አሳሳቢው የውሻ እብደት በሽታ

በዛብህ ደሳለኝ በውሻ እብደት በሽታ (ራቢስ) በተያዘ ውሻ በመነከሱ በለጋ ዕድሜው ከ45 በላይ መርፌዎችን በዕምብርቱ እንዲወስድ ተገድዷል፡፡ መርፌው በወቅቱ ካስከተለበት ስቃይ በላይ አሁን ድረስም ቅዝቃዜ እና ብርድ ሲያገኘው ስለሚያመው ልብስ ደራርቦ መልበስ ያዘወትራል፡፡ ተሸፋፍኖ መሄድንም እንደሚመርጥ ይናገራል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስኮ አካባቢ ነዋሪ የሆነው በዛብህ በልጅነት ዕድሜው በውሻ ዕብደት በሽታ በተያዘ ውሻ መነከሱ ዛሬም ድረስ የጤና ዕክል አስከትሎበታል፡፡ ነገሩን የከፋ አድርጎ ያባባሰው ደግሞ የነከሰው ውሻ በውሻ ዕብደት በሽታ እንደተያዘ አለመታወቁ ነበር፡፡

ውሻው በበሽታው እንደተያዘ ባለመታወቁ የበዛብህ ወላጆች ወደሕክምና ከመውሰድ ይልቅ በቸልታ ያልፉታል። ጉዳዩ ውሎ ሲያድር ልጁ ላይ የህመም ምልክት በመታየቱ ወደ ሕክምና ወሰዱት፡፡

በወቅቱ በዛብህን የመረመሩት የሕክምና ባለሙያዎች ሕፃኑ በራቢስ በሽታ መያዙን ተናግረው፤ በሕይወት የመትረፉ ዕድል 50 በመቶ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የሕፃን በዛብህ አባት እንዲወስኑ ተደርጎ ሕክምናው ተጀመረ፡፡

አሁን በዛብህ አድጎ እና ሥራ ይዞ አዲስ አበባ ውስጥ የመንግሥት ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በኮሪደር ልማቱ መዲናዋ ውብ መሆኗ ቢያስደስትም በየመንገዱ የውሾቹ ነገር የሚታዩት ውሾች ጉዳይ ግን ሊታሰብበት ይገባል ይላል፡፡

በምሽት የእጅ ባትሪ ይዞ መሄድን ግድ ይሉ የነበሩ የመዲናዋ መንገዶች አሁን ላይ ፍንትው ብለው ብርሃናቸውን ፈንጥቀዋል። እየሰነፈጡ ለጉንፋን ይዳርጉ የነበሩ ጎዳናዎቿ ወደ ጠረናቸው ማራኪ ሆኗል። ሆኖም ወትሮ በየመንገድ የሚንገላወዱ ውሾችና መንደሮች ሲፈርሱ ማደሪያ ያጡ ውሾች ግን ዛሬም አሉ፡፡

በመዲናዋ ለመናፈስ የወጣ ከተሜ ምቹ የእግረኛ መንገድና የመዝናኛ ቦታዎች ተገንብተውለታል። ይሁንና ባለቤት አልባ ውሾች እዚህም እዚያም የመታየታቸው ጉዳይ ደግሞ ሊታሰብበት እንደሚገባ በዛብህ ይናገራል።

ሚሊዮችን የያዘችው አዲስ አበባ ፤ ከነዋሪዎቿ መሳ ለመሳ የሚኖሩ 400 ሺህ ባለቤት አልባ ውሾችም እንዳሏት መረጃዎች ያመላክታሉ።

አያድርገው እና የውሻ ዕብደት በሽታ (ራቢስ) አልያም ሌላ በውሾች የሚተላለፍ ወረርሽኝ ቢከሰት ተጠቂ የሚሆነው ሰፊው ሕዝብ ነው። በግብርና ሚኒስቴር የቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ ዴስክ ኃላፊ ሲሳይ ጌታቸው (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ የውሻ ዕብደት በሽታ ትኩረት ከተነፈጋቸው በሽታዎች ውስጥ አንዱ ነው ፡፡

በሽታው ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ተናግረው፤ በዓለም ላይ ከ150 ሀገራት ውስጥ በሽታው እንደሚገኝ፤ በአህጉር ደረጃ ሲታይም በአፍሪካና በኤዥያ የሚገኘው አብላጫውን እንደሚይዝ ይጠቅሳሉ፡፡

አስከፊው ሁኔታ ደግሞ መቶ በመቶ ገዳይ በሽታ መሆኑ ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡ በሽታው ከ15 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትና ታዳጊዎችን እንዲሁም ሴቶችን ማጥቃቱም ሌላ የበሽታው አስከፊ ገፅታ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

አንድ ሕፃን በውሻ ዕብደት በሽታ ከተለከፈና በጊዜው ሕክምና ካልወሰደ በአካባቢው የሚያገኘውን ነገር እየነከሰ፤ ራሱን ከአገኘው ነገር ጋር እየፈጠፈጠ ለሞት የሚዳረግበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ በሽታው ከበሽታነቱ ባሻገር ማኅበረሰባዊ ሥነልቦና ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ያስገነዝባሉ፡፡

የውሻ ዕብደት በሽታ በክረምትም ሆነ በበጋ የሚመርጠው ጊዜ አለመኖሩን በመጥቀስ፤ በወረርሽኝ መልክ በየትኛውም አጋጣሚ ሊነሳ ይችላል ይላሉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የውሻ ዕብደት በሽታን እኤአ እስከ 2030 ድረስ ለማጥፋት የተቀመጠ ግብ መኖሩን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያም ግቡን ለማሳካት የተቀረፀ ስትራቴጂ እየተተገበረ እንደሚገኝ ይገልፃሉ፡፡ በተመሳሳይ በአዲስ አበባም ይህ ስትራቴጂ የሚተገበር ይሆናል ይላሉ።

የውሻ ባለቤትነትንና የውሻ ብዛትን መቆጣጠር በዚህ ስትራቴጂ አንዱ የውሻ ዕብደት በሽታን ለማጥፋት የሚደረግ ርምጃ መሆኑን ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር 400 ሺህ እንደሚደርስ መገመቱን እንደሚጋሩት፤ ከውሾች ተፈጥሯዊ የመራባት ሂደት በተጨማሪ በከተማዋ በየጊዜው በሚሠሩ ልማቶች የሚኖሩበትን አካባቢ በሚለቁ ዜጎች ምክንያት የባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም አስጊ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

በዚህም ልማት የሚያሠራ አካል ዜጎች የሚኖሩበትን አካባቢ ሲለቁ ውሾቻቸውን ይዘው እንዲዘዋወሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባት ላይ መደረሱን ጠቅሰው፤ ሂደቱንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነን እንደግፋለን ይላሉ፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት መንገድ ላይ ውሾች በብዛት ይታያሉ፤ ይህን ቁጥር መቀነስ ተገቢ በመሆኑ ጉዳዩን የተመለከተ ዕቅድ መያዙንም ያነሳሉ፡፡ ያረጁና የታመሙ ውሾችን ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሕግ በሚፈቅደው መልኩ የሚወገዱበት መንገድ እንደሚመቻች ነው የሚናገሩት፡፡

ሌሎች ውሾች ደግሞ ባለቤት እንዲኖራቸው እየተሠራ መሆኑን ከእነዚህ ርምጃዎች የሚተርፉት ውሾች ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ እንደሚወገዱ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ይህ ሥራ የሚጀመር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የውሻ ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን እንደሚገመት ጠቁመው፤ በሽታውን ከሀገር ለማጥፋት ለአምሥት ተከታታይ ዓመታት 70 በመቶ የሚሆነውን የውሻ ብዛት መከትብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You