እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ የአዕምሮ ጤና ሲባል የራስን ማንነት አውቆ ራስን መምራት መቻል፣ ኃላፊነትን ማወቅና መወጣት፣ ምክንያታዊ ካልሆነ ጭንቀት ነፃ የሆነ ሕይወት መምራት፣ እንዲሁም ካሉበት ማኅበረሰብ ጋር በመግባባት ተግባርን ማከናወንና በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤን የመከተል ሁኔታን ያመለክታል።
ከዚህ በተቃራኒ በአዕምሮ ሕመም ክስተቶች ዙሪያ ሳይንሳዊ የሆነና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ትምህርት ያልተስፋፋ በመሆኑ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ስለ አእምሮ ሕመም ያለው ግንዛቤ በጣም አነስተኛና በባህል ሲወርዱ ሲወራረዱ በመጡ አባባሎች ላይ የተመሰረተ ነው።
የአእምሮ ሕመምን በተመለከተ ከሳይንሳዊ መረጃዎች ውጪ ያሉ የተለመዱ አባባሎች እንደሚያስቀምጡት ልክፍት ወይም ቁጣ ሳይሆን ማንኛውም የሰው አካል እንደሚታመም ሁሉ አእምሮም እንደሚታመም፤ በተለያዩ ምክንያቶችም መረበሽ እንደሚደርስበት የስነ አእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ይገልፃሉ። የአእምሮ ሕመም የእርኩስ መንፈስ ውጤት ሳይሆን እንደማንኛውም የሰውነት ሕመም በተወሰነ የክፍሉ አካል/አንጎል/ መታመም የተነሳ የሚፈጠር መሆኑንም ባለሞያዎች ይጠቁማሉ። ይህም በአብዛኛው እርስ በእርስ ሰላም ማጣት፣ ካለመከባበርና ካለመተባበር ጋር እንደሚያያዝም ያስቀምጣሉ። የአዕምሮ ሕመም እንደማንኛውም የአካል ሕመም በሕክምና ሊድን የሚችል መሆኑንም ያስረዳሉ።
አእምሮን ጤነኛ ወይም ሕመምተኛ ብሎ ለመፈረጅ የሚያስችል መስፈርት ወይም መመዘኛ ግልፅ በሆነና ሁሉም ሰው ሊስማማበት በሚችል መልኩ የተቀመጠ አይደለም። የአንድ ሰው አእምሮ ጤነኛ ወይም ሕመምተኛ ለማለትና ለመገምገም እንደሕብረተሰቡና እንደየአካባቢው ባህልና ግንዛቤ እንደሚወሰን የሕክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ። በዚህም የአንድ ሰው አእምሮ ጤነኛ አይደለም ለማለት ከሚያስችሉ አጠቃላይ መስፈርቶች ከሚከተሉት አንዱ ወይም ከአንድ በላይ ሲኖረው እንደሆነ አብዛኛዎቹ ምሁራን ይስማማሉ።
የግለሰቡ አእምሮ ለራሱ ጭንቀትን የሚፈጥር ከሆነ፣ ለሰላማዊ ማሕበራዊ ግንኙነት ወይም ከሰዎች ጋር በመግባባት ለመኖር እንቅፋት የሚሆን ከሆነ፣ በራሱ ወይም በሌሎች ላይ የአካል፣ የመንፈስ ወይም ማሕበራዊ ቀውስን የሚያስከትል ከሆነ፣ ቤተሰቡን የመንግስት ስራውን፣ ትምህርቱን ወይም ማሕበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ ባሕሪው እንቅፋት ከሆነውና የመሳሰሉት ሲከሰቱ ወይም ሲታዩ የግለሰቡ አእምሮ ጤነኛ አይደለም ለማለት ያስችላል።
የዘንድሮው የዓለም አእምሮ ጤና ቀን ‹‹በሁሉም የስራ ቦታ ቅድሚያ ለአእምሮ ጤና! ግዜው አሁን ነው!›› በሚል መሪ ቃል በጥቅምት ወር መግቢያ ላይ ተከብሯል። ይህ መሪ ቃል ሊመረጥ የቻለውም ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ አካባቢ አለመኖር ብዙዎችን ለአእምሮ ጤና ችግር እያጋለጠ በመምጣቱ ነው። ባልተመቻቸ፣ ጭቅጭቅ በሞላበት፣ ከልክ ያለፈ ክትትልና ማስጨነቅ በበዛበት የስራ ቦታና አካባቢ መስራት የሰዎችን አእምሮ ጤና ከማወክ ባሻገር አጠቃላይ ሕይወታቸውን በማቃወስ በስራቸው ወይም በምርታማነት ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በእጅጉ እየጎዳ በመምጣቱም ነው።
ይህ እውነታ በኢትዮጵያም የሚንፀባረቅ ሲሆን አሁን ባለው መረጃ መሰረት ከአምስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የአእምሮ ታማሚ እንደሆነ ይነገራል። ይህም በተለያዩ መንስኤዎች ምክንያት በኢትዮጵያ የአእምሮ ጤና መታወክ የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እየጨመረ እንደመጣ ይጠቁማል። ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ አካባቢ አለመኖር ደግሞ ይህን አሃዝ ከፍ ካደረጉ መንስኤዎች ውስጥ በዋናነት ይጠቀሳል። መረጃዎች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው።
አቶ ሳሙኤል ቶሎሳ በአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተመላላሽ ሕክምና ክፍል ኃላፊ ሲሆኑ በሞያቸው ደግሞ የአእምሮ ጤና ስፔሺያሊስት ሃኪም ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የዓለም አእምሮ ጤና ቀን ሁሌም ጥቅምት 10 ቀን ይከበራል። በኢትዮጵያም ቀኑ ሁሌም በየዓመቱ ይከበራል። ይህም የሆነው የአእምሮ ሕክምና ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የሕክምና ትምህርት ዘርፍ በመሆኑና በዓለም አቀፍ ደረጃ ፆታ፣ ዘርና ቀለም ሳይለይ ሁሉንም ሰው ሊያም የሚችል በመሆኑ ነው። ለአእምሮ ሕመም የሚያጋልጡ ምክንያቶችም ብቻ ናቸው እንጂ የሚለያዩት ሕመሙ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ይነካል። የአዕምሮ ጤና ድርጅትም ከመስከረም ወር ጀምሮ የአእምሮ ጤና ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ እንዲያልፍና ጥቅምት 10 ቀን ደግሞ ቀኑን ታሳቢ በማድረግ በየዓመቱ እንዲከበር ያደርጋል።
ቀኑ በየዓመቱ ሲከበር የየቀኑ መሪ ቃል ይኖረዋል። ቀኑን በየዓመቱ ለማክበር ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ በአእምሮ ጤና ዙሪያ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ማሕበረሰቡ ስለ አእምሮ ጤና ችግር ያለውን የተዛባ አመለካከት እንዲያስተካክል ለማድረግ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ገና ታዳጊ በሆኑ ሀገራት ያለውን የአመለካከት ክፍተት ለመሙላት ነው። ሰዎች ለአእምሮ ጤና ችግር የተሻለና ዘመናዊ የሕክምና አማራጭ መኖራቸውን እንዲያውቁና በቶሎ ሕክምና ቢያገኙ ወደ ጤንነት የሚመለሱበት እድል ሰፊ መሆኑን ለማስገንዘብም ጭምር ነው።
የዘንድሮው የአእምሮ ጤና ቀን መሪ ቃል ‹‹በሁሉም የስራ ቦታ ቅድሚያ ለአእምሮ ጤና! ግዜው አሁን ነው!›› የሚል ሲሆን ከዚህ ቀደም ከነበረው መሪ ቃል የሚለየው በስራ ቦታ ላይ የሚፈጠሩ የአእምሮ ሕመሞችን ትኩረት ለመስጠትና ለመከላከል ያለመ ነው። በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ምክንያቶች በስራ ቦታዎች ላይ የሚከሰቱ የአእምሮ ሕመሞች አሉ። በኢትዮጵያም በተለያዩ ምክንያቶች በስራ ቦታ ላይ የሚያጋጥሙ የአእምሮ ጤና ችግሮች እየጨመሩ መጥተዋል። በተለይ የስራ ሰዓት አመቺ አለመሆንና አስተማማኝ የስራ ላይ ደህንነት ያለመኖር ከአጋላጭ ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት ላይ በዋናነት የሚስተዋለው ለስራ ላይ ደህንነት በቂ ትኩረት ያለመስጠት ነው። ከሌሎች የጤና ጉዳዮች አኳያ ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ትኩረት በተመሳሳይ ዝቅተኛ በመሆኑ ሰዎች በስራቸው ውጤታማ ያለመሆንና ምርታማነታቸውም ዝቅ የማለት ሁኔታዎች ይታያሉ። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ወጣትና አምራች ኃይል ነው። ስለዚህ ይህ አምራች ኃይል በተለያዩ ምክንያቶች ለአእምሮ ጤና ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ።
ወጣቱ ለተለያዩ ሱሶች ተጋላጭ እንደመሆኑ ሱስ አምጪ ነገሮችን ተጠቅሞ ወደ ስራ ሊገባ ይችላል። ስራ እየሰራ በሱሱ ምክንያት ስራውን አቋርጦ ለመጠቀም ይሄዳል። የተለመዱ የአእምሮ ጤና ችግሮች የሚስተዋልበት የእድሜ ክልልም ነው ወጣትነት። ወጣትነት ቤተሰብ የሚመሰረትበት እድሜ ነው። ሌሎችን የሚደግፉበት እድሜ ነው። አለመግባባቶች የሚፈጠሩበት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በቀላሉ ተግባብቶ ለመኖርም አስቸጋሪ የሆነና ያለመብሰል የሚታይበት እድሜ እንደመሆኑ በነዚህ ምክንያቶች ወጣቶች ለአእምሮ ሕመሞች ሊጋለጡ ይችላሉ።
ቀላል የሚባሉ የአእምሮ ሕመሞች በግዜ ካልታከሙና እያደጉ ከሄዱ ከባድ የአእምሮ ሕመም ሊያስከትሉ ይችላሉ። አንድ ሰው የአእምሮ ሕመም ከገጠመው ደግሞ ራሱንና ቤተሰቡን ሊረዳ አይችልም። በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያደርሳቸው ጉዳቶችም ይኖራሉ። ስለዚህ የአእምሮ ሕመም ድምር ውጤቱ ቤተሰብን ያፈርሳል። ማህበረሰብን ይጎዳል። እንደሀገርም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ይፈጥራል። ከዚህ አኳያ ስራ ቦታ ላይ የሚኖሩ የስነ አእምሮ ደህንነቶችንና ጤንነቶችን እንዲከበሩ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ይሆናል። ይህን በማድረግ ረገድ ደግሞ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ማስተካከል ያስፈልጋል።
የሰራተኞችን አካላዊና ስነ አእምሯዊ ደህንነታቸውን እንዲሁም ማህበራዊ ሕይወታቸውን መጠበቅ ለአእምሮ ጤናና ለምርታማነት ብሎም ለሀገርም እድገት በጣም ወሳኝ ነው። ከዚህ አንፃር የዘንድሮው የዓለም አእምሮ ቀን በሁሉም ስራ ቦታ ላይ ቅድሚያ ለአእምሮ ጤና ትኩረት እንዲያደርግ ታሳቢ በማድረግ ተከብሯል።
አቶ ሳሙኤል እንደሚናገሩት፣ የአእምሮ ሕመምን በሚመለከት በተለያዩ ሀገራት ላይ የተሰሩ ጥናቶች አሉ። ለምሳሌ በታዳጊ ሀገራት ከ10 እስከ 15 ከመቶ የሚሆነው በስራ ላይ ያለ የሕብረተሰብ ክፍል ለተለመደ የአእምሮ ሕመሞች ተጋላጭ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛዎቹ ማለትም ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ሕክምና አያገኙም። ይህም በስራቸው ውጤታማ አይሆኑም ማለት ነው።
ለምሳሌ በድብርት ወይም በመከፋት ስሜት ውስጥ ያለ ሰራተኛ ስራውን በተሟላ ትኩረት ለመስራት ይቸግረዋል። የተሰጠውን ስራ ሌሎች ሰራተኞች በሚጨርሱበት ሰዓት ሳይሆን በጣም ዘግይቶ ሊጨርስ ይችላል። ስራ ላይ ሊያንቀላፋ ይችላል። በስራ ገበታው ላይ በሰዓት ላይገኝ ይችላል። እነዚህ ምልክቶች ሰራተኛው ከዚህ በፊት የነበረው ብቃት እየቀነሰ ስለመምጣቱ ጠቋሚ ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ምልክቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት በስራ ቦታ ለአእምሮ ሕመም አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን መለየትና የስራ አካባቢን ምቹና ደህንቱ የተጠበቀ ማድረግ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ የስራ አካባቢ በሚታሰበው ልክ ለአካላዊና ስነ አእምሯዊ ጤንነት የተመቻቸ አይደለም። ሰዎች የሚሰሩባቸው የስራ ቦታዎች የተጨናነቁና ብዙ ረብሻ ያለባቸው ናቸው። ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞችም ከሚቀመጡባቸው ወንበሮች ጀምሮ ስራውን ለማስኬድ ጥቅም ላይ የሚውሉ መሳሪያዎች አመቺ አይደሉም። በፋብሪካዎች አካባቢ ደግሞ የደህንት መሳሪያዎች በአግባቡ ያለመጠቀም፣ ረጅም ሰዓት መስራት፣ ለሰሩበት ስራ ተመጣጣኝ ክፍያ ያለማግኘት፣ ወጣ ብለው የሚዝናኑባቸው ፕሮግራሞች በስራ ተቋማት ውስጥ ያለመኖር በስነልቦና፣ ማህበራዊና አእምሮ ጤናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።
ስለዚህ በቁጥራዊ መረጃዎች ላይ እንደሀገር ጥናት አልተደረገም እንጂ ምቹና ደህንነቱ ባልተጠበቀ የስራ አካባቢ ላይ በመስራት ምክንያት የሚከሰቱ የአእምሮ ሕመሞች ከፍተኛ እንደሆኑ ይገመታል። ለአእምሮ ሕመም ብቻ ሳይሆን ከዚህ ሕመም ውጪ በሆኑ ሌሎች አካላዊ ሕመሞች ሲጋለጡም ይታያል። ሰዎች ሳያማቸው ሀኪም ቤት የመሄድ፣ የሕክምና እረፍት መፈለግ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከስራ ገበታ ላይ መቅረት፣ እረፍት ማብዛትና እነዚህን መሰል ነገሮችን የማብዛት ሁኔታዎች አሉ። አዕምሮ ሕመም ኖሮባቸውም ከስራ መቅረት፣ የሕክምና እርዳታ መፈለግና አዕምሯቸውን እንዳመማቸው መናገሩ ደግሞ ልገለል እችላለው የሚል ፍራቻ ሊያድርባቸው ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ ሰራተኞች የአእምሮ ሕክምና ክትትል ያደርጋሉ። በግዜ ለመታከም የመጡት ተሽሏቸው በስራቸው ውጤታማ ሆነዋል። ነገር ግን አብዛኛው ሰራተኛ በተለይም በሚሰራበት ቦታ ላይ በአእምሮ ሕመም ውስጥ ያለ ሰው የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት አያገኝም። በሌላ አባባል በአእምሮ ሕክምና ተደራሽ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ጤና ተቋማት ላይ በሚደረገው ድጋፍ አካላዊ ሕመም አለብኝ ብለው የሚመጡ አብዛኛዎቹ ሰራተኞች የሕመማቸው መነሻ አእምሮና ስነ ልቦናዊ ነው። ስለዚህ ሰዎች የሕክምና አማራጮችን ለማግኘት በተለያዩ አቅጣጫዎች ይሄዳሉ። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የአእምሮ ታማሚዎች ከዘመናዊው ሕክምና ውጪ ወደ እምነት ተቋማት ሊሄዱ ይችላሉ። ወደ ተለያዩ ሱሶች ውስጥ የሚገቡና ሱስን ለአእምሮ ሕመም እንደመደበቂያ የሚጠቀሙም አሉ።
አቶ ሳሙኤል እንደሚገልፁት፣ የስራ ላይ የአእምሮ ሕመም ጉዳይ እንደሀገር ብዙ ባለድርሻ አካላትን ይመለከታል። አንዱና ትልቁ ነገር የፖሊስ ማሕቀፍ ሊኖር ይገባል። ስራ ቦታዎች ደረጃቸውን የጠበቁና ለሰራተኞች አመቺ ብሎም ደህንታቸው የተጠበቀ ሊሆኑ ይገባል። ሰራተኞች የሚያርፉባቸውና የሚዝናኑባቸው ቦታዎች መኖር አለባቸው። አሁን ላይ በተለይ በአንዳንድ ትላልቅ የመንግስት ተቋማት ላይ የስራ አካባቢን የመቀየር፣ የማሳመርና ፅዱ የማድረግ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ሁሉም ተቋማት ላይ በዚህ ልክ መሰራት አለበት። ከዚህ ባለፈ ሰራተኞች በቂ እረፍት ሊያገኙ ይገባል። በአሰሪና ሰራተኛ እንዲሁም በአመራርና ፈፃሚዎች መካከልም ጤናማና መልካም የስራ ግንኙነት ሊኖር ይገባል።
በሌላ በኩል የማኔጅመንት ስርዓትንም መቀየር ያስፈልጋል። በጣም ጥብቅ ክትትል፣ በሆነው ባልሆነው የት ገባህ የት ወጣህ የሚል አሰራር ካለ ሰራተኛውን ለፍርሃት በመዳረግ ለአእምሮ ጤና ችግር ስለሚያጋልጠው እንዲህ አይነቱ የማኔጅመንት ስርዓት መቀየር ይኖርበታል። በዚህ ጥብቅና ክትትል በበዛበት የማኔጅመንት ስርዓት ምክንያት ሰራተኞች የሚሰሩበትን ተቋም እንዲጠሉና ደሞዝ ቀንሰውም ቢሆን ሌላ የተሻለ ተቋም እንዲገቡ ያስገድዳቸዋል። ስለዚህ ሰራተኞች በተቋም ውስጥ ደስተኛ ሆነው እንዲቆዩ የስነ አእምሯዊና ስነ ልቦናዊ ጤንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያደርጉ አሰራሮችን ዘርግቶ መተግበር ያስፈልጋል።
በተቋማት ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መገንባት፣ ቤተ መፅሃፍቶችን ማዘጋጀት እንዲሁም ሰራተኞች ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የሚያጠናክሩበት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ከከተማ ወጣ ብለው እንዲዝናኑና አእምሯቸውን እንዲያድሱ ማድረግ በጣም ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ስለዚህ እንደየተቋማት ባህሪ የሰራተኞችን ስነ ልቦናዊና ስነ አእምሯዊ ጤና የሚጠብቁ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም