– ከሁለት ሺህ በላይ የግል ባለይዞታዎች ይነሳሉ
አዲስ አበባ፡– በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስምንት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ግምት መዘጋጀቱን እና ከሁለት ሺህ በላይ የግል ባለይዞታዎች እንደሚነሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ፡፡ የሚነሱ ዜጎች ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ሳይንገላቱ እንዲዛወሩ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ከሁለት ሺህ 800 በላይ ሄክታር ስፋት እና 135 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት እየለማ ነው።
የኮሪደር ልማቱ የአስፋልት፣ የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶችን፣ የወንዝ ዳር ልማትን፣ መዝናኛዎችን፣ የሕፃናት መጫወቻዎችን፣ የመኪና ማቆሚያዎችንና የእግረኛ ማቋረጫዎችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ወደፊት የሚጨምር ቢሆንም እስካሁን በተደረገው ልየታ መሰረት በኮሪደር ልማቱ ሁለት ሺህ 074 የሚደርሱ የግል ይዞታዎች እንደሚነሱ ጠቁመው፤ እስካሁን ከ500 በላይ ለግል ባለይዞታ ተነሺዎች ተገቢው ካሳ መሰጠቱን ገልጸዋል።
ስምንት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ግምት ተሰርቶ፤ አራት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ክፍያ የተፈጸመ መሆኑን አመልክተው፤ ለቀሪዎቹም ካሳ፣ ማጓጓዣ እና የቤት ኪራይ እና ሌሎች ክፍያዎችን ሳንፈጽም ከቦታቸው አናስነሳም ብለዋል፡፡
የልማት ተነሺዎች በሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤት፣ መንገድ፣ ውሃ፣ የጤና ተቋማት እና ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኮሪደር ልማቱ ከመጀመሩ በፊት የልማት ተነሺዎች ምትክ ቤትና የካሳ ጉዳይ በትኩረት ሲሰራበት መቆየቱን ገልጸው፤ ስራው እንደተጀመረ የልማት ተነሺዎች ወደተዘ ጋጀላቸው ስፍራ ያለምንም መንገላታት እንዲዛወሩ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለግል ባለይዞታዎች ካሳ ከመክፈል በተጨማሪም ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ለሁለት ዓመት የሚሆን የቤት ኪራይ እና የማጓጓዣ ገንዘብ የካሳ ሕጉ በሚለው መሰረት እንደሚሰጣቸው አብራርተዋል፡፡
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ በልማት ምክንያት ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች የወቅቱን ገበያ መሰረት ያደረገ ዋጋ ተጠንቶ ለቤታቸው ግምት ይሰጣቸዋል፡፡ ቦታን በሚመለከት ግን ምትክ ስለሚሰጥ ግምት አይሰራለትም፡፡ ከቀበሌ ቤት ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች ደግሞ ምትክ ቤት የሚሰጥ እና ማጓጓዣ የመክፈል ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ አክለዋል፡፡
የሰነድ አልባ ባለይዞታዎችን በሚመለከት ባለው የሰነድ አልባ ሕግና መመሪያ መሰረት የሚስተናገዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሰነድ አልባ በሕገወጥ መንገድ የተገነባው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰነድ አልባ የሚያስብሉ መመዘኛዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ሰነድ አልባ ለሆኑ የልማት ተነሺዎች ዘላቂ መብታቸውን የሚያረጋግጡበት ቦታ ተዘጋጅቶ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
ሁለተኛውን ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በተሰራው ስራም የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን የማጠናቀቅ እንዲሁም ሳይቱን ነጻ የማድረግ፣ ተቋራጭ እና አማካሪ የመመደብ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማት በሚሰራባቸው አካባቢዎች ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ እየተደረገ ስለመሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ 2 ሺህ 879 ሄክታር ስፋት፤ 135 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 240 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 237 የእግረኛ መንገድ፣ 32 የሕፃናት መጫዎች ቦታዎች፣ 79 የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች ፣ 114 የታክሲ እና አውቶቡስ መጫኛ እና ማውረጃን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
58 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች፣ 368 ሄክታር አረንጓዴ ልማት ሽፋን ያላቸው ቦታዎች፣ የ111 ኪሎ ሜትር ሳይክል መንገድ፣ 17 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ 106 የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ 121 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር፣ 182 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር፣ 50 የተሽከርካሪና እግረኛ መተላለፊያ፣ 75 ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ (ሪቴይኒንግ) ስራዎችን የሚያካትት ነውም ተብሏል ::
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም