አዲስ አበባ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት በማስተናገድ የዲፕሎማሲ መዲናነቷን አስመስክራለች

-ከሳዑዲ አረቢያ 94 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል

አዲስ አበባ፡– አዲስ አበባ በሩብ ዓመቱ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት በማስተናገድ የዲፕሎማሲ መዲናነቷን ማስመስከሯን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 94 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለመገናኛ ብዙኃን ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት በማስተናገድ የዲፕሎማሲ መዲናነቷን አስመስክራለች።

ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ በኮንፍረንስ ቱሪዝም እና ዲፕሎማሲ ዙሪያ በተሰሩ ሥራዎች የአፍሪካ ድምጽና ወኪል መሆኑዋን በተገቢው ደረጃ ማሳየት ችላለች ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አዲስ አበባም የኮንፍረንስ ቱሪዝምንና ዲፕሎማሲን በመሳብ ረገድ አቅሟ እያደገ መምጣቱንና የዲፕሎማሲ መዲናነቷን ያስመሰከረችበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገዷን ጠቅሰው፤ ከርሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ፣ የካፍ ጉባኤ፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤና ሌሎች ጉባኤዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

ከረሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለችውን ሥራዎች በተሞክሮነት መቅረባቸውን ገልጸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በስፋት ለጉባኤው ታዳሚዎች ማሳየት መቻሉን ተናግረዋል።

የጉባኤዎቹ በተሳካ ሁኔታ መካሄድ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አቅምና ሚና ያሳየ መሆኑን በመግለጽ፤ ጉባኤዎቹ ከገጽታ ግንባታ የቱሪዝምን ገቢ ከማሳደግ አኳያና የተለያዩ ልምዶችን ለማጋራት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ጠቁመዋል።

ጉባኤዎቹ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች እያደረገች ያለችውን የልማት እንቅስቃሴዎችን በተግባር ያሳየችበት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ነብያት፤ በተለይም “ከርሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የሀገራት መሪዎችና የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የልማትና የለውጥ ውጤቶችን ተመልክተዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) የተመራው ልዑክ በሩሲያ ሶቺ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌ ላቭሮቭና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲም በቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ዋና ገዢ ሹ ኩሊን የተመራ የግዛቷ 15 ግዙፍ ኩባንያዎች፣ የሥራ ኃላፊዎች የሚሳተፉበት የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ በመግለጽ፤ ፎረሙ የኢትዮ-ቻይናን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በንግድና ኢንቨስትመንት ይበልጥ ለማጠናከር አይነተኛ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መንግሥት ከሚያዚያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 2017 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 94 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ገልጸው፤ ከማይናማር 31 በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ ደላሎች ከመታለልና የሥራ ስምሪት ስምምነት ሳይደረግ ከሚደረግ ጉዞ መቆጠብ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You