ ለኢትዮጵያ የሚመቸው ሰዓት እያለፈ ነው ባይ ነኝ:: ምክንያቱም ግብጽ ለተባበሩት መንግሥታት የጻፈችውን ደብዳቤ በመጥቀስ ‘ግብጽ ሱማሊያን የጦር ሜዳ ልታደርግ ነው፤ እኔም ሥጋት አለብኝ፤ ልትወጋኝ ነው’ በማለት የመልስ ምት ለተባበሩት መንግሥታት መስጠት ተገቢ ነው::
ይህ በአንድ በኩል የሱማሊያን ሕዝብ ለማንቃት የሚጠቅም ነው:: ምክንያቱም ግብጽ ወደ አካባቢው የመስፈሯ ነገር ለሱማሊያ ሕዝብ አስባ ሳይሆን የሕዳሴ ግድብን ተቃውሞ በቅርብ ርቀት ለመግለጽ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የጦርነት ሜዳ እንዲሆን የመረጠችው የሱማሊያን ምድር ነው:: ምክንያቱም ተዋጊዎቹ ግብጽና ኢትዮጵያ ናቸውና:: ስለሆነም የሱማሊያ ሕዝብ ይህን ቢያውቅ ጥሩ ነው:: ኢትዮጵያ ደግሞ ለዚህ መስዋዕትነት መክፈል አለባት:: ግብጽ መቼም ቢሆን ለሱማሊያ አንዳች ጥቅም ማምጣት አትችልም:: ይህን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን ፈተና ለመቀልበስ ለአንዴና ለመጨረሻ ከመንግሥት ጎን መቆም አለበት::
የባሕር በር ጥያቄውንም ቢሆን አንዴ ገብተንበታል:: መግባት የነበረብን በአሰብ በኩል ነበር ወይስ በሱማሊላንድ የሚለው ሌላ ራሱን የቻለ ጥያቄ ሆኖ ሳለ ማለት ነው:: ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለአሸናፊነት መሰለፍ ይጠበቅበታል::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከተፈራረመችበት ጊዜ ጀምሮ ጎረቤት ሀገር ሱማሊያ ጉዳዩን በበጎ መመልከት አልፈለገችም:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ለሱማሊያ ደህንነት ስትከፍል የቆየችው መስዋዕትነት መገለጽ የነበረበት በዚህ መልኩ ነበር?
ጥላሁን (ዶ/ር)፡- እርግጥ ነው በሱማሊያ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግዛቶች እስካሁኗም ጊዜ ድረስ ግብጽ ወደምድራቸው የመምጣቷን ነገር እየተቃወሙ ናቸው:: ነገር ግን በኢትዮጵያውን ባሕል ውለታ የሚባለው ጉዳይ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው:: በተለይም የደም መስዋዕትነት ብሎም የሕይወት መስዋዕትነት የተገበረለት ውለታ ሲሆን ደግሞ ዋጋው ላቅ ያለ ነው፡ የሱማሊያ መንግሥት በውስጡ ባለው ኃይል ምክንያት ከመንግሥትነት ተራ ወጥቶ የዱርዬዎች መጫወቻ ሆኖ እንደነበር የሚታወስ ነው:: ኢትዮጵያ የሱማሊያ መንግሥት እንዲመሠረትና በእግሩ እንዲቆም አድርጋለች፤ ይህን ስታደርግ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ሕይወት ገብራ መሆኗ የማይካድ ሐቅ ነው:: ሱማሊያ፤ ሱማሊያ እንድትሆን ኢትዮጵያ የከፈለችው የወታደሮቿን የሕይወት መስዋዕትነት ነው:: ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገር ሱማሊያ መረጋጋት ደሟን ገብራለች፤ አጥንቷንም ክስክሳለች:: ለሱማሊያ የተሰዋው የደም መስዋዕት ሱማሊያን ሀገር እንድትሆንና ዛሬ ላይ እንድትደርስ አድርጓታል::
ነገር ግን ሱማሊያ ኢትዮጵያ ስለምን የባሕር በር ታገኛለች በሚል ያልተገባ ድርጊት እየፈጸመች ነው:: ይህ ደግሞ ከአንድ ሀገር መንግሥት ቀርቶ ከየትኛውም ግለሰብ የሚጠበቅ የውለታ አመላለስ ስልት አይደለም:: ኢትዮጵያ የከፈለችውን መስዋዕት ዓለም የሚያውቀው ነው:: ከምንም በላይ ደግሞ እነርሱ አሳምረው ያውቁታል:: መንግሥታቸው መንግሥት መሆን ባልቻለበት ጊዜ ከአንድም ሁለት ሶስቴ መንግሥት መስርተን አቋቁመናቸዋል::
ዛሬ ግን ሱማሊያውያን ኢትዮጵያ ከሀገራችን ትውጣልን ለማለት መብቃታቸው የሚገርም ነው:: ይህን ለማለት አቅም የፈጠርንላቸውና ያደራጀናቸው እኛ ነበርን፤ ነንም:: በኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት አንገቷን ቀና ያደረገች ሱማሊያ፣ ለኢትዮጵያ ምላሿ መሆን ያለበት ይህ አልነበረም::
የሱማሊያ መረጋጋት የኢትዮጵያም ጭምር ነው በሚል ኢትዮጵያ የሚቻላትን ስታደርግ ቆይታለች:: ርግጥ ነው ሱማሊያውያንን የመደገፋችን ምስጢር ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም ጭምር በማሰብ እንደሆነ የሚታወቅ ነው:: አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ከግብጽ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ጠላት ሱማሊያ መሆኗ ነው::
ሱማሊያውያን ከዚህ ቀደምም ታላቋን ሱማሊያን እንመሠርታለን በሚል እስከ አዋሽ ድንበራችን ነው ሲሉ ያልሙ የነበሩ ናቸው:: እነርሱ ጂቡቲም ኬንያም ውስጥ ግዛት አለን የሚሉ ናቸው:: በዚህች አቅማቸው መንግሥት መመስረት ባልቻሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን ይህን ሕልም የሚሉትን ቅዠት መርሳት የሚይፈልጉ ናቸው:: አሁንም እየቆረቆራቸው ያለውና እያቃዣቸው የሚገኘው የራስ ገዟ ሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችው ስምምነት ብቻ ሳይሆን ዋናው ሕልማቸው የቀደመው መንግሥታቸው ሲያድባሬ ታላቋ ሱማሊያን እንመሠርታለን የሚለውን ቅዠት እውን እናደርግ በሚል ነው::
ስለዚህ ሱማሊያውያን እኛ ኢትዮጵያውያን ሞተንላቸው ማንነታቸውን ማየት ችለናል:: እነርሱ አንዳች መልካም ነገር ሲያደርጉ አላየንም:: ለኤርትራ መገንጠል እንኳ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው:: ነገር ግን ለሱማሌላንድ መገንጠል፣ ለፑንትላንድ መገንጠል እኛም አስተዋጽኦ ማድረግ ነው:: የተለያዩ መንግሥታት ሆነው አካባቢያቸውን ሲጠብቁ አልሸባብ ከኢትዮጵያ እጁን ያነሳል:: ለሱማሊያውያን የምንከፍለው መስዋዕትነት ከአሁን በኋላ እምብዛም አይታየኝም:: በመሆኑም ኢትዮጵያም የራሷን አቅጣጫ መከተል ይኖርባታል:: ከሱማሊያውያን ጀርባ የአረብ ሊግ አለ፤ ምክንያቱም ሱማሊያ ራሷ የሊጉ አባል ሀገር ናት:: ስለዚህ እኛ ያለን አማራጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መቆም ብቻ ነው:: እኛ እየተንቀሳቀስን ያለነው እውነቱን ይዘን ነው::
እነርሱ መገንዘብ ቢችሉ የሕዳሴ ግድብ የያዘው ውሃ የጋራችን ነው:: የሕዳሴ ግድብ ውሃ በእኛ ድንበር ውስጥ ተጠራቀመ እንጂ፣ አርሰን መብላት የምንችልበትን የእርሻ መሬታችንን ያዘ እንጂ ሌላው ላይ ጉዳት አላመጣም:: ውሃው የግብጽና የሱዳን ነው:: ውሃው ለእኛ ተርባይኑን አንቀሳቅሶልን የኤሌክትሪክ ኃይል ካመነጨ በኋላ የሚሔደው ወደ እነርሱ ነው::
እኔ በሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ በሚካሄዱ ክርክሮች ውስጥ ከአንድም ሰው ሰምቼ የማላውቀው ነገር ቢኖር “ይህ ውሃ እኛ መሬት ላይ ተጠራቀመ እንጂ የግብጽና የሱዳን ነው” የሚለውን ሃሳብ ነው:: መጠኑን የጠበቀ ንጹህ ውሃ ወደ እነርሱ በመሄዱ መባል ያለበት እንዲያውም ሊከፍሉን ይገባል ነው:: ያወጣነውን ወጪ ግብጽና ሱዳን ሊጋሩን ይገባል ባይ ነኝ:: እኛ ኢትዮጵያውያን በአንዴ ሄዶ ዜሮ የሚያደርግላቸውን ውሃ ዋጋ ከፍለን ተቆጣጥረንላቸው የተመጠነ ውሃ እንዲሄድ ነው ያደረግንላቸው:: ምክንያቱም በጎርፍ እየተጥለቀለቁ ከሚደርሳባቸው ፈተና አስቁመን ዓመቱን ሙሉ የተስተካከለ ውሃ እንዲፈስላቸው አደረግን::
ስለዚህ እኛ ላደረግነው በጎነት መክፈል አለባቸው:: ይህን የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን በአግባቡ ሊያስረዱና ሊናገሩ ይገባል:: የግድቡ ውሃ የያዘብን ሰፊ መሬት ነው:: ለውሃው ዓመቱን ሙሉ ተስተካክሎ መፍሰስ ብቻ ሳይሆን አርሰን ልንበላ የተገባውን ሰፊ ይዞታ ስለያዘብን ጭምር መክፈል የሚጠብቅባቸው መሆኑን ማስገንዘብ መልካም ነው:: እኛ ከተጠራቀመው ውሃ የምናመነጨው አንድ የኤሌክትሪክ ኃይልን ነው፤ እነርሱ ግን ሥርዓቱን ጠብቆ በሚሄድላቸው ውሃ የሚሰሩት ሁሉን ነገር ነው:: ምን ምን ከተባለ መስኖ ይሰሩበታል፣ ለቱሪዝም ይጠቀሙበታል፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጩበታል፤ ከዚያ ባለፈ ያንን የሚሄድላቸው ተፈጥሯዊ የሆነ ንጹህ ውሃ ለሌሎች ሀገራት አሽገው እስከ መሸጥ የሚደርሱ ናቸው:: ምክንያቱም ውሃው እንደ ውቅያኖስ ውሃ አይደለም::
ከዚህ በኋላ እኛ የምንልክላቸው ዓይነት ንጹህ ውሃ ወደፊት ከነዳጅ በላይ የሚወደድ መሆኑ የማያጠራጥር ነው:: ስለዚህ በዚህ ልክ አላስረዳናቸውም ብዬ አስባለሁ፤ እነርሱም ትክክለኛውን ምላሽ እያገኙ አይደለም:: ለዘብተኛ የሆነ አቋም እንዳንይዝ ልንጠነቀቅ ይገባል:: እንዲያ ከሆነ የሚጠቀሙበት እነርሱ ይሆናል:: ስለዚህ እንዲያውም ከዚህ በኋላ ሊያጋጥሙን በሚችሉ ክሶችም ሆኑ ችግሮች ቀድመን አቤቱታ ማስገባት ሁሉ ይኖርብናል::
ሌላኛው ደግሞ በውሃ ጉዳይ ያለብን መነታረክ አይደለም:: ብዙ ወንዞቻችንን ለዓባይ ወንዝ የሚገብሩ ናቸው፤ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ጀርባ ወደ እንጦጦ አካባቢ የሚገኘው ሙገር ወንዝ እንዲሁም ወልዲያ አካባቢ የሚገኘው በሽሎ ወንዝ የሚገብሩት ዓባይን ነው:: እነዚህን መሰል ወንዞች ዓባይን የሚገብሩ መሆናቸውን ብዙዎች አያውቁም:: ከዚህ ጎን ለጎን ዝናባችንም ወንዛችንም የሚሄደው ወደ እነርሱ ነው:: ስለዚህ እነርሱም መጥተው ዶላራቸውን ኢንቨስት በማድረግ ተፋሰሱን ማልማት፣ ችግኞችን መትከል ይጠበቅባቸዋል:: ያኔ የዝናብ መጠኑም ይጨምራል፤ የውሃ ምንጩም ይጎለብታል፤ እንደዚያ ሲሆን ደግሞ የውሃ መጠኑ ከፍ ይላል:: ይህን በአግባቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ማስረዳት ይጠበቃል::
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ የኢትዮጵያና የሱማሊያ ግንኙነት ምን አቅጣጫ መከተል አለበት?
ጥላሁን (ዶ/ር)፡- ስለግንኙነት ከመጥቀሴ በፊት ሱማሊያ ራሷ ሱማሊያ ሆና ትዘልቃለች ወይ የሚለው የመጀመሪያው ጥያቄዬ ነው:: ምክንያቱም ሱማሊያ የራሷ ችግር እያየለባት ነው:: ነገር ግን የጎረቤት ችግር እኛንም ሊያጋጥም የሚችል ፈተና ነው:: መቶ በመቶ ችግሯን እራሷ መውጣት አለባት ብለን ብንተውም የችግሯ ወላፈን እኛም ዘንድ መድረሱ አይቀርምና ለእርሷ ስንል ሳይሆን ለራሳችን ብለን ማድረግ የተገባን ማድረግ አለብን ባይ ነኝ::
በርግጥ በሱማሊያ ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲወጣ መወሰኑ ተስምቷል:: ነገር ግን ይህን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መቀበል አለብን ብዬ አላስብም:: መንግሥት ውሳኔውን የሚቀበል ከሆነ ደግሞ ድንበሩን በደንብ አጠናክሮ መያዝና የግብጽን አመቺ ያልሆነ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እግር በእግር በመከታተል አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት መጀመር አለበት:: ግብጽ ተረጋግታ ከኢትዮጵያ ድንበር ተጋርታ እስክትደላደል መጠበቅ የለብንም:: ከዚህ ጎን ለጎን ያለብንን የውስጥ ችግር መንግሥት መፍታት በሚያስችለው ላይ መሥራት አለበት:: ከዚያም ትኩረቶቻችንን ወደ ድንበሮቻችን ማድረግ ይኖርብናል:: ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ተረጋግተን መሥራት ይጠበቅብናል፤ ገና ብዙ ግድቦችን በወንዞቻችን ላይ መሥራት ይኖርብናል:: ስለዚህም የውስጥ ችግሮቻችንን አስወግደን ትኩረታችንን ወደልማት ማዞር አለብን::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::
ጥላሁን (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም