አዲስ አበባ፡- የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጁ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ የወጣውን ፖሊሲ ወደ ተግባር እንደሚያሸጋግር ተገለጸ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅና የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እንደገለጹት፣ የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጁ የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በመንግሥት የተወሰነውን ፖሊሲ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል ነው፡፡
በህብረተሰቡ ዘንድ የባንኮች ተአማኒነት ጠንክሮ እንዲሄድ ዘርፉ በሕግ ማዕቀፍና በአዋጅ መደገፍ አለበት ያሉት ሰብሳቢው፣ የሕግ ማዕቀፉ ከዓለም አቀፍ የባንኮች ሥራ አኳያ የተቃኘና ከሀገሪቱ የሕግ ሁኔታዎች ያገናዘበ ሆኖ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የፋይናንስ ዘርፉን ዘመናዊ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ዘርፉ በቴክኖሎጂ፣ በእውቀት፣ በክህሎት ለመደገፍ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ በመፍጠርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር አብረው በመሥራት በቴክኖሎጂ፣ የአቅምና ክህሎትን በማሳደግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚደግፍም አመላክተዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፣ ረቂቅ አዋጁ መንግሥት በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ የውጭ ኢንቨስትመንትን የፈቀደ በመሆኑ አዋጁ ፖሊሲውን ወደ ተግባር የሚያሸጋግር ነው፡፡
የውጭ የባንኮች በፋይናንስ ዘርፍ ተሰማርተው ለኢኮኖሚው እድገት ቀጣይነት ያለው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል አዋጅ ነው ያሉት ገዢው፣ የውጭ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገቡ ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርትና አካሄዶች ምንድናቸው? የሚለውን የሚለይ ነው ብለዋል፡፡
የባንክ ሥራ አዋጅ ከ16 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለክለሳ እንደተዘጋጀ በመግለጽ፣ ረቂቅ አዋጁ አዳዲስ ባንኮች ወደ ዘርፉ ሲቀላቀሉ ሊያሟሉ ስለሚገባቸው መስፈርትና ፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን የሚወስን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በፍቃድ አሰጣጥን፣ አካሄዱንና የውጭ ባንኮችን አመራረጥ ሂደትን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ ባንኮች ቀውስ ቢያጋጥማቸው ብሔራዊ ባንክ እንዴት መፍትሄ መስጠት እንዳለበት የተደራጀ ሥርዓትንም ያበጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት የማድረግ እሳቤ በመንግሥት በኩል ውሳኔ አግኝቷል ያሉት ገዢው፣ የዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ ዘርፉ ከፍ እንዲልና ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚውን የብድር ፍላጎቶች ማሟላት የሚያስችሉ ባንኮች ወደ ሥራ ሲገቡ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ እንሠማራለን ብሎ ሁኔታውን ያሟላና የጠየቀ ሁሉም ባንክ ፍቃድ እንደማይሰጠው በመግለጽ፣ ብሔራዊ ባንክ እንደ ኢኮኖሚው ሁኔታ እያየና የፋይናንስ ዘርፉን ተጽዕኖ እየገመገመ እንደ ሁኔታው ፍቃድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በባንክ ሥራ ውስጥ ለመሳተፍ ከሚቻልባቸው አንደኛው መንገድ የውጭ ባንኮች ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በቅንጅት መሥራት መሆኑን ገልጸው፣ የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር በፈቀዱት ልክ በቅንጅት እንዲሠሩ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየ ሲሆን ለብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም