ሞሄ አምባ የተባለችውን መንደር አቆልቁዬ እያየሁ፤ ዙሪያ ገባዬን ደግሞ እንደ ሰማይ ሊደፋብኝ ያኮበኮበ ከሚመስለው እንዶዴ ተራራን የእንግጦሽ እያየሁ በአካባቢው ልምላ ሜና በመልክዓምድር አቀማመጡ በስሜት እየተናጥኩ ነው። ከአንኮበር ቅርብ ርቀት ላይ እገኛለሁ። ለግል ጉዳዬ ወደዚህ ስፍራ ያቀናሁት ከ15 ቀን በፊት ነበር። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የንግድ ቀረጥ ተጀምሮባታል ወደሚባልላት ‹‹አልዩ አምባ›› ዘቅዘቅ ብየ የሄድኩበትን ዓላማ ሳበቃ በወሬ በወሬ ሰዎች ‹‹አፋጀሽኝ›› ደርሼ መጣሁ ሲባል ሰማሁ። ነገሩ ከጆሮዬ ስለገባና አዲስ ስለሆነብኝ ማጣራት ፈለግሁ። አፋጀሽኝ ምንድን ናት፣ ለምን አፋጀሽ ተባለች፣ ከመቼ ጀምሮ ስያሜዋን አገኘች ስል የመንደሩን ነዋሪዎችና አዋቂዎችን ልጠይቅ ወደድኩ። እዚያው አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሥፍራ ሄድኩኝ።
አቶ ከበደ ወልዴ 65 ዓመታቸው ነው፤ የተወለዱትም ሞሄ አምባ በሚባል ሥፍራ ነው። አራት ሴቶችና አምስት ወንዶች አሏቸው። ከሁለቱ በቀር ሁሉን አስተምረዋል። እርሳቸው ደግሞ በዘመነ ደርግ የጎልማሳ ትምህርት ቀስመዋል። የትዳር አጋራቸው ግን ለፊደል እንግዳ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ትምህርት ያላጠናቀቁ ልጆቻቸውን በየወሩ የቤት ኪራይ 1ሺ800 ብር ከፍለው እያስተማሩ ነው- በአዲስ አበባ። ታዲያ ለገቢ ምንጫቸውም ‹‹አፋጀሽኝ›› ባለውለታቸው ናት። እርሳቸው ደግሞ በዚህች ሥፍራ 42 ዓመታት ኖረዋል፣ አፋጀሽኝን ጠብቀዋል። እኚህ ሰው በአካባቢው ስለሚነሱ መልካም ሥራዎች ሁሉ አሻራቸው ጎላ ብሎ ይታያል።
እንደ አቶ ከበደ ገለፃ፤ አካባቢው ለምለም ስለነበር በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት የነበሩ ባለርስቶች አንዲት ትንሽ የውሃ ምንጭ ስለነበረች ይጠቁመት ነበር። በተለይም አካባቢው ፍራፍሬ ለማልማት የታደለ ስለነበረ ባለርስቶች በዚህ ሥፍራ ይጣሉ ነበር። በጭቃ ግንብ እየገነቡም ውሃውን ገድበው ለራሳቸው ለመጠቀም ይሞክሩ ነበር።
ፊን! ፊን! እያለች ከመሬት ውስጥ ከምትመነጨውና፤ በእንዶዴ ተራራ ጠፈፍ ብሎና መሬት ለመሬት ሰርጎ በሚለግሳት ውሃ አፋጀሽኝ በቅባት እንደወረዛች ልጃገረድ አካባቢውን ሸጋ መልክ ሰጥታ የውበት ፀዳል ሆናለች። የተጠራቀመው ውሃ ከትንሿ ምንጭ ሳይሆን ከትልቅ ጅረት የሚመነጭ ይመስላል። ብቻ በነገስታቱ ዘመን ይህችን ውሃ ‹እኔ ልጠቀም› በሚል ሽኩቻ የባለርስት አሽከሮችም ተገድለውበታል፤ ደም ፈሶበታል። ነገሩ እየከፋ ሲሄድ ባለርስቶቹ ተሰባስበው ‹‹ይህች ውሃ አፋጀችን›› ሲሉ መከሩ። ከዚያም በወቅቱ መፍትሄ ያሉት ውሃውን መድፈን ነበር። ከዚያም አገሬው በሙሉ በትልልቅ ድንጋይ፣ ሙቀጫ እና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን እያመጡ ‹‹አፋጀሽኝ›› የተባለችው ውሃ ደፈኗት።
ዓመታት አልፈው 1977 ዓ.ም በአካባቢ ከፍተኛ ድርቅ ተፈጠረ። በዚህን ጊዜ ‹‹ሉተራን›› የሚባል ድርጅት ወደ አካባቢው መጣ። በወቅቱ አፋጀሽኝና አካባቢው በግለ ሰቦች ተይዞ ነበር። የእንዶዴ ተራራም ራቁቱን አግጦ ነበር። አፋጀሽን ለመታደግም ህዝብ እርከን እየሠራ አካባቢውን እንዲጠብቅ፤ አፋጀሽኝ ደግሞ እየተንከባከበ ለሕይወት መሰረት እንድትሆን መከሩ። ቀድሞ ጉድጓዱ ውስጥ የተቀበሩ ባዕድ ነገሮችም ወጥተው ውሃዋ ነፍስ ዘራች። በእርግጥ የተቀበረው ነገር ብዙ ስለነበር ሁሉንም ባዕድ ነገር ማስወገድ አልተቻለም። የሆነው ሆኖ ሉተራን የተባለው ድርጅት ‹‹አፋጀሽኝን›› ዙሪያዋን በግንብ አሳምሮ ውሃው እንዲጠበቅ ሆነ።
በአካባቢም የችግኝ ጣቢያ ተመሰ ረተ፡ በአካባቢውም ያልተለመዱ የዕፅዋት ዝርያዎችም በስፋት ይዘሩና ይሰራጩ ጀመር፤ ልማቱም እያደገ መጣ። አቶ ከበደም በዚህ ድርጅት ውስጥ በወር 90 ኪሎ ግራም ስንዴ እየተሰፈረላቸው እና አምስት ሊትር ዘይት በደመወዝ መልክ ይሰጣቸውና በዚሁ ሥራ ይሰሩ ጀመር። በሂደትም የመንገድ መሠረተ ልማቶች እየተሟላ ሄደ። ይሁንና ይህ ሉተራን ድርጅት በጀት ሲያጥረው 1980ዎቹ አካባቢውን ለቆ ወጣ። ከዚያም 1982 ዓ.ም ‹‹ፓዴት›› የሚባል ድርጅት መጣ፤ እናም ‹‹አፋጀሽን› የውሃ መስመር ዘርግቶ ነዋሪዎች ለማከፋፈል ሞከረ። ግን ይህ ድርጅትም ወዲያውኑ ለቆ ወጣ። በመቀጠል ደግሞ የመኖር ህልውና የሆነችው ‹‹አፋጀሽኝ›› የወረዳው ግብርና ቢሮ ያስተዳድር ጀመር።
በመቀጠል ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያ ናዊ ልማት ተራድዖ ኮሚሽን ወደ ስፍራው መጣ። በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ቦረቦር እና ተራቁቶ የነበረውን የእንዶዴ ተራራ በደን ሸፍኖት፤ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ አደረገው። በአካባቢው ግዙፍ 10 የውሃ ታንከሮችን ሰራላቸው። ብልሽት ቢደርስባቸው በሚል እሳቤም 70 ሰዎችን በጥገና ሙያ አሰልጥኖ ውሃው ሆነ መስመሩ ችግር ሲደርስበት ወዲያውኑ እንዲጠግኑ አደረገ። ከዚያው አፋጀሽኝን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ አካባቢው በመስኖ እንዲለ ማም፤ ግጭት እንዲርቅም ሆነ።
በአካባቢው የዓሳ ገንዳ ሰርቶ 30 ሥራ አጥ ወጣቶች ሥራ ፈጥሮላቸዋል፤ ዶሮ እርባታ ጀምሮ አዲስ የሥራ ባህል አስለምዶ አፋጀሽኝ የሚሸሿት ሳይሆን የሚመር ጧት ሥፍራ መሆኗን ይናገራሉ። በደን እንዲሸፍንም አደረገ። አገር በቀል ድርጅት መሆኑም የበለጠ እንዲቆረቆር አድርጎታል ይላሉ። ታዲያ አፋጀሽኝ ከግጭት ይልቅ የልማት ቀጠና ሆናለች ይላሉ-አቶ ከበደ።
ቀደም ሲል በእውቀት ማነስ ሰዎች ይጣሉ እንደነበር የሚስታውሱት አቶ ከበደ፤ አሁን ደግሞ የሰዎች መሰልጠንና መረዳት ሲበዛ ውሃው ለመጠቀም ሽኩቻ ተጀመረ ‹‹ከመረዳት መፋጀት እየመጣ መሆኑን›› ይናገራሉ። ነገር ግን እነዚህ 10 የውሃ ታንከሮች መሠራታቸው ችግሩን እያቃለለ ነው ይላሉ።
አቶ አሸናፊ ወርቅነህ ደግሞ 65 ዓመታቸው ነው። እርሳቸውም አፋጀሽኝ ከችግር ሲጠብቋት 43 ዓመት ሞላቸው። እርሳቸውም የአፋጀሽኝ ባለርስት ዱላ ያማዘዘች ነበረች ይላሉ። ቀድሞ ባለርስቶች ውሃዋን ለመስኖ እና ሌላ ግልጋሎት ለመጠቀም ሲሉ ወደ ተለያዩ ቦታ ሲጠልፉ አንዱ ሲያፈርስ ሌላው ሰው ሲያቃና ሁሉ ይፋጅበት ጀመር። ከውሃ በተጨማሪም ቀበሌውም ‹‹አፋጀኸኝ›› ተብሎ መጠሪያ እንዳገኘ ይናገራሉ። ሰባት ልጆች ወልደዋል። ወዲህ ደግሞ እርሳቸው ልጅ ሳሉ ‹‹አፋጀሽኝ›› ፀበል እንደሚባልና የአገሬው ሰው እንደ ፀበል እየሄደ ይጠመቅ ነበር ይላሉ። ብቻ የአካባቢው የባለርስቶች ዓይን ማረፊያ እና ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ደብተራ ሰርጤ፣ አየለ ሰርጤ፣ ሽፈራ በየነ፣ አበባየሁ በየነ በአካባቢው ከነበሩ ባለርስቶች እንደነበሩም ያስታውሳሉ።
አፋጀሽኝ አሁን የበረከት ስፍራ እየሆነች ነው የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ በአፋጀሽኝ ትሩፋት ቤት ሠርተው ተቀይረዋል። ባንክ ቤት 10ሺ ብር አስቀምጠዋል። አሁን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሲታገዝ አገር እየለማበት ነው። ቀድሞ ጉልበተኛና ባለርዕስት ብቻ ይጠቀምበት የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድዖ ኮሚሽን በመምጣቱና አዲስ አሰራር በመዘርጋቱ ሁሉም ተጠቃሚ እየሆነ ነው ይላሉ። ባለፈው ዓመት ብቻ በማህበር ተደራጅተው ባህር ዛፍ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ሌሎች ችግኞችን ሸጠው 18ሺ ብር አግኝተዋል- አቶ አሸናፊ። ታዲያ ከአፋጀሽኝ ማዶ እያሻገሩ ቤታቸውን እየቃኙ፤ አፋጀሽኝንም በስስት እየተመለከቱ ይኸው ዓመታት ነጎዱ፤ እርሳቸውም እስከ ሕይወት ፍፃሜያቸው ሊጠብቋት ይቋምጣሉ።
አቶ አሸናፊ እንደሚሉት፤ በድርቅና ደን እጦት ገጦ የነበረው እንዶዴ ተራራ ደን በመልበሱ ለአካባቢው ሌላ ጠበቃ ይመስል የውሃ ምንጭ ሆኗል። ሰውም ሥርዓት ይዞ በአግባቡ እየተጠቀሙበት ነው። ዛሬ አካባቢው በልማት በመታጀቡ በ‹‹አይሱዚ መኪና›› ፍራፍሬ እየተጫነ ወደ ከተማ ይወሰዳል። ውሃውም እየጎለበተ መጠኑም እየጨመረ መጥ ቷል።
አቶ አሸናፊ፤ በ1970ዎቹ ትዳር መስርተው ነበር። ግን ችግር አይኑን አፍጦ በመጣ ጊዜ 12 በሬ ሞቶባቸዋል። ያጣ የነጣ ሰውም ሆነው ነበር። ግን ዕድሜ ለ‹‹አፋጀሽኝ›› እርሳቸውንም ታድጋለች። ሰው ሲፋጅ ወየው ጉድ! እያሉ ዓመታትን አስቆጥረው፤ ዛሬ ደግሞ ብር እየቆጠሩ ሕይወታቸው እየተለወጠ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድዖ ኮሚሽን አፋጀሽኝ ወደ ሥራ ስላስገባት ይላሉ።
ይሁንና አሁንም ቢሆን ወጣቶች ውሃ ዋና እያማራቸው ወደ አፋጀሽኝ ጎራ ይላሉ፤ እኛ ግን እየከለከልን ነው ይላሉ። ውሃው ለዓሣ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ስለሚጠቀም ይበከላል ብለው ይሠጋሉ።
አሁን ፊን! ፊን! ከምትለው ውሃ ሁሉም በየፊናው አመስግኖ ይኖራል። የሁለቱም አዛውንቶች ደመወዝ በወር 300 ብር ነው። ግን የግጭት መንሰኤ የነበረችው ምንጭ ህዝቡ ከመፋጀት ወደ ልማት በመዞራቸው ደስተኞች ናቸው። የሰዎች ሕይወት ተቀይሮ፤ አካባቢው ተጠብቆ ከግጭት ነፃ መሆኑ ያስደስታቸዋል።
በአቶ ከበደ እና አሸናፊ እምነት፤ አፋጀሽኝን ሲጠብቁና ሲንከባከቡ፣ አፋጀሽኝም በረከቷን ለአገሬው ሰው መለገሷ ትቀጥላለች። ግን ደግሞ 42 ዓመታት ያገለገሉበት ሥራ ላይ ቋሚ ተቀጣሪ አለመሆናቸውና፤ በ300 ብር ደመወዝ ብቻ ተወስነው መኖራቸው ቅር ይላቸዋል። ወዲህ ደግሞ ‹‹ጎመን በጤና›› እያሉ ያገኙትን እያመሰገኑ መጪውን ተስፋ እያደረጉ ይኖራሉ፤ የአፋጀሽኝ ጠባቂዎች፣ የአፋጀሽኝ ልጆች፣ የአፋጀሽኝ ተቆርቋሪዎች።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር