ታላቋ ኢትዮጵያ በትልቁ ሀምራዊ የጥበብ ዘርፏ ሥልጣኔ የተነቀሰበት የታላቅነት ዘመን እንደነበራት ለሁላችንም እሙን ነው። ላላመንን ምልክት ይሆን ዘንድ ደግሞ ርዝራዥም ይሁን በገፍ ዛሬም ድረስ በዓይኖቻችን የምንመለከታቸው ማሳያዎች እንዳሉን ማናችንም አንክደውም።
ከሞት ባህር ዳርቻ የቆመው የግእዝ ቋንቋም ሁሉን ሊነግረን የሚጠብቀው እኛኑ ነው። ይሁን እንጂ እሱ ያውቀናል እንጂ እኛ ስለማናውቀው ግድ አልሰጠንም። እነዚህን እውነታዎች ጥቁር ደም ያለው ሀበሻው ቢክድ እንኳን ነጩ ፈረንጅ በአሥር ጣቶቹ ይፈርምበታል። ዓለም በሙሉ በእግር ጣቱ ቆሞ ይሄንን ሀቅ ፍለጋ ላይ መሆኑንም አይስተውም። ዓይኖቹ በግእዝ ቋንቋ ላይ ናቸው። ምክንያቱም የታላቁ ሚስጢር ቁልፍ በግእዝ ፊደላት ተቀርጾ ብራናዎች ላይ ሰፍረዋልና፡፡
ብራናዎቹን ታቅፈናል። ለኛ የረከሰው ወርቅ ደግሞ ለእነርሱ የእስትንፋስ ያህል ነው። “በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ…” ብንል እንኳን ፈጽሞ አይገልጸንም። አሳዛኙ ነገር የኛ መጣል ብቻ አይደለም። እኛ ጋቢ በርዶን የነጮችን ነጠላ ፍለጋ በምንማስንበት ዘመን እነርሱ ደግሞ ወደኛ እየፈጠኑ፣ እየገሰገሱ መሆኑ እንጂ።
ታዲያ እኮ እኛን ፍለጋ አይደለም። የእኛን ፍለጋ ነው። የኛ የምንለው ግእዝ ሳይገባን እነሱ አሳምሮ ገብቷቸዋል። በገዛ ወርቃችን ‹‹እንቁልልጭ›› ለመባልም ተቃርበናል። የጣልነውን ካላነሳን ግን መሃል ከተማ ላይ እንደነጋበት ጅብ መቅበዝበዛችን ነው፡፡
ከምድር አጽናፍ እስከ አጽናፍ፣ ከሰማይ ክዋክብት እስከ ጨረቃ፣ ከኪነ ጥበብ እስከ ኪነ ህንጻ፣ ከመድኃኒት እስከ ተፈጥሮ ምትሀት በግእዝ ተጽፎ የማይገኝ ዕውቀትና ጥበብ እንደሌለ ሁላችንም በልበሙሉነት እናወራለን። እስኪ ከተጻፈው? ተብለን ብንጠይቅ ግን የምናውቀው ምንም የለም።
ታዲያ ‹‹አለኝ! አለኝ!›› ብለው ጉራ ቢቸረችሩ ምን ሊረባ? ለማንበብ የማንችለውን ግእዝ በጭንቅላት ተሸክመነው ብንዞር ከድካም በቀር ትርፉ ምንድነው? በድንገት ዓለምን ሙሉ ሊለውጥ የሚችል የግእዝ መጽሐፍ እጃችን ቢገባ አንብበን ምን እንደሆነ ለመለየት የማንችል ነን። ተራው ግለሰብ ቀርቶ ስንቱን ተአምር ስለመሥራት የሚያስቡ አብዛኛዎቹ ሊቀ ምሁራኑም ከእጃቸው የገባውን ብራና ገልጦ ለመረዳት ተስኗቸው “ቄሱም ዝም፤ መጽሐፉም ዝም” ዓይነት ሆኖ ተፋጠዋል፡፡
ችግሩ የእነርሱ የመረዳት ችሎታ ስላነሰ አይደለም። ስንቱን የባዕድ ቋንቋ ፈትፍቶ የሚያበላን የትምህርት ሥርዓቱ ስለዚህ ቁምነገር ያለማለቱ ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚታዩ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው ። እንዲያም ሆኖ ጠብሰቅ ባለ የትምህርት ሥርዓት እስካልታቀፈ ድረስ በስንጥር ለኮፍ! ቢያደርጉት ተነስቶ እንደ ወፍ አይበርም።
ግእዝን እናንሳ ብለን ስንነሳ በመጀመሪያ ሊታየንና ቦታ ሊሰጠው የሚገባው በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ነው። በትምህርት የጣልነውን ነገር በምክርና ዝክር ልናመጣው አንችልም። በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለምናደርገው ጉዞም መንገዱ ጥርጊያ ያሻዋል። እያንዳንዳችን ስለ ግእዝ ቋንቋ የያዝነውን አላግባብ የሆነ አመለካከትን ማስወገድ ግድ ይለናል፡፡
ዓላማው ለሀገር ትንሳኤ እንጂ ለፖለቲካ ፍጆታ ስንል አንድ ሰሞን ላይ ሆይ! ሆይ! ብለን ‹‹ሥራ ያውጣህ›› የምንለው ጉዳይም አይደለም። ዛሬ ላይ ጀርመን በዩኒቨርሲቲዎቿ ግእዝን ታስተምራለች። የሚዘረፈው ቅኔያችን ብቻ ሳይሆን እኛ ጭምር ነን። እኛ ግን ይኸው በገዛ ራሳችን ላይ እንቀናለን። እነርሱ ማስተማር ሲጀምሩ ቃል ያልወጣው አንዳንዱ፤ ግእዝ በዩኒቨርሲቲዎቻችን ሊጀመር ነው ሲባል“…የሚያምረው በባለቤቱ አፍ ሲነገር ነው…ግእዝን ለባለቤቱ ለቀቅ…” የሚሉትን እና መሰል ቃላትን ከማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተመለከትኩ።
መጥበብን የምንወድ ብሄርና ሃይማኖት ላይ ሸነቆርነው እንጂ ግእዝ በትንሹ ከአክሱም፣ ከኩሽ…ምድር አልፎ እስከ ማያ ሥልጣኔ ድረስ የነበረ ቋንቋ ነው። እንኳንስ ኢትዮጵያን መላው አፍሪካን አልፎ አስከ መጓዝ ደርሷል። ይሁን እንጂ ደርሰን ለራሳችን ጠላት ራሳችን እንሆናለን። የኖህን መርከብ ሠርታ ግእዝን ከጥፋት ውሃ ያዳነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንኳን የኔ ነው ብላ አታውቅም። ለዚህ አበርክቶዋ እውቅና ሰጥቶ ምስጋና ይገባታል፡፡
በትምህርቱ ሥርዓት ውስጥ መሠራት አለበት ስንል የተሠራና የታሰበ የለም ማለት አይደለም። ግን የተሞከረበት መንገድ መሠረቱ ሳይቆም በመሆኑ ተጨባጭ ለውጥ ለማየት አልተቻለም። ምስኪኑ ገበሬ ጠዋት በማለዳ ተነስቶ መሬቱን ሊያርስ ግርጌው ይወርዳል። እርፍና ማረሻውን ጨብጦ ይቆፍራል። በሬውን ጠምዶ መሬቱን ይጎደፍራል። ሰርዶ መንቀሉን በጉልጓሎው መድከሙን ይያያዘዋል፡፡
ምንም አዝመራ ለማይታይበት መሬት ነጭ ላቡን ያንጠፈጥፋል። በነጋታውም እየሄደ ይህንኑ ግብሩን ይቀጥላል። ገበሬው ትርፉ ከሚዘራው ላይ ሆኖ ሳለ ስለምን ለመሬቱ ይዳክራል? ምክንያቱም መሬቱን በመንከባከብ ያፈሰሰው ላብና ድካሙ ሁሉ ለመሬቱ ብሎ ሳይሆን ገና ለሚዘራት ዘር ሲል ነው። መሬቱን ሳያለማ ዘር ቢዘራ ያለውንም ያጣል እንጂ በተስፋ የሚጠብቀው አዝመራ አይኖረውም።
ያ ሁሉ የምንናፍቀው ዕውቀትና ጥበብ ያረፈው በግእዝ መሬት ላይ እንደመሆኑ አስቀድመን ግእዝን እስካልጠበቅን የምንጠብቀው ሁሉ ከንቱ ምኞትና ተስፋ ነው። ያልመገቧትን ላም ወተት አምጪ አይሏትም። አርግተው ካልናጡት ወተት ውስጥም አይቤና ቅቤ አይወጡም። ታላቁ የአባቶች ጥበብ ላም አለኝ በሰማይ…የሆነብንም ለዚሁ ነው። አሁን ማሰብ ያለብን በአንድ ጀንበር በግእዝ ስለመጥለቅለቅ ሳይሆን አንድ ሁለት እያሉ የማይነቃነቅ መሠረት ስለማጽናት ነው። ሀሁ ተብሎ ፊደል ሳይቆጠር ቃል ልመስርት ማለት ዋጋ ቢስ ነው። ቃላትን ሳያውቁም ቅኔ ካልዘረፍኩ አይባልም።
ከጅምሩ በኬጂና አንደኛ ደረጃም ይሁን በሁለተኛ እናስተምር ብለን ብንጀምር አስተማሪው ማን ሊሆን ነው? መቼም የኔታና መሪጌታ ልንቀጥር አይሆንም። አጀማመራችን መሆን ያለበት የሚያስተምረውን ከማፍራት ነው። እንቅስቃሴውን ስንጀምር ግእዝ የራሱ የሆነ መንግሥታዊ ተቋም ሊኖረው ይገባል። አሊያ ግን ከሌላው ጋር አደባልቀን እንሂድበት ብንል ትርፉ ድካም ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለመጀመር በታሰበው ዕቅድ ውስጥ ሃላፊነቱ የተተወው ሙሉ ለሙሉ ለራሳቸው ለዩኒቨርሲቲዎቹ በመሆኑ የቻሉት በራሳቸው መንገድ ጥቂት ጥረዋል። ሌላውም መንገዱ ጠፍቶት ይሁን ችላ ብሎት ከነኣካቴው ትቶታል ፡፡ግእዝ እንዲሁ ለይስሙላ በራስ መንገድ የሚጀማመር ሳይሆን በዩኒቨርሲቲዎች በራሱ የትምህርት ክፍል የሚመራ፣ በሀገር ደረጃም ከላይ ሆኖ መንገዱን የሚቀይስ ተቋም ያስፈልገዋል። ምንም ስለቋንቋው የማያውቁቱ እንኳን ሰጥ ለጥ አድርገው የሚመሩትን ጉዳይ እኛ እንደምን ያቅተን።
በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የታላቅነት ቁልፍ ያለው በግእዝ ስለመሆኑ እያስተማረ፤ ግእዝን ካሸሸው “እየው ግን አትብላው” ዓይነት አሳይቶ መንሳት ነው። ትንሳኤ ኢትዮጵያን ለማቆም የግእዝን ምርኩዝ መያዙ አማራጭ አናድርገው፡፡
የግእዝ ቋንቋ የትምህርት ሥርዓቱ ዋነኛ አጀንዳ መሆን አለበት ስንል ቋንቋውን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ? ወይንስ ለጥንቱ ትዝታና የኛ ስለመሆኑን ለዓለም ለማሳየት? ሁለቱም የእግረ መንገድ እንጂ ዋነኛ ዓላማዎቻችን ሆነው አይደለም። “ብልጥ ከሰው፣ ሞኝ ከራሱ ይማራል” ብለን ተርተን በዚህ ግን ከየትኛውም ለመማር የቻልን አይመስለኝም። ቆጭቶን ከውድቀታችን ለመማር አልተነሳንም።
እንግሊዝ ያን ሁሉ መጽሐፍቶቻችንን ስታግዝ፣ ጀርመን ቆማ በኛ ግእዝ ቅኔ ስትዘርፍ አይሞቀን! አይበርደን! ጆሮ ዳባ አልን። ለምንድነው ይህን ያህል የሚቋምጡት? ብለን እንኳን አንጠይቅም። ጀርመኖች ግእዝን ለማስተማር ሲነሱ ለቋንቋው ውለታ ለመዋል አይደለም። ደስ ስላላቸው ብቻ ከመሬት ተነስተው ከዚህ ሁሉ የዓለም ቋንቋ ግእዝን ሁለተኛቸው ለማድረግ ሲያስቡ አንድና አንድ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈ ትልቅ የዓለም ሚስጢር በመኖሩ ነው።
ዓለም እንኳንስ ስለጨረቃና ክዋክብት ቀርቶ ስለምትኖርበት ምድር እንኳን በቅጡ ሳታውቅ በፊት የኛ አባቶች መንኩራኩር ሳይፈልጉ፣ ሳተላይት ሳያስወነጭፉ እዚህ ቁጭ ብለው ህዋ ላይ ነበሩ። ዓለም በሽታ ምን እንደሆን ሳያውቅ የኛ አባቶች ግን መድሃኒት ሲቀምሙ ነበር። አሁን ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል። ፊት ፊት ስንመራ በወደቅንበት ሳንነሳ ስለቀረን ኋለኞች ፊተኞች ሆነው አሁን አዋቂም ጌታም፣ ሰጪኝም ነሺም እነርሱ ሆነዋል።
ታዲያ የትና የት ጥለውን ከሄዱ በኋላ እጃችን ያለውን ግእዝን ሊቀበሉን ወደኋላ አቆራርጠው ከወደቅንበት ሲመለሱ ምን ሽተው ነው የሚመስለን? መቼም እንደ ደጉ ሳምራዊ ሊጸድቁብን ነው ብለን የምናስብ አይመስለኝም። ከገባን ግእዝ ጉዳያቸው አይደለም። ጉዳዩ በግእዝ የተጻፈውን ማወቁ ላይ ነው። አውቆም ዓለምን መዘወሪያ ቁልፍ መጨበጥ ነው። ጨብጦም የታላቅነት ማማ ላይ መውጣት ነው። ወጥቶም ሁሉንም ቁልቁል እያዩ፣ ዓለም ሁሉ የሚነጠፍለት ጌታ መሆን ነው። ከዚያስ? እንደማንል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም