አዲስ አበባ፡– በሀዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ለከተማው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን የሲዳማ ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ በከተማው ስድስት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እየተሠራ ነው::
በሲዳማ ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደስታ ዳንጮ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሲዳማ ክልል መቀመጫ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ስድስት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለከተማው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
በከተማው በመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በተመረጡ አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ተግባራትን ያካተተ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህም መምቦ ሆቴል እስከ ሪፈራል ሆስፒታል አደባባይ አንድ ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሥራ ከ90 በመቶ በላይ ግንባታው ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡
ከሻፌታ አደባባይ እስከ ሳውዝ ስፕሪንግ እንዲሁም ከመሀል መገንጠያ እስከ ፍቅር ሀይቅ እና ከታቦር መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ግሎባል ጋራጅ በአጠቃላይ አምስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ የሰነድ፣ ዲዛይን ዝግጅት እና ካሳ ክፍያ የመሳሰሉት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀው ለግንባታ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም ወጣ ያለ አጥር እና መንገድ ዳር ቤቶች የማፍረስ እንዲሁም መንገዶችን በማስፋት ወደግንባታ የሚገባ መሆኑን አቶ ደስታ ገልጸዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ምቹ የእግረኛ መንገድ፣ ጭስ አልባ ትራንስፖርት ለማስፋፋት የሚያግዝ የብስክሌት መንገድ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ ፋውንቴን፣ መዝናኛ፣ የልጆች መጫወቻ እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የሚያካትት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማው የመንገድ ማስፋፊያ ሥራዎች እየተሠራ ሲሆን፤ ከ30 እስከ 50 ሜትር ስፋት ያላቸው እና በአጠቃላይ 35 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 10 መንገዶች ጥናት አልቆ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ደስታ እንደገለጹት፤ ከተማዋ የቱሪስት ማዕከል ከመሆኗ አንጻር ለመዝናናት እና ለኑሮ ተስማሚ ከሚባሉ ከተሞች ተጠቃሽ ናት፡፡ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ ከሚጠበቀው በላይ ከፍ የሚያደርግና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡
እንዲሁም ከተማዋ ያላትን የቱሪዝም መስህብነትና ተመራጭነት በማሳደግ ለከተማው ብሎም ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም