አዲስ አበባ:– ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ የሚገነባ ሀገራዊ መግባባት የሚፈለገውን ሀገራዊ አንድነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ አስታወቁ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትግሉ መለሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ብዝሃነትን ባከበረ መልኩ የሚገነባ ሀገራዊ መግባባት ጠንካራ አንድነት ለመፍጠር ያስችላል፡፡
ሀገራዊ አንድነት ብዝሃነትን ከግምት ባስገባና በጠበቀ ሁኔታ መከናወን አለበት ያሉት አቶ ትግሉ፤ እራስን ከማስተዳደር ጋር በተገናኘ የሚኖሩ ልዩ ፍላጎቶችንና ብዝሃነትን በጠበቀ መልኩ የሚገነባ ሀገራዊ መግባባት የሚፈለገውን ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት ለመፍጠር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የተለያዩ ባህሎች፣ እሴቶችና ሃይማኖ ቶች ያሏት በመሆኑ ብዝሃነትን ባማከለ መልኩ ሀገራዊ አንድነት ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ትግሉ ገለጻ፣ ህብረብሄራዊነት የኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና የተሰጣቸው 76 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አሉ። ሁሉም የራሳቸው ባህል፣ ማንነትና እራስን በራስ ማስተዳደርን ጨምሮ
ብዙ ፍላጎት አሏቸው፡፡ ሀገራዊ አንድነት በመፍጠር ሂደት ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶች ሊጠበቅ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
መድብለ ባህላዊና ህብረብሄራዊነት አንድ ላይ ተሳስረው መሄድ አለባቸው ያሉት አቶ ትግሉ፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎት ከሀገር አንድነት ጋር ሚዛንን አስጠብቆ ማስኬድ ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ፣ ባለፉት ዓመታት በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች ብዝሃነት የተስተናገደበት መንገድ ሚዛኑን ጠብቆ ላለመሄዱ ማሳያ ነው። ችግሩን ለመፍታት አሁን ላይ ሀገራዊ አንድነት ላይ ያደላ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅ አመላካች ሁኔታዎች መታየታቸውም ጠቅሰዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንድነት፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን ከማጎልበት አንጻር ግዴታና ስልጣን አለበት ያሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው፤ ይህንን ግዴታውንና ስልጣኑን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች ራሳቸውን የቻሉ ፖለቲካዊ አንድምታዎችና ከአስተዳደር ጋር የተገናኙ ጉዳዮች መገለጫዎች መሆናቸውን አመልክተው፤ ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ መግባባት ላይ መሥራት አስፈላጊ እየሆነ የመጣበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚከበረው “ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው። ይህ ደግሞ ለሀገራዊ አንድነት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም