ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች መካከል የግብርና ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። በግብርናው ዘርፍ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለመሸፈን ብቻ አይደለም የምትሠራው፣ ለውጭ ገበያም ጭምር ታመርታለች። እንደ ቡና፣ ቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎች ያሉት የወጪ ምርቶች በልዩ ሁኔታ የሚመረቱበት ሁኔታም እየታየ ነው። ሀገሪቱ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችንም እያመረተች ለውጭ ገበያ ታቀርባለች፡፡
እንደ ጥራጥሬ ያሉትን ምርቶች ደግሞ ወደ አፍሪካ ገበያዎች ትልካለች። በተለይ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በእዚህ በኩል ይጠቀሳሉ። በቅርቡ ደግሞ አቮካዶና ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ኮሜሳ ገበያ ለማቅረብ የደረሰችበት ስምምነትም ይህንኑ ይጠቁማል። የኤሌክትሪክ ሃይል ምርትም ሌላው ለአፍሪካ ገበያ እየቀረበ ያለ ምርት ነው። በቀጣይም ሌሎች ምርቶችን ለእዚህ ገበያ ታቀርባለች። ከዚህ ውጪም በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት ሀገሮች የሚገቡ ምርቶችን በሕጋዊ መንገድ ሊላኩ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር የአፍሪካ ገበያዋ ሊሰፋ ይችላል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከአፍሪካ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ፣ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ ምርቶች ስለመኖራቸው ገበያው ያመለክታል። የአፍሪካ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል። ለእዚህም የግብጽ፣ ሱዳንና ኬንያ ኩባንያዎች ወይም ባለሀብቶችን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
አሁን ላይ ሀገሪቱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል መሆኗ ይታወቃል። ነጻ የንግድ ቀጣናው የአፍሪካ ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የሚጣለውን ቀረጥና ሌሎች ከቀረጥ ውጭ ያሉ ተግዳሮቶችን በሂደት በመቀነስ የአፍሪካ የእርስ በእርስ የንግድ ትስስር ለማሳለጥ የተቋቋመ እንደመሆኑ ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ የገበያ እድል ይዞ መጥቷል። ይህም ኢትዮጵያን የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርጋት ይችላል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ፤ ኢትዮጵያ ከንግድ መሠረተ ልማቶች አነስተኛ መሆን፣ ተመሳሳይ እና ውስን ምርቶችን ከመላክ፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማቷ አለመዘመን እና ከአፍሪካ ሀገራት ጋር አመቺ የንግድ ስምምነቶችን እያደረገች ካለመሆኗ ጋር በተያያዘ የነጻ ገበያ እድሉን በአግባቡ መጠቀም ሳትችል ቆይታለች።
አሁን ግን እያከናወነች ባለችው እንቅስቃሴ ነገሮች እንደሚቀየሩ ይታሰባል። ሀገሪቱ ወደ አፍሪካ ሀገራት በስፋት ልትልካቸው የምትችላቸው በርካታ የግብርና ምርቶች ያሏት እንደመሆኗ በእነዚህም ላይ በስፋት እየሠራች ያለችበት ሁኔታ ይህን ሁኔታ ይቀይረዋል ተብሎም ይታመናል ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ከአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን በላይ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን ሕዝብ የሚያስተሳስር ሲሆን፣ ይህም ከ3 ነጥብ 4 (GDP) ትሪሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ አህጉራዊ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ይይዛል። ነጻ ገበያው ይህን ያህል አቅም ያለው መሆኑ አባል ሀገሮች ያላቸውን ሊሸጡ፣ የሌላቸውን ደግሞ ሊሸምቱበት የሚያስችል መልካም አድል ሲሆን፣ ለእዚህ ግን ገበያው የሚጠይቃቸውን መሠረተ ልማቶች አሟልቶ መገኘት ይገባል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በወጪ ምርት ላይ ትኩረት ሰጥተው ለሚሠሩና ኢኮኖሚያቸው እያደገ ለሚገኙ ሀገሮች ደግሞ ይህ እድል ብዙ መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገራት አኳያ ስትታይ በተለየ መልኩ የምታመርትበት መልከአምድር፤ የምርት አይነትና ቁርጠኛ አመራር አላት። በግብርናው ዘርፍ ለውጭ ገበያ ሊውሉ የሚችሉ እንደ ስንዴ ባሉት ምርቶች ላይ በስፋት እየሠራች ከፍተኛ ውጤትም እያስመዘገበች ትገኛለች።
እስከ አሁንም ጥራጥሬ እና የቅባት እህሎችን ወደ አፍሪካ ሀገሮች የምትልክ እንደመሆኗ እነዚህን ምርቶች በስፋት አምርታ ለገበያው በመላክ በሚገባ መጠቀም ትችላለች። በትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎትም እንዲሁ አቅሙ እንዳላት ይታወቃል። በተለይ በአህጉሪቱ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ በኩል ትልቅ አቅም ይሆናል፡፡
የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሌሎች አቅሞች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ሁሉ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ስምምነትን ለመጠቀም ጥሩ እድል መሆኑ እየተገለጸ ነው። ይህ ምቹ ሁኔታ ብቻውን በራሱ ውጤታማ አያደርግም ፤ አቅም በሚገባ አውቆ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻርም ሀገሪቱ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ምን አከናወነች የሚለውን ማየት ተገቢ ነው ።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጣው የ2017 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ረፖርት እንደሚያመላክተው፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ጋር በተያያዘ በርካታ ተግባራትን አከናውናለች። አንዱ ከአባል ሀገራት ለሚቀርቡ ጥያቄዎችና የድርድር ሰነዶች ምላሽ መስጠት የሚለው ነው፤ ይህንንም በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባውን የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ እነዚህን የድርድር ሰነዶችን መከለስ በማስፈለጉ ከዓለም ንግድ ድርጅት ከመጡ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሰነዶችን በመከለስ ማጠናቀቅ ተችሏል። ሰነዶቹንም ለብሔራዊ ስቲሪሚንግ ኮሚቴ በማቅረብ በ18 የግዴታ አንቀጾች ላይ ውሳኔ በማስጠት ለሴክሬታሪያት ተልኳል፡፡
ሌላው የተከናወነው ተግባር ለድርድር ሰነዶች የሚያግዙ የዳሰሳ ጥናቶችን ማካሄድ ነው፤ በቀጣይ ለሚካሄዱ ድርድሮች ግብዓት የሚሆኑና የሀገራችንን አቋም ለመያዝ የሚያግዙ ሁለት ጥናቶች ተመርጠው በቀጣይ ሩብ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራባቸው ይገኛል። እነዚህም በገቢ ንግድ ፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ላይ የዳሰሳ ጥናት ማድረግ እና በቴክኒካዊ የንግድ መሰናክሎች (Technical Barriers to Trade) ዙሪያ ያሉ ሕጎችና አሠራሮችን ከዓለም ንግድ ድርጅት የTBT ስምምነት ጋር ያላቸውን ክፍተት ለመለየት እና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለማጠናከር የሚረዱ ስለመሆናቸው ሪፖርቱ አመላክቷል።
የሁለትዮሽ ውህደትን በማጠናከር የድንበር ንግድ እድሎችን ማስፋት የሚለውም ሌላው ተግባር ሲሆን፤ በዚህ ሥር የሁለትዮሽ ግንኙትን በማጠናከር የወጪ ንግድ ገበያን ማስፋፋት፣ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ውጤታማ የንግድ ስምምነቶችን መፈራረም፤ ሕጋዊ ንግድን ማጠናከር እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተሳካ የንግድ ግንኙነትን ማጠናከር ብሎም ሀገራዊ የድንበር ተሻጋሪ ንግድ (የጠረፍ ንግድ) ስትራተጂ ማዘጋጀት እና ተግባራዊ ማድረግ የሚሉት ጉዳዮች ተዘርዝረው እየተተገበሩ ይገኛሉ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናው ተወዳዳሪነትን በእጅጉ የሚፈልግ በመሆኑ እንደ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ የመሳሰሉ ዋነኛ ተፎካካሪ ሀገራትን በልጦ መገኘት ግድ እንደሚልም መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ አኳያ እቅድ የተያዘው በሁለተኛ ሩብ ዓመት ቢሆንም በዚህ ሩብ ዓመት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያለውን የንግድ ልውውጥ ውጤታማ ለማድረግ እና የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ንግድ እና ኢ-መደበኛ ንግዶችን ወደ መደበኛ ለመቀየር አንድ ስምምንት አድርጎ ወደ ተግባር መቀየር በማስፈለጉ ይህ እውን እንዲሆን ተደርጓል፡፡
አስቀድመው የሚሸጡ ምርቶችን በማምረት ጥሩ ልምድ ያላቸው እንደ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ነጋዴዎችን ለመወዳደር አቅምን ማሳደግ ግድ ይላልና ሀገራችን የምትፈራረማቸው ስምምነቶች በትኩረት መተግበር ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንጻርም በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ በርካታ ተግባራት አሉ። ለአብነት ከጂቡቲ ጋር የተፈራረመችውን የጠረፍ ንግድ ስምምነት ወደ ሥራ ለማስገባትም በሀገራችን በኩል ለአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ሥልጠናና በአዲስ መልክ የጠረፍ ንግድ ፈቃድ ሰጥታለች። በአፋር ክልል በኩል የጠረፍ ንግዱን ጀምራለች። ይህ ግን የበለጠ መጠናከር ይኖርበታል።
ከንግድ ቀጣናው ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረገው ጉዞ በጥሩ ሁኔታ እንዳለ መረጃው ያመለክታል። በቀጣይም ይህን በማፋጠን ወደ ተጠቃሚነቱ መግባት ያስፈልጋል። በዚህ ነጻ ገበያ የምንፎካከራቸው ሀገራት በርካታ ስለሆኑ ለውድድሩ ፈጥኖ በመዘጋጀት ሜዳ ገበቶ መግጠም ያስፈልጋል። ለገበያ የተደረጉ ስምምነቶችና የመሳሰሉት በተግባር መተርጎም አለባቸው። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዳዮችን በሚመለከት ሰሞኑን ሀገራችን ላይ እየተከናወኑ ስብሰባዎችንም ሀገራችን ፍላጎቷን ለማሳካት የምትጠቀምባቸው ሊሆኑ ይገባል። የስብሰባዎቹን ውሳኔዎችንም ለሀገር በሚመጥን መልኩ አውርዶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋ
ክብረ መንግሥት
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም