በ2024 የአፍሪካ ሴት ክለቦች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ነገ ከናይጄሪያው ኤዶ ኩዊንስ ጋር ያደርጋል። ክለቡ በሳምንቱ አጋማሽ የሀገር ቤት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ 21 ተጫዋቾችን አካቶ ወደ ውድድሩ ስፍራ አቅንቷል፡፡
የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በሞሮኮ ካዛብላንካና እንዲሁም ከዚህች ከተማ በ96 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ኤል ጃዲዳ የወደብ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ኅዳር 14/2017 ዓ.ም ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ተወካዩ ንግድ ባንክ በታሪኩ የመጀመሪያ ተሳትፎውንና የመጀመሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። ውድድሮቹ በላርቢ ዛኦዩሊ ስታድየም ካዛብላንካ እና ቤን ኤም መሀመድ ኤል- አዳዲ ስታድየም ይካሄዳሉ፡፡
ንግድ ባንክ ባለፈው ነሐሴ ወር በኢትዮጵያ የተካሄደውን የምሥራቅ አፍሪካ ዞን የካፍ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪ ውድድርን በማሸነፍ የመጀመሪያ የመድረኩን ተሳትፎ ማረጋገጡ የሚታወስ ነው። በቻምፒዮንስ ሊጉ ከየዞኑ ቻምፒዮን የሆኑ ስድስት ቡድኖችንና የአዘጋጅ ሀገር አንድ ክለብ እንዲሁም የአምና የመድረኩ ቻምፒዮን ክለብን ጨምሮ ስምንት ክለቦች ይፎካከራሉ፡፡
ስምንቱ ክለቦች በሁለት ምድቦች ተከፍለው በሚያካሂዱት አህጉራዊ ውድድር ንግድ ባንክ የመጀመሪያውን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ምሽት 2 ሰዓት ከናይጄሪያው ኤዶ ክዊንስ ክለብ በማድረግ ይጀምራል። በምድብ ሁለት ከጠንካራ የአህጉሪቱ ክለቦች የተደለደለው ንግድ ባንክ ከናይጄሪያው ክለብ ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። ውድድሩ ዛሬ በምድብ አንድ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች የሚጀምር ሲሆን፤ ነገም እንዲሁ ሁለት ጨዋታዎችን በማድረግ ይቀጥላል። የዲሞክራቲክ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ ከደቡብ አፍሪካው ዩደብሊዩሲ ክለብ እና የሞሮኮው ኤኤስ ፋር ከሴኔጋሉ ኢግልስ ዴ ላ መዲና ክለብ የዛሬ ጨዋታዎች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ናይጄሪያው ኤዶ ክዊንስ እና ማሜሎዲ ሰንዳወንስ ከኤፍ ማሳር ነገ የሚካሄዱ ጨዋታዎች ናቸው።
ንግድ ባንክ በሀገር ቤት ረዘም ያለ ዝግጅት በማድረግ ከቀናት በፊት ወደ ውድድሩ ስፍራ ያቀና ሲሆን 21 ተጫዋቾችን በስብስቡ ማካተት ችሏል። የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታ ከጠንካራውና የአምና አሸናፊው ማሜሎዲ ሰንዳወንስ በመጪው ሃሙስ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል። ሶስተኛውን እና የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ የነገ ሳምንት ከግብፁ ክለብ ማሳር ጋር የሚያደርግም ይሆናል፡፡
የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፣ ከአፍሪካ ምርጥ የሴት ቡድኖች ጋር የሚደረገው ውድድር ከባድና ፈታኝ እንደሆነና ውድድሩ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ በመምጣቱ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ከካፍ ኦላይን ድረ-ገጽ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስተያየት ሰጥተዋል። የአፍሪካ እግር ኳስ ቡድኖች ጠንካሮች እንዲሁም ጎል ለማስቆጠር ረጃጅም ኳሶችን የሚጠቀሙ በመሆኑ፣ ኳስን መሰረት ያደረግ አጨዋወትን ይዞ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
በውድድሩ የሚሳተፉ 8ቱ የሴት ክለቦች እያንዳንዳቸው 150 ሺ ዶላርን የሚያገኙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁ በተሳትፎ ብቻ ይህን ገንዘብ ወደ ካዝናው የሚያስገባ ይሆናል። የካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እኤአ በ2021 የተጀመረ ሲሆን፤ አሁን የሽልማት ገንዘብ መጠኑን 52 በመቶ በማሳደግ ወደ 2 ሚሊዮን 350 ሺ ዶላር ከፍ ማድረጉ ተገልጿል። የውድድሩ አሸናፊ ክለብ 600 ሺ የአሜሪካን ዶላር ሲበረከት ይሄ በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስን ለማሳደግ እና የካፍ ውድድሮች የሽልማት ገንዘብን በመጨመር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሆነ ተመላክቷል። በዚህም 2 ኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቅ የሴት ክለብ 400 ሺ ዶላር፣ 3ኛ ደረጃ 350 ሺ ዶላር፣ 4ኛ ደረጃ 300 ሺ ዶላር፤ የምድብ 3ኛ 200 ሺ ዶላር እና የምድብ 4 ኛ ክለብ 150 ሺ ዶላር ያገኛል፡፡
በውድድሩ የሴካፋ ቻምፒዮኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ፣ ኤዶ ኩዊንስ እና ኤፍሲ ማሳር በምድብ ሁለት የተደለደሉ ሲሆን፣ ቲፒ ማዜምቤ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስተርን ኬፕ፣ ኤግልስ ዴ ላ መዲና እና ኤ ኤስ ፋር በምድብ አንድ የተደለደሉ ክለቦች ናቸው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች ውድድሩን ያሸነፉት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና የአዘጋጅዋ ሀገር ክለብ የሆነው እንዲሁም ከዚህ ቀደም ውድድሩን ያሸነፉት ኤ ኤስ ፋር ለአሸናፊነት ቅድመ ግምት ያገኙ ክለቦች ሆነዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም