አዲስ አበባ :- መንግሥት ለግል አልሚዎች ትኩረት ሰጥቶ ችግሮችን የሚፈታበት አሰራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት 15ኛው የንግድ ሚኒስትሮች ካውንስል ጉባኤ ተሳታፊዎችና የአባል ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች የወጪ ንግድ ምርቶች ማሳያ ማእከልንና ገላን የሚገኘው ኤ.ኤም.ጂ ኢንዱስትሪያል ፋብሪካ ጐብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያን ለግል አልሚዎች ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው። የግል አልሚዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግሥት ብዙ እየሰራ ነው ብለዋል።
የግል አልሚዎች ለሀገር እድገት የጀርባ አጥንት ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ዕድገት እየጨመረ ሲመጣ ሀገር በቀል አልሚዎች ያስፈልጋሉ። በመሆኑም መንግሥት ለግል አልሚዎች ትኩረት ሰጥቶ ችግሮችን የሚፈታበት አሰራር ዘርግቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ እድገት ውስጥ የግል አልሚዎች ሚና አይተኬ በመሆኑ በፖሊሲና ስትራቴጂ የመደገፍ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው። የመንግሥት ድጋፍ ባይኖር ኤ.ኤም .ጂን ጨምሮ በርካታ የግል ድርጅቶች ለውጤት አይበቁም ነበር። መንግሥት አቅሙ በፈቀደው ልክ ሁሉንም አልሚዎች የመደገፍ የማበረታታት ስራ እየሰራ ነው።
ከሀገር ውስጥ ወጥተው አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድርን እንዲወዳደሩ የማድረግ ጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው በኢትዮጵያዊያኖች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከውጭ ሲታይ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ንግድና ኢንቨስትመንት ያለ ይመስላል፣ ነገር ግን ብዙ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች የተያዙት በውጭ ዜጐች ነው። የኢትዮጵያ ሀብት 99 በመቶ የተያዘው በኢትዮጵያ ነው ብለዋል።
አፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና አንዱ እቅዱ የግል አልሚዎች ለኢኮኖሚው አጋዥ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ያሉት ዶክተር ካሳሁን፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ውስጥ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ ታደርጋለች ሲሉ ገልጸዋል። እንዲሁም የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ለግል አልሚዎች ትልቅ የገበያ እድልን ይፈጥራል ሲሉ አስረድተዋል።
የዓለም ንግድን የምንቀላቀለው የግሉን ዘርፍ ይዘን ነው፣ የግሉ ዘርፍ አምራች፣ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆን ከማድረግ ረገድ መንግሥት የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው ያለው። ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ሚኒስትሩ።
እንደ ካሳሁን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሴክሬታሪያት 15ኛው የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ትልቅ እድል ነው። በኢትዮጵያ መልካም ገጽታና የተሰሩ ስራዎች ለማስጐብኝት እድል የሰጠ ነው። ከሰሞኑን አዲስ አበባ በብዙ የውጭ ዜጐች የተጎበኘችበት ነው።
የተጠናቀቀው የአፍሪካ 15ኛው የንግድ ሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የቀረቡ ውሳኔዎችን አጽድቋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም