ኢትዮጵያ በተለይ ካለፈው ዓመት ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ እያከናወነች ባለችው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ የመኖሪያና የመሥሪያ ከተማ፣ ጎብኚዎችንና እንግዶችን የምትስብ ከማድረግ አኳያ ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች። የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው ልማት ከተማይቱ እንደስሟ ውብ እና ማራኪ ከማድረግ በዘለለ ሃገሪቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ ለቱሪዝም ተመራጭ ከሆኑ ከተሞች አንዷ እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም።
የከተማዋን መልማት ነዋሪዎቿም ለዘመናት ሲመኙትና ሲናፍቁት የነበረ ጉዳይ በመሆኑ በፍፁም ቅንነት ለልማቱ ስኬት አጋርነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ። በከተማይቱ እየታየ ያለው ፈጣንና ማራኪ የልማት ሥራ ተጠናቆ ለማየት ከመጓጓት ባለፈ ከኖሩበት ቀዬ በመነሳታቸውም ሆነ በልማት ሥራው በመንገድ ላይ በሚፈጠሩ መጨናነቆች ምንም አይነት ቅሬታ አላሰሙም። ይልቁንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከመንግሥት ጎን በመቆም ልማቱ በሁሉም የከተማዋ መንደሮች ዘልቆ እንዲገባ እየጎተጎቱ ይገኛሉ።
አብዛኞቻችን የከተማዋ ነዋሪዎች እንደምናውቀው የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ ለጥቂት ጊዜያት ቢሆን በተለይ ዋና ዋና የሚባሉ የከተማዋ መንገዶች በመዘጋታቸው አሽከርካሪዎች ተለዋጭ መንገዶችን ለመጠቀም ተገደው እንደነበር ይታወሳል። በዚህ ምክንያትም በተለይም የታክሲ አሽከርካሪዎች በነባሩ ታሪፍ ላይ በእጥፍ ዋጋ በመጨመር አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ነዋሪው ልማቱ ቶሎ እንዲጠናቀቅ ካለው ፍላጎት በመነጨ የታክሲ አሽከርካሪዎች በሚያደርጉት አላግባብ የታሪፍ ጭማሪም ያልተገባ መንገድ ማቆራረጥ እምብዛም አላጉረመረመም።
በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ዋና ዋና መንገዶች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ቀድሞ አገልግሎታቸው ቢመለሱም በተለይ ታፔላ ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ታክሲዎች አሽከርካሪዎች ወደ መስመሩ ሙሉ ለሙሉ ገብተው በአግባቡ መሥራት ሲገባቸው ሕዝቡን እያንገላቱ ይገኛሉ። ከተመደበው ታሪፍ በላይ ከማስከፈላቸውም ባሻገር ዋናውን መስመር በመተው እና አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም ተሳፋሪውን በማይፈልገው መስመር በማጓጓዝና ካሰበበት ሳይደርስ እንዲወርድ በማድረግ ሲያማርሩት ይስተዋላሉ።
ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ ከመገናኛ-ቀበና-አራት ኪሎ ፒያሳ የሚዘልቀውን መስመር ማንሳት ይቻላል። ለእዚህ መስመር ከኮሪደር ልማቱ በፊት ከመነሻ እስከ መዳረሻ ወይም ከመገናኛ እስከ ፒያሳ በይፋ የሚታወቀው ታሪፍ 13 ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሆኖ ግን 15 ብር ይከፈል እንደነበር አስታውሳለሁ።
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተወሰነው መንገድ በመዘጋቱና አሽከርካሪዎች የአዋሬን አስፋልት ለመጠቀም ተገደው በነበረበት ወቅት ስምንት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ተመድቦለት የነበረውን ታሪፍ ተሳፋሪው 10 ብር ይከፈልበት የነበረውና ከመገናኛ አራት ኪሎ መንገድ ፒያሳ ለሚዘልቀው እኩል 20 ብር እንዲከፍል ይጠየቅ ነበር። ይህም ቢሆን ተሳፋሪው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የተጠየቀውን ሲከፍል ቆይቷል፤ ምቹ ያልሆነና ራቅ ያለ ቦታ እንዲወርድ ሲጠየቅም የተባለውን ሲፈጽምም ነበር።
መንገዱ ተጠናቆ ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ ከተመለሰ በኋላም ግን አብዛኞቹ የታክሲ አሽከርካሪዎች ወደ ቀድሞው ታሪፍ ለመመለስ ፍቃደኝነታቸውን አላሳዩም። አቋራጩ መንገድ ሕዝብን ለማጭበርበር ይበልጥ አዋጭ ስለሆነላቸው በነበረው መስመር (ከመገናኛ ቀበና አራት ኪሎ ፒያሳ) ለመሄድ አይሹም።
በዚህ ምክንያት በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለሰዓታት ታክሲ ጥበቃ ይንከራተታሉ፤ በትከክለኛው መስመር ለመሄድ አንድ ፈቃደኛ የሆነ ታክሲ ሲመጣ ለመግባት በሚደረግ ግፊያ በተለይ አቅመ-ደካሞች፣ ነፍሰጡሮች እና ሕፃናት ወድቀው የሚጎዱበት ሁኔታንም ታዝቤያለሁ። ይህንን ተገን አድርጎ የሰው ኪስ የሚገባውም የመገናኛን ሌባ መኖሩን መቼም መናገር አይጠበቅብኝም!።
ይህንን ሁሉ ስቃይ አልፎ መግባት የቻለው ተሳፋሪም ቢሆን በተለይ አራት ኪሎን ተሻግሮ መውረድ የሚሻ ከሆነ ስቃዩ ገና አላበቃለትም። እንዴት? ካላችሁኝ ላስረዳችሁ፤ ነገሩ እንዲህ ነው፤ የዛሬ አጀንዳዬ ዋነኛ ርዕሰ-ጉዳይ የሆኑት እና ሃይ ባይ ያጡት የታክሲ አሽከርካሪዎች ከመገናኛ ተነስተው ልክ እንግሊዝ ኤምባሲ ጋ ሲደርሱ በአዋሬ መታጠፊያ ይታጠፉሉ፤ በገዛ ፍቃዳቸው መንገድ ቀይረው ተሳፋሪውን የረጅም ርቀት እንዲከፍል ያደርጉታል፡፡
እንግዲህ እዚህ ጋር ልብ ማለት የሚገባው ጉዳይ እነዚህ አሽከርካሪዎች ከተሰጣቸው ታፔላ ውጭ የሚሄዱ መሆኑ ነው። ከታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ ከመደረጉም በላይ ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ ተጠቃሚውን ማዕከል ባላደረገ መልኩ እነሱ በሚሹት ቦታ ብቻ ማውረዳቸው ነው።
ለዚህም ቀድሞ ባነሳሁት መስመር በተለይም አራት ኪሎ ተሻግሮ (ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ጋር) መዳረሻው የሆነ ተሳፋሪ ከታሪፍ በላይ እንዲከፍል ተደርጎም እነሱ እንዲመቻቸው ሲሉ አደባባዩን በመዞር እና አብሮኆት ቤተ-መጽሐፍት ጋ እንዲወርድ ያስገድዱታል።
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ አሽከርካሪው እና ረዳቱ ተሳፋሪውን ከሚጠበቀው በላይ ከፍሎም ረጅም ርቀት በእግሩ እንዲሄድ አድርገው ቅሬታ ቢያሰማ ስድብና ዘለፋ ገፋ ካለም ወደ መማታት የሚከጅላቸው ወቅት ያለ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ። እኔም አንዷ የገፈቱ ቀማሽ ነበርኩ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ያጋጠመኝን ልንግራችሁ እወዳለሁ፤ አንድ የሥራ ቀን እኔም ሆንኩ አስር ተሳፋሪዎች ከመገናኛ ወደ አራት ኪሎ ፒያሳ እንዲሄድ ታፔላ በተሰጠው ተሽከርካሪ በአንድ የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪ አስገዳጅነት ተሳፍረን ገባን። አራት ኪሎ (ሥላሴ ቤተክርስቲያን) ጋ ስንደርስ የአራት ኪሎ ተሳፋሪዎች ሁላችንም እንድንወርድ በረዳቱ ተጠየቅን፤ አንዳንዶቹ ተሳፋሪዎች ፈርተው ሲወርዱ እኔና አንድ ሌላ ተሳፋሪ መውረጃችን አልደረሰምና እንሻገራለን ብለን ቁጭ አልን።
‹‹ውረዱ!፤ አንወርድም!›› ጭቅጭቅ ተነሳ፤ በተለይ ረዳቱና ሌላኛው ተሳፋሪ አምቧጋራቸው በረታ፤ ተሳፋሪው ዋጋ እንደሚጨምርለት ቢነግረውም ረዳቱ ግን ፀያፍ ስድብ ማውረዱን ቀጠለ፤ ተው ቢባልም ለያዥ ለገራዥ አስቸገረ፤ እናም ልክ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስንደርስ የመኪናው በር እንደተከፈተ ተሳፋሪውና ረዳቱ ለድብድብ ተያያዙ፤ ሹፌሩም ከመገላገል ይልቅ ለረዳቱ ተደርቦ ለሁለት ተሳፋሪውን በቦክስና በእርግጫ አጣደፉት።
እኔም ሆንኩ ሌሎች ተሳፋሪዎች ለመገላገል ብንሞክርም የሚቻል አልሆነም፤ ሌሎች ተሳፋሪዎች፣ በተለይ ሸምገል ያሉ አንድ ሰው ሊገላግሉ እሳቸውም የዱላው ተቋዳሽ በመሆናቸው ጩኸትና ግርግሩ በረታ፤ ይሄን ጊዜ ብርሃንና ሠላም ማተሚያ በር ላይ የነበሩ ወታደሮች ሮጠው መጡ፤ እነሱ ባይመጡና አደብ ባያስጓዟቸው ኖሮ ይደርስ የነበረው አደጋ ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር!፡፡
እንግዲህ ይህንን ገጠመኝን አብነት አድርጌ አቀረብኩ እንጂ የዚህ መንገድ የዘወትር ተጠቃሚ የሆነ ሰው ከዚህም የባሰ ችግር እንደሚያጋጥመው አልጠራጠርም!። የአሽከርካሪዎችን ስምሪት የሚቆጣጠረው የመንግሥት አካልም ይህንን ችግር አላስተዋለም ብዬ አላምንም።
ምክንያቱም ደግሞ በተለይ መነሻ ላይ አሽከርካሪዎች የሕዝብ አገልጋይነታቸውን በመዘንጋት ለጥቅማቸው ብቻ ቆመው እነሱ ባሻቸው መስመር ብቻ ካልሄድን ብለው ከተቆጣጣሪው አካል ባልደረቦች ጋር የሚያደርጉት እሰጣ አገባ የየቀኑ ገጠመኝ በመሆኑ ነው።
ይህ ተቆጣጣሪ አካል አሽከርካሪዎችን በልልምጥና በማግባባት ብቻ እንዲጭኑ ከማድረግ ባሻገር የማስገደድ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በተለይ ለልማትና ለመሳሰሉት ሥራዎች ሲባል የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ አለአግባብ በመጠቀም ሕዝብን እያንገላቱና ላልተገባ ወጪ እያደረጉ ያሉ አሽከርካሪዎችን አደብ ሊያስገዛ ይገባል።
ይህን ሁል ስል ግን በታማኝነት በሕዝብና በመንግሥት የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሚወጡ ቅን አሽከርካሪዎች የሉም ማለት እንዳልሆነ እንድትረዱልኝ እሻለሁ!። በታፔላቸው የማይሠሩትም ሆነ እያቆራረጡ በመጫን አላግባብ ትርፍ የሚያግበሰብሱት፣ ሕዝብን ለእንግልትና ላልተገባ ወጪ የሚዳርጉት እነዚህ ሕገወጦች ‘ሃይ ባይ!’ ይሻሉ የሚል መልዕክቴን አስተላልፌያለሁ!።
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም