“ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ የግብርና ሥራዎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው”- አቶ ጥላሁን ከበደ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አርባ ምንጭ:- ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ የግብርና ስራዎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ብዙ ጸጋና አቅም ቢኖራትም ለረጅም ጊዜ ከተረጂነትና ከኋላቀርነት መላቀቅ አልቻለ ችም። ከለውጡ ወዲህ ይህ ታሪክ እየተቀየረ ነው፤ እንደ ሀገር በኢኮኖሚው የታሪክ እጥፋት እየተመዘገበ ነው።

ከለውጡ በኋላ በሀገር ደረጃ የተጀመሩ የግብርና ስራዎች በተጨባጭ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ገልጸው፤ የግብርና ስራን በእውቀትና በውጤታማ ፖሊሲ በመምራት፣ ጸጋዎችን በመለየትና ለስነምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ ሰብሎችን በመዝራት በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የመጣው ለውጥ በስንዴ ምርት የተመዘገበው ውጤት አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀምና በዝናብ ጥገኛ ያልሆነ ግብርናን በማስፋፋት ኢኮኖሚው ላይ ውጤት ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በማስቀረት ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አውስተው፤ በዚህም የታሪክ እጥፋት ተመዝግቧል፣ በግብርና የተመዘገበውን በቱሪዝም ዘርፉም በመድገም ኢኮኖሚውን ይበልጥ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመዘገበው የግብር ውጤት በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና በሀገራት እውቅና የተሰጠው ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ በሌማት ትሩፋት እየተሰራ ያለው ስራ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ነው። ከለውጡ ወዲህ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተሰሩ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የቱሪዝም መዳረሻዎች በአጭር ጊዜ አገልግሎት እየሰጡ ነው። የቱሪስት መዳረሻዎች ሀገር ያላትን አቅም ማሳያ ከመሆናቸውም በላይ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።

ደቡብ ኢትዮጵያ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ በተቋቋመ በአንድ ዓመት ውስጥ በርካታ የልማት ስራዎች አከናውኗል። ክልሉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለው አስተዋጽኦ እንዲጨምር በራስ አቅም ለኢንቨስትመንት ምቹ የማድረግ ስራ ስለመሰራቱ ጠቅሰዋል።

ከልማትና ከመልካም አስተዳደር አኳያ የሕዝብ ጥያቄዎችን የመፍታት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ በቡና፣ በአትክልትና በጥራጥሬ በርካታ ሀብት ያለው በመሆኑ ግብርናውን በልዩ ትኩረት የመደገፍ ስራ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ በግሉ ዘርፍ ተመራጭ እየሆነ ነው፣ በዚህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልጸው፤ በክልሉ ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ አቅም መኖሩን ገልጸው፤ ለማልማት ወደ ክልሉ ለሚመጡ ባለሀብቶች አስፈላጊው እገዛ ይደረጋል ብለዋል።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም

Recommended For You