
የዘመኑ ቴክኖሎጂ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን እያሳየን ነው። በተለይም ከጤናው አንጻር የማይታሰቡና የማይታለሙ የሚመስሉ ሀሳቦችን በተግባር ተተርጉመው እዲታዩ አስችሏል። በዛሬው የ‹‹ማህደረ ጤና›› ዓምዳችንም የምናነሳው ይህንኑ ጉዳይ ያረጋግጥልናል። ጉዳዩ ታካሚና ሐኪም በአካል ሳይገናኙ ሕክምና ማድረግ ይቻላል የሚለውን ምላሽ የሚሰጠን ነው።
ይህ ሕክምና በሳይንሳዊ ስሙ ቴሌ ሜዲስን ተብሎ ይጠራል። አንዳንዴም የርቀት ሕክምና ይሉታል። ምክንያቱም ሕክምናው የሚሰጠው ታካሚዎችና ሐኪሞች ምንም አይነት አካላዊ ግንኙነት ሳይኖራቸው በበይነ መረብና በስልክ ውስጥ ሀሳብን በድምጽ በማስተላለፍና በመቀበል ነው። ለመሆኑ ይህ የሕክምና አይነት እንደ እኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ይሰራ ይሆን፤ ምን ያህልስ እየተጠቀምንበት ነው፤ ሕክምናው በአጠቃላይ እንዴት እየተተገበረ ይገኛልና የሚሉ መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ሰፊ ማብራሪያ ይዘናል። በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየታቸውን የለገሱን ደግሞ ዶክተር ብሌን ሙጬ በረዳት ሄልዝ ኬር ውስጥ ጠቅላላ ሀኪምና የማርኬቲንግ ኃላፊ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይህ ሕክምና አዲስና በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተጀመረ ነው። እንደ ሀገር በስፋት መተግበር የጀመረው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ ነው። እንደሚታወቀው ወቅት ብዙዎች ወደ ሕክምና ጣቢያ ለመሄድ የማይችሉበት፤ የሕክምና ባለሙያዎች ቀን ከሌሊት ሳይሉ ማህበረሰቡን ለማገልገል የተሯሯጡበት ነው።
የቴሌ ሜዲስን የሕክምና ስልት ባለሙያዎች ታማሚዎችን ‹‹ቤት ተቀምጣችሁ በስልክ ክትትል እናደርጋችኋላን›› ሲሉ መጨናነቁን ለመቀነስ ተጠቅመውበትም ነበር። ወረርሽኙ ቀድሞ ሊያጠቃቸው የሚችላቸውን ሰዎች በተለይም ከበድ [ክሮኒክ] በሽታ ያለባቸው ሰዎችን ለመታደግ እድል የሰጠ ነበር። ይህ ሕክምና ሐኪሞችንም፤ ታካሚዎችንም ከማሳረፍና መጨናነቅን ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ ሚናም የተጫወተ ነበር። ከዚ አንጻርም በሀራችን የቴሌሜዲሲን ጅማሮ በኮረና ጊዜ እንደነበር ሃላፊዋ ያስታውሳሉ።
ቴሌ ሜዲስን ሐኪሙና ታካሚው በአካል ሳይገናኙ በርቀት ሆነው የጤና መረጃዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በመስጠትና በመቀበል ሕክምናን ማድረግ ነው። ለምሳሌ፡- በስልክ፤ በቪዲዮ ጥሪና በበይነመረብ እንዲሁም ተቋማት በፈጠሩት ፕላት ፎርሞች መረጃ በማስተላለፍ ሕክምናን ማከናወን ነው። በዚህ ሕክምና ውስጥ የሚደረጉ ተግባራት ልዩ ልዩ ናቸው። የመጀመርያው በሽታን ማወቅና መለየት እንዲሁም ስለ ሕክምናው መወያየት ነው። ከዚያ ለታካሚው ተራ የሚመስሉ ግን ጠቃሚ መረጃዎችን ከታማሚው ጋር መወያየት ይቀጥላል። ምክንያቱም በቴሌ ሜዲስን ወሳኙ ነገር ጥርት ያለ መረጃ ማግኘትና ታካሚውን ተረድቶ ለዚያ የሚመጥን ሙሉ መረጃ መስጠት እንደሆነ ያስረዳሉ።
አክለውም በጤናው ዘርፍ ተራ የሚባል መረጃ ባይኖርም ትንሽ የጤና ምክር ስህተት ለትልቅ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላልና በቴሌ ሜዲስን ሕክምና ሰፊ ውይይት ማድረግ የግድ ነው። ከታማሚው የሚሰጥ መረጃም በአንጻሩ ለሐኪሙና ለሕክምናው መሳካት ትልቅ ግብአት ይሆናል ይላሉ።
ሌላው የቴሌሜዲሰን አገልግሎት አንድ ታማሚ በአካል ሆስፒታል ሄዶ ታክሞ ከሐኪሙ ጋር የነበረው ቆይታ ግን አደናጋሪ ቢሆንበትና ተጨማሪ መረጃን ቢሻ፤ ስልክ ደውሎ ይህንኑ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ማድረግ ነው። በተጨማሪ ይህ አገልግሎት የድንገተኛ የስልክ ሕክምና አገልግሎትንም መስጠት የሚቻልበት ነው። ለአብነት አንድ ሰው ቤት ውስጥ ወይም መንገድ ላይ አደጋ ቢደርስበትና በቅርብ ያለው ሰው የመጀመርያ እርዳታ ለመስጠት ፈልጎ ነገር ግን ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ቢገባው፤ የስልክ ጥሪ በማድረግ በዚሁ ከሰለጠኑ ሐኪሞች ዘንድ አስፈላጊውን እርዳታ ማግኘትና ሕክምና መስጠት የሚቻልበት እንደሆነም ዶክተር ብሌን ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ቴሌ ሜዲስን አንድ ሰው ለምሳሌ፡- የጤና እክል ገጥሞት ነገር ግን የት ሆስፒታል መሄድ እንዳለበት፣ በየትኛው ሐኪምና ስፔሻሊስት ቢታይ እንደሚሻለው አማራጮችን ማወቅ ቢፈልግ፣ የትኞቹ ታማሚዎች፣ ለየትኞቹ በሽታዎቻቸው የት መታከም እንዳለባቸው፣ በዘርፉ ያሉ ሐኪሞች መቼና የት እንደሚገኙ፣ ቀጠሮ ከማስያዝ ጀምሮ የተሟላ አገልግሎት መስጠት ተጨማሪ ተግባሩ ስለመሆኑም ያነሳሉ።
ብዙ ጊዜ ሕክምናው ሲሰጥ ታካሚና ስፔሻሊስቱ በሚያደርጉት ምክክር አማካኝነት እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር ብሌን፤ አንዳንድ ጊዜ ታካሚው የማይናገር ከሆነ፤ ልጆች ከሆኑና ሁለቱ የማይገናኙበት መሰል አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ አስታማሚዎች ወይም ሌሎች አካላት ምክሩን ሊጠይቁ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። እናም የቴሌ ሜዲስን አገልግሎት የሐኪም ምክክር፤ የታካሚ የጤና ክትትል፤ የተለየ ትዕዛዝና መድሀኒት ለመስጠት ሲፈለግ፤ የራጅ፣ የኤክስሬና መሰል ንባቦችን ለማድረግ ሲፈለግ፤ የአዕምሮ ጤና እንክብካቤ፤ የጤና ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ነው፤ በመሆኑም በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ብሌን ሀሳብ፤ በቴሌ ሜዲስን መታከም የማይችሉ በሽታዎች አሉ። ለአብነት ተኝቶ መታከምን የሚጠይቁ ህመሞች፤ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሕመሞች፤ ራጅና ሲቲስካንን የመሳሰሉ ተግባራትን የሚፈልጉ ህመሞች የግድ ወደ ጤና ተቋማት መሄድን ይሻሉ። ሐኪሙ ታካሚዎችን በአካል አግኝቶ የሚከውናቸውም ናቸው። በእርግጥ እነዚህም ቢሆኑ በበለጸጉት ሀገራት መፍትሄ እየተሰጣቸው ይገኛል። ለአብነት በአውሮፓውያን ዘንድ ሮቦቲክ ሰርጀሪ ጭምር ማድረግ ተችሏል። ይህም ሩቅ ያለው ሐኪም ራሱ ጋር ያለውን መሳሪያ በመጠቀም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የተቀመጠውን ሰው ማሽኑን በመቆጣጠር ሕክምናውን ማድረግ መቻል ነው። እንደ እኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ግን ይህን ለማድረግ በብዙ መልኩ እድሉ የለም። በተለይ ከኢንተርኔት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች በፍጹም እንዳይታሰቡ የሚያደርጉ ናቸው። በስልክ እንኳን ተግባብቶ ለመፈጸም የሚያስቸግር ኔትወርክ ነው ያለው። በእርግጥ አሁን ላይ እንደ ሀገር የተጀመረው ዲጅታል ሄልዝ ኢኒሼቲቭ ብዙ ነገሮችን ይቀይራል። ትልቁን የቴክኖሎጂ መጠቀም ተግባርን እውን ማድረግ ባንችልም ቀላል የሚባሉትን የጤና ችግሮች ለማከምም ያስችለናል።
በሀገር ደረጃ ጅምሮችን ማድነቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አሁን ላይ ጊዜው የቅርብ ቢሆንም በቴሌ ሜዲስን ጠንከር ያሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል። መረጃዎች እንደሚያመለከቱት በኢትዮጵያ አሁን ላይ በቀን ቢያንስ 3000 ታካሚዎች በቴሌ ሜዲስን ምክር ለማግኘት ይደወላሉ። በረዳት ሄልዝ ኬር ብቻ እስከ 200 የሚደርስ ሰው በቀን ይደውላል፤ ምክር አግኝቶም የቴሌ ሜዲስን አገልግሎት ያገኛል። ቴሌ ሜዲስን በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፤ የሀኪሞች እጥረት፤ የሆስፒታሎች መጨናነቅ፤ የሆስፒታሎች በቅርብ ርቀት አለመኖር ሳያሳስበን ህክምናን ለታካሚ በጥራት ልናዳርስ የምንችልበት አንዱ የሕክምና ማግኛ ዘዴ ነው።
ታካሚዎችን ከእንግልትና ከወጪ ለመታደግ፤ ሐኪሞች በአሉበት ሆነው ተጨማሪ ሥራዎችን እንዲያከናወኑ ለማድረግም የሚያስችል የሕክምና ዘዴ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ታማሚዎች በሆነ ባልሆነው የጤና ተቋማትን ማጨናነቃቸውን በማስቀረት በቀላሉ መታከም የሚችሉትን በቤታቸው በማከም ከከባድ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በጥራትና በጊዜው ሕክምና እንዲያገኙ የሚያስችል ስለመሆኑም ይናገራሉ።
ቴሌ ሜዲስን ከዘመኑ እኩል እንድንራመድ ያስችለናልም። ማለትም ቤታችን ቁጭ ብለን የተለያዩ ሥራዎቻችንን እያከናወንን የሕክምና ክትትላችንን እንድናደርግ፣ በረባው ባረባው ሆስፒታል እንዳንመላለስ፣ እንዳንንገላታ፣ ልበታችንን ጊዜያችንን እንድንቆጥብ እንዲሁም ገንዘባችንን እንዳናባክን ያደርገናል። ከዚያም የሚልቀው ደግሞ በህመም ውስጥ ሆነን ችግራችንን ባለመናገራችን የሚመጣውን አደጋ ይቀንስልናል። ማለትም በጊዜው የሚሰሙንን ህመሞች ለሕክምና ባለሙያ በቀላሉ ከቤታችን ሆነን በማስረዳት መታከም ያስችለናል።
ሌላው የቴሌ ሜዲስን ጥቅም አንድ ሰው ከሐኪሙ ጋር ውሎ መድኃኒት ገዝቶ ቤቱ ገብቶ ስለ መድኃኒቱ አወሳሰድ ግራ ቢገባው ደውሎ ከሐኪሞቻችን ጋር ሊወያይበት እንዲችል እድል ይሰጣል። አሊያም አንድን የሕክምና ሂደት [ፐሮሲጀር] ለማድረግ ያሰበ ታማሚ የሕክምና ሂደቱን በተመለከተ ሊያውቃቸው የሚገቡ ቅድመ ጥንቃቄና ድኅረ ጥንቃቄዎችን ከሐኪሞቹ በተጨማሪ በስልክ ከቴሌ ሐኪሞች ጋር እንዲመክርበት የሚሆንበትም ነው።
አገልሎቱን ሲያገኝ የሚከፍለው ገንዘብ በጣም ትንሽ በመሆኑም በተለይ አቅማቸው የሕክምና ወጨዎችን ለመሸፈን ለሚቸገሩ ሰዎች እጅጉን አዋጭነት አለው። በተጨማሪም በገጠር አካባቢ ሆነው በትራንስፖርትና መሰል ችግሮች ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት መምጣት ለማይችሉ ታካሚዎችም ይህ ሕክምና አማራጭ ይሰጣል። ቴሌ ሜዲስን በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ ነው። ጥንቃቄው ደግሞ ከሁሉም አካላት መምጣት ይኖርበታል ይላሉ።
ታካሚው ከትክክለኛ ሐኪም ትክክለኛ ምክር ማግኘቱን እርግጠኛ መሆን ይኖርበታል የሚሉት ኃላፊዋ፤ የሐኪሙንም ምክር በአግባቡ ሰምቶ መተግበር የግድ መሆኑን ያስረዳሉ፤ ይህ ካልሆነ ግን አደጋው የከፋ ነው። የመጀመሪያው የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች መቆራረጥና ጥራት ችግር የሚገጥም ከሆነ ዳግም ችግሩን ለማስረዳት የተለየ አጋጣሚ መፈለግንም ይጠይቃል። ሌላኛው ጥንቃቄ የሚሻው ጉዳይ ደግሞ የሕክምናው ጥራት ነው። ለአንዳንድ ሰዎች በቂ መረጃ ሳይደርሳቸው የስልክና ኢንተርኔት መቋርጥ፤ ሰዎቹ ነጻ ሆነው ችግራቸውን አለመናገራቸው፤ የማስረዳት ችግሮች መፈጠር በአግባቡ ሊታዩ የሚገባቸው መሆናቸውን ዶክተር ብሌን ይናራሉ።
የሐኪሞች ታማኝነትም እንዲሁ ያስፈልጋል። የሚታወቅ ተቋምና በሚያማክሩበት የሙያ መስክ በቂ እውቀትም ልምድም ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል። ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ ይህ ሕክምና ከተሰጠ ብዙዎችን ሊቀጥፍ ይችላል። ሌላው የኢንተርኔት ጥበቃው የላላ መሆን የመጠበቅ መብታቸው እንዳያጎድፍ የሚፈሩ አካላትን ነጻነት መስጠት ያስፈልጋል። ይህ የሚሆነው በመንግስት በኩል ብቻ ነው። መንግስት የኢንተርኔት ጥበቃዎችን በስፋት ማጠናከር አለበት። እናም ይህ የሕክምና አገልግሎት በአግባቡ ይከወን ዘንድ ታማኝ መሆንና ተጠያቂነት ያለበት ሥራ መስራት ያስፈልጋል። ታካሚዎችን በአግባቡ አነጋግሮ በቂ መረጃ መውሰዱን ካረጋገጡ በኋላ ወደ ውሳኔ መሄድ፤ አቅም ያለው የሰው ኃይል መፍጠርም ይገባል። እንደ መንግስት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ ነው። በጤና ተቋማት በኩል ደግሞ የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠሩን ሥራ በስፋት ማከናወን ይገባል። በአጠቃላይ ከታካሚው እስከ ሐኪሙ፤ ከመንግስት እስከ ጤና ተቋማት ድረስ ያሉ አካላት ለሕክምናው ልዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ አሳስበዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም