በከተሞች የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ሥራ በገጠሮችም ለማከናወን መታቀዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስረዱት፤ የገጠር ኮሪደር ማለት የእያንዳንዱን አርሶ አደር ቤት እና የአኗኗር ዘዬ መቀየር እና በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየር እንደ ሀገር የታሰበውን ብልጽግና ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
የገጠር ኮሪደር ልማት ምን ሊመስል ይችላል የሚለውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በምስል ሲያስተላልፉ ከተጠቀሟቸው ምስሎች ደግሞ አንዱና ዋነኛው በጉራጌ አካባቢ የሚገኙ ባህላዊ አሠራሮች ታዋቂው የጀፎረ መንገድ ይገኝበታል።
የባህል ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ጎይቴ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ጀፎረ በመባል የሚጠራ አውራ ጎዳና በጉራጌ አካባቢ የውበትና የንጽህና መገለጫ መሆኑን ያስረዳሉ።
ጀፎረ የጉራጌ ምድር መለያው፣ መታወቂያውና መገለጫ ቅርሱ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ በግራና በቀኝ በትይዩ በሚገኙ መንደሮች መካከል ለጥ ብለው የሚታዩ፣ እንደዘመናዊ ከተማ በአርኪቴክቸር ሳይሆን ሲሚንቶና አሸዋ ሳይጎበኛቸው በባሕላዊ የምህንድስና ጥበብ የተሠሩ ውብና ማራኪ ጥንታዊ አረንጓዴ መንደሮች በሁሉም የጉራጌ ወረዳዎች ውስጥ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ።
እያንዳንዱ ጀፎረ መቼ እንደተመሰረተ በውል ባይታወቅም ከመኖሪያ መንደሮቹ ጋር አብሮ እንደተመሰረተ ግን ይነገራል ይላሉ፡፡ ጀፎረ በየቅጥር ግቢዎቹ ውስጥ ሶስት አይነት (ጒየ፣ ሐራር እና ዘገር የሚባሉ) የሳር ክዳን ቤቶች ተመሳጥረው በረድፍ በሚታዩባቸው ሰፈሮች መካከል ቀጥ ብሎ የሚያልፍ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
ኮረብታ፣ ወንዝ፣ ሸለቆ፣ ገደላገደል፣ ጫካ፣ ወዘተ ቢያጋጥመው የማይቋረጥ ወደ ግራ ወይንም ወደ ቀኝ ታጥፎ እንደገና ስሙንና መልኩን ይዞ የሚቀጥል መሆኑንም በጽሑፋቸው ያነሳሉ። ከአንድ መንደር ተነስቶ ወደሌሎች መንደሮች የሚዘልቅ፣ ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ፣ ሄዶ ሄዶ የማይደክመው፣ ርዝመቱ ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ የማይታወቅ ነው ይላሉ፡፡
ወንዝ ካጋጠመው፣ ተራራ ከተጋረጠበት፣ ሸለቆ እንቅፋት ከሆነበት እነዚህን ሁሉ በጎን አልፎ በጀመረው ዓይነት የሚዘልቅ፣ ሙሉውን ለምለም ሳር የለበሰ፣ ደልዳላ፣ በየመካከሉ የዝግባ፣ የዋርካ፣ የሾላ፣ የሃበሻ ጽድ የመሳሰሉ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች የሚታዩበት ሰፊ የገጠር አውራ ጎዳና ነው፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት፤ ጀፎረ በጣም ፅዱና ለአይን የሚማርክ ነው፡፡ በጥንት ጊዜ የጎን ስፋቱ ከ12 ዘንግ በላይ እንደነበር ይነገራልም። በአንዳንድ ሰፈሮች ውስጥ ስፋቱ በተለያዩ ምክንያቶች እየጠበበ ቢመጣም በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ከ40 እስከ 50 ሜትር ያህል የጎን ስፋት ያላቸው ጀፎረዎች በተለያዩ መንደሮች ውስጥ መኖራቸውን በጽሑፋቸው ያብራራሉ።
በተጨማሪም ጀፎረ የአንድ ሰፈር፣ ጎሳ፣ መለያ ብቻ ሳይሆን እንደማናቸውም ቅርሶቻችን የሀገራችን አኩሪ ቅርስ እንደመሆኑ ይህንን በልዩነት የሚታየውን ቅርሳችንን ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ እንደ ሀገርም ትርጉም ያለው ጥረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው፤ ጀፎረ በሀገር በቀል እውቀትና ጥበብ ስፋቱ ተለክቶ የተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ርዝመቱ ግን ተወስኖ የማይቀመጥ መሆኑን ያስረዳሉ።
የገጠር ኮሪደር ተምሳሌት የሆነው ጀፎረ በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉት የሚገልጹት ኃላፊዋ፤ ባህላዊ ዳኝነት፣ የእናቶች ቀን፣ የልጃገረዶች ቀን፣ የተለያዩ በዓላት፣ የፈረስ ጉግስ፣ የደመራ ሥነሥርዓት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ኩነቶች እንደሚካሄዱበት ነው ያስታወቁት፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ እንደዝግባ፣ ጽድና ሌሎችም ሀገር በቀል የሆኑ ዛፎችን እንደጥላ ለመጠቀምና ለማስዋብ የሚሆኑ ነገሮችን ይተክላል። ከዚህ ባሻገር ግን ማንኛውም ሰው የኔ ነው በሚል አጥሩን ገፋ አድርጎ ቢያጥር፣ የጀፎረ መንገዱን ቢያጠብ፣ የተለያዩ ችግኝና ሰብሎችን አምርቶ ቢጠቀም፣ ባልተገባ መንገድ ቢቆፍር በማህበረሰቡ የዳኝነት ሥርዓት መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ፡፡
ከወልቂጤ ወደ ቡታጅራ የሚወስድ ወደ 80 ኪሎ ሜትር የሚሆን አስፓልት ሲሰራ አንድም ቤትና ቋሚ ንብረት እንዳልተነሳና ካሳ እንዳልተከፈለ ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ ማህበረሰቡ ቀድሞ ገብቶት የቀየሰው የጀፎረ መንገድ በመኖሩ አስፓልቱ እንደተገነባና ከመንገዱ ዳር ለእግረኛ እና ለእንስሳት የሚሆን መሬት ጭምር እንዳለም ጭምር ይጠቁማሉ።
በክረምት ጊዜ ባለሀብቶች መኪና ይዞ ለመግባት ሲሉ ጀፎረውን ጠጠር የማልበስና የነበረውን ገፅታ የመቀየር፣ አጥሩን በቆርቆሮና በብሎኬት የማጠር የመሳሰሉት ነገሮች ግን ቀሪ ሥራዎችን የሚጠይቁ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
የገጠር ኮሪደር ምሳሌ የሆነውን ጀፎረ ማስፋፋትና መጠበቅ እንደሚገባም አንስተው፤ የገጠር ኮሪደር ልማቱ ፅዱ አካባቢን መፍጠር፣ በኢኮኖሚ የተሻለ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፣ አጥሩ በቆርቆሮ ሳይሆን በቀርከሀ የሆነ፣ ከቤቱ ጓሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ የሚተክልና የእንስሳት ተዋፅኦ እና የዶሮ እርባታን አቀናጅቶ የያዘ መሆኑን አስታውሰዋል።
አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር አብዛኛውን ጊዜ በዞኑ ከብቶችና ሰዎች በአንድ ቤት እንደማያድሩም ጠቅሰዋል፡፡
እንደባህል ቱሪዝም ቢሮ መሰረተ ልማቶች ጀፎረውን በማያበላሽ መልኩ የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ የማድረግ ስራዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው ነው ያወሱት።
የቱሪዝም አቅም መሆን የሚችል ከመሆኑ አኳያም የቱሪስት መዳረሻ ተሰርቶለት ቢጎበኝ ተጨማሪ ገቢ መፍጠር እንደሚያስችል ይገልጻሉ።
ጀፎረ በዓለም አቀፍ ደረጃም እንደቅርስ እንዲመዘገብ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፤ የገጠር ኮሪደሩን በተለያዩ አካባቢዎች በማስፋፋት ምቹና ለኑሩ ተስማሚ የሆነ አካባቢን መፍጠር እንደሚገባም ያስረዳሉ።
በተጨማሪ የገጠር ቤቶች እንደከተማ በፕላን ካለመሰራታቸው አኳያ በዞኑ የሚታየው በምህንድስና የተሰራ የሚመስል ዲዛይን ጥልቅ ጥናትና ምርምር ይፈልጋል ይላሉ፡፡
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም