ተኪ ምርቶችን 60 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- ተኪ ምርቶችን ከ40 በመቶ ወደ 60 በመቶ ለማድረስም ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኘ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለጸ፡፡

ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ እያደረጉ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ከአደጉ ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ ነው ሲሉ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአምራቾችን ምርት፤ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ከትናንት በስቲያ ከባለድርሻ አካላት ሲካሄድ እንደገለጹት፤እስካሁን በተሰራው ውጤታማ ስራ 40 በመቶ የሚሆኑ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል፡፡ በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት ደግሞ የተኪ ምርቶችን 60 በመቶ ለማድረስም እየተሰራ ነው፡፡

ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ እያደረጉ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ከአደጉ ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ፈትቶ የሀገር ብልፅግናን እውን ለማድረግና በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎችን በምርቶች ጥራት፣ በምርታማነት፣ በተዳራሽነትና በዋጋ እርስ በርስ ተወዳዳሪ ከመሆን አልፈው ዓለም ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መስራት አስፈላጊ ነው፤ ተወዳዳሪ ለማድረግም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የስራ ባህሎችን ማላመድ፤ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ አስፈላጊውን ድጋፍ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አብዱልፈታ፤ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የተሻለ ዋጋ እንዲያወጡ የማድረግ ስራም ከጅምሩ ውጤት እየተገኘ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪው፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናው ዘርፍ ላይ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሚሽን በመፍጠር ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ብልፅግናን እውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ማሽንና የሰው ጉልበት በመጠቀም ጥራት ያለው፤ የተሻለ ዋጋ የሚያወጣ፤ በዓለምም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማምረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና አዳዲስ የስራ ባህሎችን ተግባራዊ ማድረግ ካልተቻለ ተወዳዳሪ ለመሆን ይቅርና በገበያው ላይ ለመቆየት ያዳግታል ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ኢንዱስትሪዎች በገበያው ላይ ለመቆየት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ጠንካራ የስራ ባህሎችን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪው፣ በትምህርት፣ በጤና በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪነትን ከፍ የሚያደርግ ስራ መስራት ያስፈልጋል፤ ጥራት ያለው ምርታማነት ከአምራች እስከ ሸማች ያለውን ሰንሰለት ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ የሚያደርገው መንግሥትንም ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች 20 በመቶ ብቻ በማምረት ተወዳዳሪ መሆን አይችሉም፤ ተወዳዳሪ ለመሆን ሙሉ አቅማቸውን መጠቀም አለባቸው ብለዋል፡፡

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You