ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ- በማራቶን ከዋክብቱ አንደበት

ሃያ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ የ‹‹ሌብል›› ደረጃና እውቅና በሰጠው ማግስት ከትናንት በስቲያ 50 ሺ ሰዎችን ያሳተፈ ትልቅ ውድድር አካሂዶ በስኬት ማጠናቀቅ ችሏል። ይህም ለትልቁ የአፍሪካ የጎዳና ላይ ውድድር ድርብ-ድል ከማጎናጸፉ በላይ ውጤታማና ተተኪ አትሌቶችን የማፍራት የሚያደርገውን ጥረት የሚያጠናክርና ትልቅ አቅም እንደሚሆነው ታምኖበታል። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖና ከትልቅ የዓለማችን የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ እንዲሆን እንዳስቻለውም የወቅቱ የማራቶን ከዋክብት አትሌቶች መስክረውለታል።

በዘንድሮው ውድድር በክብር እንግድነት የተገኙት ኢትዮጵያዊው የወቅቱ የኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊ አትሌት ታምራት ቶላና ከወር በፊት የሴቶችን የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ያሻሻለችው ኬንያዊት አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ታላቅነት የመሰከሩ አትሌቶች ናቸው። ሁለቱ የወቅቱ የማራቶን ኮከቦች ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ‹‹ትልቅ ደረጃ ላይ መቀመጥ የሚችል፣ ወጣትና እውቅ አትሌቶችን የሚያፈራ ነው›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊው አትሌት ታምራት ቶላ፣ በ2008 ዓ.ም በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ላይ የተሳተፈ አትሌት ነበር። ውድድሩ በአሁኑ ወቅት ማደጉን እና የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሱን የተናገረው ታምራት፣ በመድረኩ የሚያሸንፉ አትሌቶች በኦሊምፒክና ዓለም

ቻምፒዮና ሀገርን የሚወክሉ በመሆኑ ትልቅ ውድድር እንደሚያሰኘው ጠቁሟል። ‹‹በዓለም አትሌቲክስ በቅርቡ የጎዳና ላይ ሌብል (Road label race) ደረጃ ማግኘቱ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል›› በማለትም የዓመቱ ከቤት ውጪ ውድድሮች ኮከብ አትሌቶች እጩ ተናግሯል።

እንደ ታምራት አስተያየት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያሳትፋቸውን ሰዓት ለማሟላት ውጪ ሀገር ሄደው የሚወዳደሩበትን ሁኔታ የማስቀረት አቅም አለው። ከተለያዩ ዓለማት ትልልቅ አትሌቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሚሳተፉበትን እድልም ይፈጥራል። ይህም ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች አቋማቸውን በሀገራቸው ለመፈተሽና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመወዳደር በር ይከፍታል። ሀገርን ወክለው ተፎካካሪና ሜዳሊያ የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን ለማፍራትም ጥሩ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብሏል።

ታላቁ ሩጫ የስኬታማ የአትሌቲክስ ጉዞው መነሻ መሆኑን የሚያስታውሰው አትሌት ታምራት፣ መጀመሪያ በታላቁ ሩጫ አሸንፎ በኦሊምፒክና ዓለም ቻምፒዮና ሀገሩን መወከል እንደቻለ ይናገራል። የሴቶች የዓለም ማራቶን ክብረወሰንን ያሻሻለችው አትሌትና ሌሎች ታላላቅ አትሌቶችም በክብር እንግድነት እንዲሁም ለተሳትፎ መምጣታቸው ወጣትና ጥሩ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ጠቅሷል።

ኬንያዊቷ የወቅቱ የማራቶን ክብረወሰን ባለቤት ሩት ቼፕንጌቲች ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ

በኢትዮጵያ ውድድር የክብር እንግዳ ሆናለች። አትሌቷ ከልጅነቷ ጀምሮ ትልልቅ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ልምምድ ሲሰሩና ውድድሮችን ሲያደርጉ እያየች ማደጓን አሁን ላይ ክብረወሰን እንድታሻሽል እንዳነሳሳት ተናግራለች። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ከሚካሄዱት ውድድሮች ትልቅ ደረጃ የሚሰጠውና ቀዳሚው እንደሆነም ገልጸለች። ሩት አጠቃላይ ውድድሩና የተሳተፊውን ሕዝብ ብዛት እንዳስደነቃት እንዲሁም ተፎካካሪ አትሌቶችን መመልከቷን ጠቁማለች። ውድድሩ የተቀናጀ፣ ወጥነት ያለው፣ መስተንግዶውም ጥሩ በመሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ትልልቅ አትሌቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲወዳደሩም መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ባለፈው የቺካጎ ማራቶን የዓለም የማራቶን ክብረወሰንን በእጇ በማስገባቷ ደስተኛ እንደሆነችና ሕልሟ እውን እንዳደረገችም ተናግራለች። በኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች መካካል የሚደረገው ፉክክር አስደሳች እንደሆነና ታዳጊ አትሌቶችን ለማፍራት እንደሚረዳም ጠቅሳለች። ወጣት አትሌቶች እንደ አትሌት ኃይሌ፣ ጥሩነሽ፣ መሠረት ውጤታማ ለመሆን ጥሩ ባህሪን ተላብሰው ጠንክረውና በርትተው መስራት ይጠበቅባቸዋልም ብላለች።

አትሌት ሩት ቼፕንጌቲች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ ስለመሆኗ እና ታላቁ ሩጫ እያሳያ ስላለው እድገት አስመልክቶ ዘገባ የሰራው የኬኒያው ኔሽን ጋዜጣ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም ካሉ ትልልቅ የሩጫ ውድድር ፌስቲቫሎች ለመመደብ በትክከለኛው ጎዳና ላይ ይገኛል ብሏል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም

Recommended For You