ቦንጋ፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተካሄደው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት አሳታፊና ሃሳቦች ያለምንም ተጽእኖ የተንሸራሸሩበት እንደነበር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሲያካሂደው የነበረውን የአጀንዳ ማሰባሰብና ለሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት አጠናቋል።
የምክክር መድረኩ ተወካዮች አጀንዳዎቻቸውን ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ፣ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እና ዘገየ አስፋው በይፋ አስረክበዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ በክልሉ ያካሄደው የምክክር ሂደት ውጤታማ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ክልላዊ ምክክሩና አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ሃሳቦች ያለምንም ገደብ እና ተጽእኖ ተንሸራሽረውበታል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ አንድ ሺህ የሚሆኑ ከ10 የተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች የተወከሉ ተወካዮች በሰፊው ተመካክረው አጀንዳዎቻቸውን ማሰባሰባቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ በሁለተኛው ምዕራፍም አንድ ሺህ 200 የሚሆኑ የክልሉ ባለድርሻ አካላትና የህብረተሰቡ ተወካዮች ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ገለፃ፤ 11 ክልላዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ የክልሉ መንግሥት ተወካዮች፣ ተቋማትና ማህበራት፣ ታዋቂና ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች በጥልቅ መክረውና አጀንዳዎችን አደራጅተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
በክልሉ የምክክር ሂደት አጀንዳዎችን ከማሰባሰቡ ባሻገር ጊዜ ወስዶ፣ ተከባብሮና ተደማምጦ የጋራ አጀንዳዎችን መቅረጽ እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነበር ያሉት ኮሚሽነሯ፤ እንዲሁም ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮች ውክልናም ግልጽና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ሁኔታ መከናወኑን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ እንደ ሀገር ላሉብን የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ አጀንዳዎችን በመቅረጽ መግባባት ላይ እንዲደርስ እየሰራ ነውም ብለዋል።
እንዲሁም ሌሎች አጀንዳዎች በየደረጃው ላሉ የሚመለከታቸው አካላት እንዲቀርቡና መፍትሄ እንዲያገኙ እንደሚሰራ የገለጹት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ቀጣዩ ተግባር የሚሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔውን ማካሄድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ዕድል ለሀገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ መልካም መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን በመረዳት፤ በሂደቱ እየተሳተፉና ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉ ላሉ አካላት ኮሚሽኑ እንደሚያመሰግን ተናግረዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ ላይ በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት ለተሳተፉ ሁሉም የህብረተሰብ ተወካዮች እና ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ለመድረኩ ስኬት ለተጉ አካላት ኮሚሽኑ ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።
በቀጣይም የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች እንደሚካሄድ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አመላክተዋል።
በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሐረር፣ በአፋር፣ በሱማሌ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን መቻሉን ኮሚሽኑ መግለፁ የሚታወስ ነው።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም