አዲስ አበባ፡- 120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታው አፈጻጸም 82 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 120 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ታስቦ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ግንባታ ፕሮጀክት በአሁኑ ጊዜ አፈጻጸሙ ላይ 82 በመቶ ደርሷል፡፡
የግንባታ ሥራው ደረጃ በደረጃ እየተሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ ሞገስ ፤ በዚህም ስምንት ክላስተር ያላቸው 80 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችሉ የንፋስ ተርባይኖች ተከላ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አሁን ላይ
80 ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ብሄራዊ የኃይል ቋት የማስገባቱ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ የተቀረውን 40 ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ቋት ለማስገባት የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ተርባይኖችን የመትከል ሥራው በፋይናንስ አቅርቦት ምክንያት ለሁለት ዓመታት ባለበት እንዲቆም ተደርጎ እንደነበር አውስተዋል፡፡
አሁን ላይ ግን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አበዳሪዎችን ሳይጠብቅ በራሱ ፋይናንስ ግንባታውን ለማካሄድ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡
የአይሻ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የንፋስ ሃይሉን ወደ ሃይል ቋት በማስገባት ሃይል ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ስርጭት የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አዳማ የሚገኙት ሁለት ፕሮጀክቶች እንዲሁም በአሸጎዳ ያለው የንፋስ ሃይል ማመንጫን ጨምሮ አይሻ አራተኛ የንፋስ ሃይል ማመንጫ ነው፡፡ ካሉት የንፋስ ማመንጫ ውስጥም አይሻ ውጤታማ ሊባል የሚችል ነው ፡፡
የአይሻ ፕሮጀክት እየተገነባበት ያለው አካባቢው ከባህር ለሚነሳ ንፋስ ቅርብ በመሆኑ ተርባይን የማንቀሳቀስ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከሌሎቹ በአንጻራዊነት ሲታይ ፕሮጀክቱ የተሻለ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ፤ ፕሮጀክቱ በአካባቢው አልሚዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል ፈጥሯል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው መንግሥት በቅርቡ ከአሚያ ፓወር ጋር የተፈራረመው ስምምነት መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል። በስምምነቱ መሠረትም የግል አልሚዎቹ እስከ 300 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ ፕሮጀክት ለመገንባት ማቀዳቸውን አንስተዋል፡፡
ይህም እንደ ሀገር ከንፋስ መጠቀም ያለብንን የኤሌክትሪክ ኃይል እንድናገኝ ያደርጋል ብለው በተጨማሪም ተቋሙ በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም