– ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን 45 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር ደርሷል
አዲስ አበባ፡– ወጋገን ባንክ አጠቃላይ ሀብቱ 65 ነጥብ 7 ቢሊዮን መድረሱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን 45 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተመላክቷል።
የወጋገን ባንክ አክሲዮን ማህበር 31ኛ መደበኛና 15ኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዱሽ ሁሴን የባንኩን የ2023/24 ዓመታዊ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ወጋገን ባንክ ከታክስ በፊት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ከታክስ በኋላ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል።
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 52 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር ደርሷል ያሉት ሰብሳቢው፤ የባንኩ ከወለድ ነጻ ተቀማጭ ገንዘብም 2 ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል።
ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን 45 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰው፤ 12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብድር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 305 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን በመግለጽ፤ በአለፈው ዓመት ከተገኘው የውጪ ምንዛሬ መጠን 27 በመቶ እድገት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 65 ነጥብ 7 ቢሊዮን ደርሷል ያሉት ሰብሳቢው፤ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታልም 9 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል።
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰው፤ ባንኩ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊደርስበት ካቀደው 20 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አንጻር ዝቅተኛ በመሆኑ የባንኩን ካፒታል ለማሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዓመቱ ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች 9 ነጥብ 8 ቢሊዮን አጠቃላይ ገቢ ማስመዝገብ መቻሉን በመግለጽ፤ ከአጠቃላይ የባንኩ ገቢ ውስጥ የወለድ ገቢ 69 በመቶ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።
ባንኩ በካፒታል ማሳደግ፣ ሀብት ማሰባሰብ፣ በውጪ ምንዛሬ ግኝት፣ በብድር አሰባሰብና በሌሎች መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የደንበኞችን እርካታ የበለጠ በማሳደግ፣ ተደራሽነቱን በማስፋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም