
በጠዋቱ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በር ላይ ደርሰናል። የሰውና የመኪና ብዛት በየሁሉም ሆስፒታሎች አካባቢ ቢበዛም የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅን ያገኘሁት ግን በተለየ ድባብ ነበር። የጥበቃ ሠራተኞቹ ተገልጋዩ ሳይጉላላና አንድም ሰውና መኪና ሳይፈተሽ እንዳይገባ ከወዲያ ወዲህ እየተዋከቡ በቻሉት ልክ ለመሥራት ይጥራሉ።
ይህንን ሁሉ ትዕይንት አለፍ ብለን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ ደግሞ ‹‹የባሰ አታምጣ›› ከሚያሰኝ አጋጣሚ ያደርሳል። ጠባቧ ግቢ በሰውና መኪና ብዛት ልትፈነዳ ደርሳለች። ሰውም ሆነ መኪናው መተላለፊያ አጥቷል። እኛም ያለንን አማራጭ ሁሉ ተጠቅመን ወደምንፈልገው ክፍል አመራን። ይህ ክፍል ከውጪውና ከግቢው የተለየ ድባብ አይታይበትም። ልዩነቱ ሰልፍ ተይዞ ተገልጋዮች በወንበር ላይ መቀመጣቸው ነው። ምክንያቱን ስናጣራም ይህ ሆስፒታል ብቸኛ የሆነባቸው የጤና አገልግሎቶች አሉት። ከዚያ ባሻገርም ሁሉም በሚባል ደረጃ የጤና አገልግሎቶችም ይሰጣል።
ሆስፒታሉ የእኛም ምርጫ የሆነበት ምክንያት እንደ መንግሥት ሆስፒታል ብቸኛ ሆኖ የሚገኝበትን የስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒ (speech and language theraphy or pathology) የሕክምና ምንነት፤ እንዴት እንደሚሰጥና ምን ዓይነት ሰዎች ሕክምናው እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚተገብሩትና መሰል ነገሮችን በዛሬው የ‹‹ማኅደረ ጤና›› ዓምዳችን ልናስቃኛችሁ ስለወደድን ነው።
የስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒ (speech and language theraphy or pathology) ሕክምና ለመውሰድ የመጡ ሕጻናት ከነቤተሰቦቻቸው፤ አዋቂ ሕክምና ፈላጊዎች ከውጪው ባልተናነሰ መልኩ በክፍሉ ዙሪያ ባለው ወንበር ላይ ተራ ይዘው ተሰልፈው ተቀምጠው ብናያቸውም አልፈናቸው ልንገባ ተገደናል። ምክንያቱም ሕክምናው ለሰሙትም ሆነ ላልሰሙት ያስፈልጋቸዋልና በቂ መረጃ መስጠት ይጠበቅብናል። ስለዚህም ይህ ሁሉ ሰው ከደጅ ተቀምጦ ቀጠሮ ስለነበረን አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን። በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሥነ ልሳን ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አካሉ አሰፋን በሥራ ቢባትሉም እርሳቸውንም ሆነ እኛን ያገናኘን ማኅበረሰቡ ግንዛቤ ማግኘት አለበት የሚለው ነውና ታካሚዎቻቸውን ሌላ ባለሙያ እንዲያዩላቸው በመስጠት በቀጥታ ወደ ጉዳያችን ገባን።
የመጀመሪያ ጥያቄያችንም የስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒ (speech and language theraphy or pathology) ማለት ምን ማለት ነው የሚል ነበር። እርሳቸውም፤ የስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒ (speech and language theraphy or pathology) ማለት ከሕጻናት እስከ አዋቂ ድረስ ላሉ ሰዎች የተግባቦት እና የንግግር ክህሎትን ለማሻሻል የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት ስለመሆኑ ነገሩን፡፡
ስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቋንቋን የመረዳት ክህሎት እክል ያለባቸው፤ ቋንቋን የመግለጽ ክህሎት እክል የገጠማቸው፤ የመዋጥ እና የመመገብ ችግሮች ተጠቂ የሆኑ፤ የድምፅ እክሎችና የርዕቱነት እክሎች (Fluency disorders) ያጋጠማቸው ሰዎች ጥቂቶቹ ናቸው። ሰፋ ተደርጎ ሲብራራም የሕጻናትና የአዋቂ በሚል ተከፍሎ ሊታይ ይችላል።
የመጀመሪያው በሕጻናት በኩል ያለውን ስንመለከት የስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒ ያስፈልጋቸዋል የሚባሉት ምግብ የመመገብ ማለትም ጡጦ የመሳብ፣ የመዋጥ፣ የአፍ ጡንቻዎችን የማዘዝ ወይም የማንቀሳቀስ ችግር ያጋጠማቸው፣ የትናጋ ወይም የከንፈር መሰንጠቅ ችግር የተፈጠረባቸው፣ መናገር በሚጠበቅባቸው የእ ድሜ እርከን ላይ መናገር ሳይችሉ ሲቀሩ፤ በእድሜው የሚጠበቀው የንግግር ጥራት ከሌለው፣ ከድምፅ አወጣጥ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ሲፈጠርባቸው፤ የኦቲዝም ችግር ሲገጥማቸው፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት፣ ከክብደት በታች ሆኖ መወለድ ሲያጋጥማቸው፤ የመማር እክሎች ለምሳሌ የማንበብ፣ የመጻፍ እና የሂሳብ እክሎች ሲኖሩባቸው፤ መንተባተብ፤ የቃላት ግድፈት ሲታይባቸው ነው።
በተጨማሪም በነርቭ ሥርዓተ-ነክ ችግሮች ምክንያት የሚመጣ የነርቭ ሕመም ምክንያት ያልተለመዱ ምላሾች እና ያልተለመዱ ድምፆች ሲፈጠሩ፤ ከመስማት ጋር ተያይዞ የመናገር እክል ሲኖርባቸው የንግግር ክህሎት ምርመራ እና ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።
እንደ ሀገር ከልጆች ጋር በተያያዘ ፈታኝ የሆነብንና ሕክምናውን እያጨናነቀ ያለው ችግር የልጆች የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀም ገደብ የተጣለበት አለመሆኑ ነው። ልጆች ሰፊውን ጊዜያቸውን ከሞባይልና ቴሌቪዥን ጋር እንዲያሳልፉ ይደረጋሉ፡፡
በዚህም በባሕሪያቸው፣ በንግግር አቅማቸው ደካማና ችግር ውስጥ የገቡ ይሆናሉ። ስለዚህም ወላጆች የሚያደርጉት ሲጠፋቸው ወደ ሕክምና ተቋም ይመጣሉ። ችግሩን ለመፍታትም ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ይህ ደግሞ የሌሎች ታካሚዎችን ጊዜ እንዲሻማ ያደርገዋል ይላሉ።
የችግሩ ሁኔታ በቀላሉ መፍትሔ የሚሰጠው ቢሆንም ወላጆች ዘመናዊ ሆነዋል በማለት እየተዋቸው በርካታ ልጆች ድብርት ውስጥ ይገባሉ። በዚህም የንግግር ችግርም እየገጠማቸው ይገኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የባሕሪያቸው መለዋወጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። በዚህም ራስን ማጥፋት ድረስ የሚዘልቁ ልጆች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ቀጣዩ ትውልድ ላይም የሚያጠላው መጥፎ ጥላ ይኖራል። ስለሆነም ወላጆች ይህንን ታሳቢ አድርገው በስፋት ሊሠሩ እንደሚገባቸው በዚህ አጋጣሚ ያሳስባሉ።
ወደ አዋቂዎች ስንመጣ ደግሞ የአዕምሮ ጉዳት (traumatic brain injury)፤ ስትሮክ፤ የመርሳት ችግር (dementia)፤ የቀኝ አዕምሮ ክፍል ጉዳት፤ በበሽታ ምክንያት የሚመጡ የንግግር፣ የቋንቋ እና የድምፅ እክሎች፤ መንተባተብ ወይም በፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ የድምፅ ድግግሞሽ መፈጠር ሲኖር ነው የግድ ሕክምናው እንደሚያስፈልገው የሚመከረው ይላሉ ዶክተር አካሉ።
የሕክምና ባለሙያው እንደሚሉት፤ በነርቭ ሥርዓተ-ነክ ችግሮች ምክንያት የሚመጣ የነርቭ ሕመም የንግግር ድምፅ መዛባት ምክንያት የሚመጡ ያልተለመዱ ምላሾች እና ያልተለመዱ ድምፆች (Adult speech apraxia ) እንዲሁም ተዛማጅ የነርቭ በሽታዎች በስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒስቶች ሕክምና እንዲሰጧቸው እንደሚገደዱ ያስረዳሉ።
የስፒች ቴራፒ በኢትዮጵያ እንዴት እንደተጀመረ ሲያብራሩ ሕክምናው እንደ ሀገር የተለመደ እንዳልሆነና በቂ ባለሙያ እንደሌለው ይገልጻሉ። ብዙዎችም አውቀውት ወደ ሕክምና ተቋማት አይሄዱም ነበር ይላሉ። በዚህም ጥቂት የሚባሉ ሰዎች ሕክምናውን ለመውሰድ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ይመጣሉ። ሆስፒታሉም የተወሰኑ ባለሙያዎችን በመያዝ ሥራውን እንዲጀምረው ሆኗል። ረዘም ላለ ጊዜም ከላንቃ እና ከንፈር መሰንጠቅ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ የንግግር እክል ብቻ ሕክምናውን ሲሰጥ ስለመቆየቱም ያነሳሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ አሁን ግን በተለያየ አግባብ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እያገኘ በመሆኑ፤ ድነው የሚሄዱ ሰዎች በመበራከታቸው የተነሳ እንደ ሆስፒታል ሕክምናው መስፋት እንዳለበት ታምኖበት አለ የሚባለው ሕክምና እየተሰጠ ይገኛል። ይሁን እንጂ ሕክምና ፈላጊውና ሕክምናውን የሚሰጠው ባለሙያ የተመጣጠኑ አይደሉም። በተጨማሪ ሕክምናው ሲሰጥ ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ በበቂ ሁኔታ እንዳይሰጥ አድርጎታል፡፡
ሁኔታዎች ተገድበው እንዳይቀሩ ግን የተለያዩ አማራጮች ጥቅም ላይ የማዋል ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው። አንዱ ተጨማሪ ልምምዶችን በቤት ውስጥና በትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዲያደርጉ ከወላጆች ጋር በቅርብ ይሠራል። ለአዋቂዎችም በቂ ምክር ይሰጣል።
ይህን ሕክምና የሚሰጡት ስፒች እና ላንጉጅ ቴራፒስት ወይም ፓቶሎጂስት ባለሙያዎች ሲሆኑ፤ አሁን ላይ ያሉት በቁጥር ከ20 አይበልጡም። ይህንን ቁጥር በመያዝ ደግሞ በቀን ሳይንሱ የሚለው ከአራት እስከ አምስት ሰዎችን ማከም ይገባል ይላል። ሆኖም ያለምንም እረፍት 10 ሰዎችን በማስተናገድ ሕክምናውን ለማኅበረሰቡ ለማድረስ እየተሞከረ ይገኛል ሲሉም ያለውን የሥራ ጫና ይናገራሉ።
ሰዎች ወደ ሕክምናው እንዲሄዱ የሚያስገድዷቸው ነገሮች በሁለት ዓይነት መልኩ ይታያሉ። የመጀመሪያው በተፈጥሮ እክል ሲገጥማቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው በሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት ነው። ከዚህ አንጻርም የስፒች ቴራፒ ሕክምና ለሁለቱም ችግሮች መፍትሔ አምጪ ሕክምና ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም ዶክተር አካሉ ያስረዳሉ።
የስፒች ቴራፒ ሕክምና በአብዛኛው በልምምድና ሥልጠና የሚከናወን ሲሆን፤ ዋና ዋናዎቹም የጽሑፍ ቴራፒ፤ የንግግር ቴራፒ፤ ጆሮ መርጂያ መሣሪያ በማድረግ የሚሠራ ቴራፒ፤ የማስታወስና የመዋጥ ልምምዶች የሚደረጉበት ቴራፒዎች ናቸው። አገልግሎታቸው ሲሰጡም የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ነው። አንዱና ዋነኛው ደግሞ ንግግር በሕክምና ሂደቱ የችግሩን ዓይነትና በምን ምክንያት ችግሩ እንደደረሰ ማወቅና ከዚያ ባሻገር ከምን ዓይነት ሕመም ጋር ግንኙነት እንዳለውና ከምን ዓይነት ሕመም ወይም አደጋ ጋር ተያይዞ ችግሩ እንደተፈጠረ ይታያል። ከዚያ እንደ ችግሩ ሁኔታ በተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች መፍትሔ ለመስጠት ይሞከራል።
የንግግርና ክህሎትን ያሻሽላሉ ተብለው የሚሰጡ የስፒች ቴራፒ መለማመጃዎችና ሥልጠናዎች እድሜን፤ ሕመም መኖሩና አለመኖሩ፤ በምን ያህል ደረጃ ችግሩ የጸና ነው፤ ያለበት የእክል ዓይነትና ፍላጎት ምን ይመስላልና መሰል ነገሮችን አይቶ በዚያ ላይ በመመሥረት ነው። የሥልጠናውን አካሄድም ተከታታይነት ያለው ሲሆን፤ የሚወሰነው በሚገኘው ውጤት ላይ በመመርኮዝ ይሆናል።
የሚሰጠው ሥልጠና በአግባቡ መከታተልና መሰጠት ካልቻለ ሕመምተኛው የሚፈለገውን ውጤት ሊያሳይ አይችልምና ጊዜ ጭምር በአግባቡ ይታያል። ከዚያ ባሻገር ለኦቲዝም ተጠቂዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ምክንያቱም በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ያሉ ልጆችን ስፒች ቴራፒ የሚሰጥ ባለሙያ ስለ ባሕሪ ማረቅ፤ ባሕሪን መረዳትና መተንተን የሚችል መሆን ይጠበቅበታል። ታካሚው ረጅም ጊዜ የሚያሳልፍበት ቦታም ለለውጡ ወሳኝ ነውና በቤት ውስጥ እና በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲሁም በሥራ ቦታዎች ላይ ከሕክምና ቦታዎች በተጨማሪ ልምምድ እንዲያደርጉ ይመከራል ይላሉ።
ዶክተር አካሉ እንደሚሉት፤ የስፒች ቴራፒ ሕክምና የሚሰጠው በአንድ አካል ብቻ አይደለም። የሕክምና ባለሙያዎች ጭምር በተለያየ ዘርፍ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ቴራፒው የሚያስፈልጋቸው አካላት የተለያዩ ችግሮች ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ። እናም ሕክምናው ሲደረግ መጀመሪያ በሆስፒታሉ የሚከናወነው ተግባር በሁሉም መስክ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ተሰባስበው ችግሩን መመልከት ነው፡፡
በመቀጠልም መጀመሪያ መወሰድ ያለበት ሕክምና ላይ ውይይት ይደረግና ታካሚው ወደ መጀመሪያ ሕክምናው ይገባል። በየደረጃው ችግሮቹ ታይተው ሙሉ ሕክምና እንዲያገኝ ይሆናል። ቴራፒውም ከዚህ አንጻር ታሳቢ ተደርጎ ነው እየተሠራበት የሚገኘው ሲሉም አሠራሩ በምን መልኩ እየሄደ እንዳለ ይናገራሉ።
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ስፒች ቴራፒን ሲሰጥ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን በማሟላት ነው።
አንዱና ዋነኛው ደግሞ ሙሉ ሕክምናው በሆስፒታሉ እንዲኖር ማድረጉ ነው። ማንኛውም ታካሚ ለሌላ ጤና ምርመራ ሌላ ሆስፒታል አይሄድም። እዚያው ሁሉንም ሕክምና አግኝቶ ጤናውን ወደ ነበረበት ተመልሶ ይወጣል። ስፒች ቴራፒም በኮሌጁ በበቂ ሁኔታ መሰጠት የተቻለው ችግሩ በየደረጃው በመታየቱ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ካለው ባለሙያ አንጻር ለመጣው ሁሉ መድረስ አይቻልም ነበር ይላሉ።
ስፒች ቴራፒ በባሕሪው አስገዳጅ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ስለመሆኑ የጠቆሙት ዶክተር አካሉ፤ ዋና ዋናዎቹ ለመመገብና ለመግባባት መቸገር እንደሆኑ ይናገራሉ። ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ተግባራት የሰው ልጅ በሕይወት የመኖርን ጉዳይ የሚወስኑ ናቸው። በመሆኑም በስፒች ቴራፒ ሕክምና አማካኝነት ወደነበሩበት መመለስ ግድ ይላል። አለበለዚያ ግን ችግሩ ከግለሰብ አልፎ ማኅበረሰብንና ሀገርን ይጎዳል።
እንዴት ከተባለ ችግሩ የሚጀምረው ከልጆች ነው። ጣፋጭ ጊዜያቸውን ወላጆች በአግባቡ እንዳያዩ ያደርጋቸዋል። ልጆቹም እንደ ልብ ከእኩዮቻቸው ጋር ቦርቀው እንዳያድጉ ይገድባቸዋል። አዋቂዎችም ቢሆኑ በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት ሥራቸውን እንደቀድሞው መሥራት አይችሉም። በሰዎች ሊገለሉ ይችላሉ። ክስተቱ ድንገተኛ ስለሆነም በቀላሉ የሚፈልጉትን ጭምር እንዳያገኙ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሀገር ላይ ዐሻራቸውን እንዳያኖሩ ይገድባቸዋል። በተጨማሪም ሀገር ከእነርሱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ ያደርጋታል። በእዚህና መሰል ምክንያቶች ሕክምናው የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት እየተሠራበት ይገኛል ሲሉ ዶክተር አካሉ ያብራራሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 6 ቀን 2017 ዓ.ም