የፍራንኮ ቫሉታው ውጤት ፍተሻና የውሳኔው ተገቢነት

ፍራንኮ ቫሉታ /Franco- Valuta/ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ሲሆን የባንክ ቤት ፈቃድ (Bank Permit) ሳያስፈልገው ከውጪ ሀገር ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል ፈቃድ ነው። የፍራንኮ ቫሉታ መብት ያላቸው አስመጪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቧቸው ምርቶች የውጪ ምንዛሪን በተመለከተ በብሔራዊ ባንክ የወጡ እና በንግድ ባንኮች የሚተገበሩ ጥብቅ መመሪያዎችን የማለፍ ግዴታ የለባቸውም። ይህም ማለት የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት የባንክ ቤቶች ፍቃድ ሳያስፈልገው በፍራንኮ ቫሉታ የሚገቡ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት መብት ያገኛል ማለት ነው።

በኢትዮጵያ ያለምንም የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ምርቶችን ማስገባት በተለይ የገቢ ንግድን ለማሻሻል እና ለማረጋጋት በተለያዩ ጊዜያት ሲፈቀድ ተመልሶም ሲከለከል ቆይቷል። የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሑራን እንደሚያስረዱት ከሆነም፣ ፍራንኮ ቫሉታ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በተለይ የሀገር ኢኮኖሚ ሲንገጫገጭና ግሽበት ሲከሰት ዋጋን ከማረጋጋት አንፃር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።

ፍራንኮ ቫሉታ በተለይም የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና የምርት አቅርቦትን ለመጨመር ይረዳል። የሀገር ውስጥ ፍላጎትና አቅርቦትም አለመመጣጠን በማስተካከል፤ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የምርት እጥረትን ለመቅረፍ ጊዜያዊም ቢሆን ጥሩ መፍትሔ ተደርጎ የሚታይ ነው።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓመት በፊት በተለይ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን ያለውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲቻልና ፍራንኮ ቫሉታን መፍቀዱ የሚታወስ ነው። መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ያለውጭ ምንዛሪ ሸቀጦችን የማስገባት አሠራር መፈቀዱ በሀገሪቱ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ከዚህም በከፋ መልኩ እንዳይሰቀል ትልቅ አቅም መፍጠሩም የሚካድ አይደለም። በትግበራ ሂደትም መንግሥት ማግኘት የነበረበትን ከፍተኛ ገቢ ማጣት ግድ ብሎታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመት በፊት ለምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከልም ፍራንኮ ቫሉታ ጉዳይ አንደኛው ነው። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንዲቻል በወሰነው ፍራንኮ ቫሉታ 10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እየቻለ ማጣቱን መጠቆማቸውም የሚታወስ ነው።

በእርግጥም ፍራንኮ ቫሉታ አማራጭ መፍትሔ ከመሆኑ ባሻገር የራሱ የሆኑ ፈተናዎችን ይዞ ይመጣል። የፍራንኮ ቫሉታ ተግባራዊ በሆነባቸው ሀገራት ሆነ የምጣኔ ሃብት ምሑራኑ ሲያስረዱ እንደሚታየው፣ እንደሚደመጠው፣ የፍራንኮ ቫሉታ ተግባር ከፍተኛ ጥንቃቄን የግድ የሚል ነው። የፈቃዱን ዓላማ ለማሳካት ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማዳበር የሚፈልጉ ግለሰቦች ያላግባብ እንዳይጠቀሙበት ሂደቱ በጥብቅ ሥነ ምግባር ሊመራ ይገባል።

ከሁሉ በላይ ጠንካራ ቁጥጥር እጅግ ወሳኝ ነው። በትግበራ ወቅት ከቁጥጥር ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ ድክመቶችና በሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራት ሀገር የሚያስፈልጋትና ወደ ሀገር የሚገባው የተለያየ ሊሆን ይችላል። ተጠቃሚዎቹ እንጂ አገር የምትፈልገው ላይገባም የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ነው።

ተጠቃሚዎቹ ትርፍን ብቻ ታሳቢ በማድረግ የሚፈልጉትን ምርት ወደ ሀገር ውስጥ አስገቡ ማለት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሀገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል። ገበያ ላይ ያሉ በተለይ በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉት ሳይቀር በዝቅተኛ ዋጋ የሚገቡ ከሆነ ደግሞ የአገር ውስጥ አምራቾችን ያደቃል። በማደግ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችን ያቀጭጫል።

ፍንራኮ ቫሉታ፣ በተለይ በተለይ የጥቁር ገበያን በማስፋፋት ረገድ ከባድ ተፅዕኖ እንዳለውም እሙን ነው። ከሁሉ በላይ በወንጀል የተገኘ ገንዘብንም በእግረ መንገድ ሕጋዊ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል። አሠራሩ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ግለሰቦች በትይዩ ገበያ ገዝተው ያስቀመጡትን ወይም ያጠራቀሙትን የውጭ ምንዛሪ የሚያጥቡበት ወይም ሕጋዊ የሚያደርጉበት ሁኔታን ሊያመቻች ይችላል።

መሰል ችግሮችን ለመሻገር ከትርፉም በላይ ኪሳራን ለመራቅ በፈቃዱ ምን ውጤቱ ታይቷል? ገበያውስ ተረጋግቷል? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ በየጊዜው መቃኘት የግድ ይላል። አፈፃፀሙንም በየጊዜው በመከታተል የተፈለገውን ውጤት አምጥቷል፣ አላመጣም፣ የሚለውን መገምገም የግድ ነው። ከዚህ ባሻገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች መንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው ናቸው? አይደሉም የሚለውን መፈተሽም ተገቢ ነው።

ከዚህም ከፍ ሲል ውጤቱ እየታየ ማሻሻያዎች ካስፈለግ ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ የፍራንኮ ቫሉታን አተገባበር መንግሥት እየፈተሸው መሆኑን አሳውቀው ነበር።

‹‹ባለፉት ጥቂት ወራት ከሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ከወሰናቸው አብረው ከማይሄዱ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ ፍራንኮ ቫሉታ ነው። ያን የወሰንበት ምክንያት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነበሩን። አንደኛው በውጭ ያለ ሀብት ከዚህ ቀደም የሸሸ ወደ ሀገር ውስጥ መምጣት የሚችል ከሆነ ዕድል ለመስጠት ሁለተኛ ባንኮቻችን አሁን በጀመርንው ኢኮኖሚክ ኦፕን አፕ በቂ ልምምድ እስኪያደርጉ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች እንዳያንሱ እና የኑሮ ውድነትን እንዳያባብሱ ጉዳት ቢኖረውም ከፈት እናድርግ የሚል እሳቤ ነበረን። ያየነው ውጤት ከዚህ በላይ መሸከም ተገቢ እንዳልሆነ የሚያሳይ በመሆኑ በቅርቡ ፍራንኮ ቫሉታን በሚመለከት ማስተካከያ እንደሚደረግ ይጠበቃል›› ነው ያሉት።

ይህን ተከትሎም መንግሥት የፍራንኮ ቫሉታ ትግበራውን በመፈተሽ መሻሻል የሚገቡ ብሎም መለወጥ ያለባቸውን ጉዳዮች በመገምገም የለውጥ እርምጃን ተከትሏል። በተለይ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባታ የፍራንኮ ቫሉታውን አጠቃላይ መልክ የሚቀይር እንደመሆኑ ለውጥ ማድረግ የግድ ነው። በዚህ አግባብ የፍራንኮ ቫሉታው ውጤት ተፈትሾ የተላለፈው ውሳኔም ተገቢነት ያለው ነው።

መታወቅ ያለበት ወሳኝ እውነት ቢኖር ፍራንኮ ቫሉታ በተወሰነ ጊዜ የተወሰነ ችግር እንዲፈታ እንጂ ለረጅም ጊዜ የሚሆን መፍትሔ አለመሆኑ፣ ጊዜያዊና ችግሮቹ ይበልጥ እንዳይባባሱ ማድረግን ታሳቢ ያደረገና ለአጭር ጊዜ የሚሆን ማስተንፈሻ መሆኑ ነው። በተለይ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በአጭር ጊዜ እንጂ በዘለቂነት መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም። መንግሥት የትግበራውን አጠቃላይ ውጤትን መዝኖ ሊስተካከል ይገባል ማለቱም ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው።

ይሁንና ከመሰል ውሳኔዎች ባሻገር በተለይ ከእለት እለት እየተባባሰ የመጣውን ዋጋ ግሽበት ፈር ለማስያዝ ዘላቂው መፍትሔ የሀገሪቱን መዋቅራዊ ኢኮኖሚ ዑደት ማስተካከል መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በተለይ ፍላጎትና አቅርቦት ምጥጥን ልዩነቱን ለማስተካከል ሀገር ውስጥ በተሻለ ማምረት የሚችልበትን መንገድ መቀየስና ለዚህ ተግባራዊነትም ሌት ተቀን መትጋት የግድ ይላል።

በተለይም ከሠላም እና ፀጥታ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች ፈጣን እልባት መስጠት፣ ሎጂስቲክስና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ በቋሚነት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግና ከውስጥ ፍላጎት አልፎም የውጭ ምንዛሪ ማስገባት የሚያስችሉ ዋና ዋና ምርቶችን በስፋት በሀገር ውስጥ ማምረት ብሎም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ታሳቢ ማድረግ ይገባል።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/ 2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You