ድህረ ምርት ብክነት- የምግብ ዋስትና ስጋት

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) በኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ምርት እንደሚባክን አሳውቋል።

ምርቱ የሚባክነው ድህረ ምርት ስብሰባ መሆኑን ጠቅሶ፤ ምርት በመሰብሰብ፣ በማድረቅ እና በማከማቸት ላይ መሆኑን ነው ያሚያስረዳው። እነዚህ ኪሳራዎች በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አላቸው።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአግሮ ኢኮኖሚስት መምህር አሰፋ ጥላሁን (ዶ/ር)፤ የሕዝብ ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የምግብ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ያነሳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የምርት ብክነት በቂ የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያበላሻል ይላሉ።

የምርት ብክነት የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ከመጉዳቱም ባሻገር በአርሶ አደሩና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያስከትላል ይላሉ።

የዘመናዊ መሠረተ ልማት እጦት በተለይ በገጠር አካባቢዎች ዘመናዊ የማከማቻ ቦታ አለመኖሩ የድህረ ምርት ብክነት አንዱ መንስዔ ነው ያሉት አሰፋ (ዶ/ር)፤ ይህም ምርት ለብልሽት እና ለተባዮች ተጋላጭ እንዲሆን ያደርጋል ነው ያሉት።

ምርትን በባህላዊ መንገድ መሰብሰብ ለጉዳትና ለምርት መጥፋት ይዳርጋል። ደረጃውን ያልጠበቀ ግብአትም የሰብል ምርትንና ጥራትን ይቀንሳል ያሉት አሰፋ ጥላሁን(ዶ/ር)፤ በሀገሪቱ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ሌላኛው የምርት ብክነት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ድርቅና ጎርፍ ያሉ አስከፊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች የግብርና ምርትን ሊያውኩ እና የድህረ ምርትን ብክነት ሊያባብሱ ይችላሉ ሲሉም ያነሳሉ። ስለዚህ የምርት ብክነትን ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መተባበር አለባቸው ሲሉም ጠቁመዋል።

ዘመናዊ የምርት ማከማቻን መገንባት እና የትራንስፖርት አውታሮችን ማሻሻል ከምርት በኋላ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመቀነስ ያስችላል። አርሶ አደሮችን በእውቀትና በክህሎት ማብቃት አሠራራቸውን በማሻሻል የምርት ብክነትን መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት።

ጠንካራ የእሴት ሰንሰለቶች መዘርጋት ገበሬዎች ለምርታቸው ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ በድህረ ምርት የሚደርሰውን ኪሳራ እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል።

ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያ ከምርት በኋላ የሚደርሰውን ኪሳራ በእጅጉ በመቀነስ የሕዝቦቿን የምግብ ዋስትና ማሻሻል ትችላለች የሚሉት ዶክተር አሰፋ፤ ይህ ደግሞ ከመንግሥት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የድህረ ምርት ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉጌታ ተዓምር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመንግሥት ዋና ትኩረት የግብርና ምርቶችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ መሆኑን ያነሳሉ። ነገር ግን ከቅድመ ምርት አሠራሮች ጋር ሲነፃፀር ለድህረ ምርት አስተዳደር የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው ይላሉ።

ለድህረ ምርት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና መመሪያዎች ቴክኒካል ተስማሚነትን፣ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትን፣ ማህበራዊ ተቀባይነትን እና የአካባቢን ዘላቂነት ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው ያሉት ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ በክልል የተመረቱ የተለያዩ የግብርና ምርቶች ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ወይም ክልሎች አካባቢዎች ወደ መዲናዋ እስኪደርሱ ድረስ እስከ 50 በመቶ እንደሚባክኑ ይገልጻሉ።

በእህል ምርቶች እስከ 30 በመቶ፤ በአትክልት እና በፍራፍሬ ምርቶች ደግሞ እስከ 50 በመቶ ድረስ የምርት ብክነት ይፈጠራል ያሉት ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ እየባከነ የሚገኘው የግብርና ምርትም በርካታ ኢትዮጵያን መመገብ የሚችል መሆኑን ይናገራሉ።

ለዚህ ደግሞ የግብርና ምርቶችን ለመሰብሰብ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አለመጠቀም፣ የሎጅስቲክስ ችግር እና በሀገሪቱ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ዋና ምክንያቶች ናቸው ነው ያሉት።

የምርት ብክነት ለምግብ ዋስትናው ከፍተኛ ስጋት መሆኑን በመጥቀስ፤ መንግሥት በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ ዘላቂ አሠራሮችን ማስተዋወቅ እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ፡፡

የእሴት ሰንሰለቶችን በማጠናከር የግብርና ዘርፉን ተግዳሮቶች መፍታት ላይ መንግሥት ማተኮር እንደሚኖርበት ጠቁመው፤ በዚህም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ይገልጻሉ።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን  ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You