በኮሪደር ልማቱ ብዙ ተሠርቷል፤ ብዙ ሊሠራበት ይገባል!

በከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከተሞች የተሟላ መሰረተ ልማት የተዘረጋባቸው፣ ለነዋሪዎች ለቱሪስቶችና እንግዶችም የተመቻቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ በአዲስ አበባ ግንባታቸው የተጠናቀቀ የኮሪደር ልማት አካባቢዎች ጥሩ ማሳያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የአራት ኪሎ መገናኛ፣ የቦሌ መገናኛ፣ የሜክሲኮ ሳር ቤት፣ የሳር ቤት ቄራ ወሎ ሰፈር መንገዶች በሚገባ በመመልከት፣ በሙሉ ልብ በመመልከት ይህን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡

አይን ጥሩ ይወዳል፤ እነዚህን አካባቢዎች ተዟዙሮ በመመልከት አይንን ከሚወደው ማገናኘትም መልካም ነው። ይህ ሲሆን የተሰራውን የኮርደር ልማት በሚገባ መቃኘት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ‹‹በሀገሪቱ ማየት የሚፈልግ ካለ ሊታይ የሚችል ብዙ ነገር አለ›› ሲሉ እንደገለጹት ሁሉ የኮሪደር ልማቱን በሚገባ መመልከት ይገባል፤ ቀጥሎም ለተከናወኑ ታላላቅ ሥራዎች እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።

በእዚህ የኮሪደር ልማት የከተናወኑትን ሁሉ ጠቅሶ እዚህ ለመግለጽ ይቸግራል። በመሬት ውስጥ ከመሬት በላይ፣ በመብራት፣ በሕንጻ እድሳትና በመሳሰሉት በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል። መንገዶቹንና የአረንጓዴ ስፍራዎቹን እንኳ ብንመለከት ብዙ ብዙ ምስክርነታችንን አድናቆታችንን ልንገልጽላቸው የሚገቡ፣ እነዚህን ሁሉ ሥራዎች የወጠኑ፣ የመሩ፣ የሰሩ እጆች ምስጋና ይገባቸዋል ብለን ልንናገርላቸው የሚገቡ ሥራዎች በብዛት ተሠርተዋል።

ጠባብ የነበሩ ጎዳናዎች እንዲሰፉ ተደርገዋል፤ የእግረኞች፣ የአይነስውራን መንገዶች በአግባቡ በሰፊው ተገንብተዋል። በመኪናም ሆነ በእግረኞች መንገድ አጓጉልነት ስንማረር የኖርን ሁሉ እነዚህ መንገዶች በመገንባታቸው እየተካስን ነው፤ ይህን የማይል ካለ ግን ራሱን መለስ ብሎ ማየት ይኖርበታል እላለሁ።

የትራንስፖርት ተርሚናሎች/መጫኛና ማውረጃዎች/፣ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራዎች፣ በእንዴት እንዴት ያሉ ውድ እና ወሳኝ ቦታዎች ላይ ተገንብተው ማየት በእጅጉ ያስደስታል። ታክሲና አውቶብስ ሲጠብቁ ከመንገድ በወጣ ሌላ ተሸከርካሪ ስንቶች እንደሞቱ፣ አደጋ እንደደረሰባቸው ለሚያውቅ የእነዚህ ተርሚናሎች መገንባት ብቻውን የኮሪደር ልማቱን አስፈላጊነት በሚገባ ያመለክታል። እነዚህ ተርሚናሎች በቀጣይም ቁጥራቸው እንዲበዛ የኮሪደር ልማቱን ከማድነቅ በተጨማሪ መደገፍ ይገባል፡፡

በኮርደር ልማቱ አዲስ አበባ ሌላ መሰረተ ልማትም አግኝታለች። ሀዋሳን፣ ባህር ዳርን አዳማን ብቻ ለብስክሌት የተመቹ ከተሞች በማድረግ፣ አዲስ አበባ ለብስክሌት ያልተፈጠረች ከተማ ተደርጋ ቆይታለች። በከተማዋ ማስፋፊያ አካባቢዎች ከነበረ ጥቂት ሙከራ ውጪ ከተማዋ ለብስክሌት የሚሆን መንገድ አልነበራትም።

የኮሪደር ልማቱ ይህን ቀይሮታል። መሀል አዲስ አበባ፣ ቸርችል ጎዳናን ጨምሮ ብዙ ኪሎ ሜትሮች የሚገመቱ መንገዶች ተገንብተዋል። ከተማዋን ለብስክሌት ያልተፈጠረች ይሉ የነበሩ ሁሉ አሁን በከተማዋ የተገነቡ እነዚህን የብስክሌት መንገዶች ሲመለከቱ ምን ይሉ ይሆን?

በእዚህ የኮሪደር ልማት አዲስ አበባን ለሰሚም ለተመልካችም በሚገርም መልኩ አፍ የሚያስይዙ የብስክሌት/ ሞተር አልባ ተሸከርካሪዎች/ መንገዶች ባለቤት ማድረግ ተችሏል። አሁን በመንገዶቹ ብስክሌቶች /አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር/ ባይታዩም፣ በቀጣይ በስፋት እንደሚጋልቡባቸው ይጠበቃል።

ከተሞች እንዲሁም መሰረተ ልማቶቻቸው እንዲህ አይደሉም የሚገነቡት፤ ብዙ ታስቦባቸው ነው። መጪው ትውልድ፣ አሁን ያለውም በቀጣይ የሚጠበቀው የምጣኔ ሀብትና ሌሎች ዘርፎች እንቅስቃሴ፣ ወዘተ ጭምር ታሳቢ ይደረጋሉ። እናም እነዚህ ብስክሌቶች አሁን ብስክሌት ሲጋለብባቸው ባይታዩም ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ የብስክሌቶች መርመስመሻ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ከተማዋ የቱሪስቶች ምርጫ እንድትሆን ጭምር እየተሰራ እንደመሆኑ ብስክሌቶች ጎዳናዎቹን ለመቀላቀል ብዙም ጊዜ አይወስድባቸውም። ዋናው መሰረተ ልማቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መገንባቱ ነው፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት እጥረት ባለበት ከተማ ብስክሌት ጥሩ አማራጭ እንደሚሆን ማንም አይስተውም፤ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ባሏት አዲስ አበባ ደግሞ እነዚህን መዳረሻዎች ቢያንስ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በብስክሌት መጎብኘት ጥሩ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህም ቀጣይ የአዲስ አበቤዎች ባህል እንደሚሆን ይጠበቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳምንቱ መጨረሻ አንዳንድ መንገዶች በእግርና በሞተር አልባ ተሸከርካሪ መጓዝ እየተለመደ መምጣቱም ይህንኑ ያመላክታል፤ ይህ ጉዳይ በሕዝቡ ዘንድ እንዲሰርጽ ለማድረግ እየተሰራ እንደመሆኑ የእነዚህ መንገዶች ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

ማንም ሊገነዘብ እንደሚችለው፣ በመሰረቱም መሰረተ ልማት የሚዘረጋው ለአሁኑ ትውልድ ብቻ አይደለም፤ በእርግጥ የአሁኑን ትውልድ ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል። ይህም ቢሆን አቅም አንሶ መሰረተ ልማቱን በስፋትና በሚገባ አለመገንባት ውስጥ ሊገባ ይችል ይሆናል እንጂ መሰረተ ልማቶቹ የሚገነቡት ለቀጣይ ዘመናትም ነው። ቢያንስ አቅም ሲገኝ መገንባት እንዲቻል የመሰረተ ልማት መገንቢያውን ቦታ በአረንጓዴ ስፍራነት እንዲለማ እየተደረገም ቢሆን ተከብሮ መቆየት ይኖርበታል። በአዲስ አበባ አንዳንድ ጎዳናዎች ይህ እየተደረገ ነው።

የዋና ዋና መንገዶች ግንባታ ሲታሰብ በቀን ይህን ያህል ተሽከርካሪዎች ሊያመላለስ፣ ለእዚህ ዓመት ያህል ሊያገለግል፣ በእዚህ በእዚህ ጥራት ሊገነባ ይገባል የሚሉት ይታያሉ። የሚገነቡት ግን የአሁኑን ችግር፣ ሕዝብ አቤት ያለበትን ችግር ታሳቢ በማድረግ ብቻ አይደለም፤ ቀጣይ ጊዜያት ታሳቢ ያደርጋሉ። በተቻለ መጠን ግን መመላለስ፣ ማፍረስ መገንባት ያልበዛበት እንዲሆን ተደርጎ ይገነባል።

የኮሪደር ልማቱ እነዚህ ያነሳሳሁዋቸውን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ነው። ለተሽከርካሪ፣ ለእግረኛ፣ ለአረንጓዴ ስፍራ ሰፊ ቦታ የተሰጠ ከመሆኑ በተጨማሪም አንድ ነገር እንዲቀመጥ አድርጓል። የሕንጻ ግንባታ ከዋና መንገድ ሊኖረው የሚገባው ርቀትም በሚገባ ተቀምጧል። ከዚህ በሁዋላ መንገድ ጥራዝ ላይ ሕንጻ የሚገነባ አይኖርም። ይህ አንዱ የኮሪደር ልማቱ ስኬት ነው።

በመንገድ ግንባታው በኩል አንድ ጉዳይ ላንሳ። በኮርደር ልማቱ አንዳንድ ጎዳናዎች ከተማዋ አይታቸው የማታውቃቸው አይነት ተደርገው ተገንብተዋል። ከመገናኛ ቦሌ መንገድ የኮሪደር ልማት መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። መንገዱ በአንድ አቅጣጫ ብቻ አምስት መኪኖችን ማስተናገድ የሚችል ተደርጎ የተገነባ ነው። ይህ መሆኑ በዚህ መንገድ ላይ ይታይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ምን ያህል ሊያስተነፍሰው እንደሚችል አስቡት።

የእግረኞች ማቋረጫ ላይ የሚታየውን መጨናነቅ ለማስቀረትም ልማቱ አዲስ ግንባታ ይዞ መጥቷል፤ የእግረኞች የምድር ውስጥ መተላለፊያ። በመገናኛ ቦሌ ጎዳና አንድ መተላለፊያ የተገነባ ሲሆን ሌላ መተላለፊያም በእዚሁ ጎዳና እየተገነባ ነው። ይህ ስራ በአራት ኪሎ አደባባይ ላይም ተከናውኗል። በዚህ ላይ በቀጣይም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል።

ከተማዋ የተራበችውን የአረንጓዴ ስፍራም በኮሪደር ልማቱ እንድታገኝ እየተደረገች ስለመሆኑም ግንባታቸው የተጠናቀቀ የኮሪደር ልማቱ የተካሄደባቸው አካባቢዎች በሚገባ ያመላክታሉ። የአረንጓዴ ስፍራ ያሌለው የኮሪደር ልማት የተካሄደበት አካባቢ የለም። አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በጣም ሰፋፊ የአረንጓዴ ስፍራዎች እንዲኖራቸው ተደርጓል። ግንፍሌ እና ቀበናን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

የከተማ ነዋሪ የእግረኛ መንገድ በማጣት በመኪና መንገድ እየሄደ ለአደጋ የተጋለጠባት ከተማ፣ በአንጻሩ ተሽከርካሪውም የተሻለ መንገድ ለመፈለግ ብሎ እግረኛ መንገድ ላይ ሲወጣ መሰረተ ልማት እየሰበረ፣ መንገደኛ እየገጨ የተጠየቀባት፣ መኪናውም ለአደጋ የተጋለጠባት ከተማ፣ የኮሪደር ልማቱ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች እነዚህ ችግሮች የማይከሰቱበት ሁኔታ እንዲኖር ተደርጓል፡፡

ከተማዋ ለሁሉም ወገን ምቹ መንገድ መገንባቷን ከትናንቱ ጋር አስተያይተን ዛሬ ማድነቃችን አንድ ትልቅ ለውጥ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ መጪው ትውልድ በተደላደለ መልኩ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ በእዚህ ትውልድ መፍጠር መቻሉም ሌላው ተሻጋሪ ስራ የተሰራበት ሁኔታን ያመላክታል።

የኮርደር ልማቱ በከተማ ልማት ስራቸው ተጠቃሽ በሆኑ የአፍሪካም የሩቅ ምስራቅ ሀገሮችም ተሞክሮ እንደተካተተ መገመት ይቻላል። የፌዴራል መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በእነዚህ ከተሞች ያደረጓቸው ጉብኝቶችን አስመልክቶ ከወጡ መረጃዎች መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።

ተሞክሮዎቹ ልማቱ በማያዳግም መልኩ እንዲካሄድ ለማድረግ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ እንደ መሆኑ ይህ ተሞክሮ የመቅሰሙ ጉዳይ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ጉብኝቱ ከመሪዎች ባሻገር በልማቱ የተሰማሩ መህንዲሶች፣ ተቋራጮች እንዲሁም በከተማ ልማት ባለሙያዎች ጭምር እንዲካሄድ ቢደረግ ስራውን የበለጠ ውጤታማ ሊያደርገው ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል።

ልማቱ ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። በአዲስ አበባ የተካሄደውና እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ያስገኘው ውጤት ሲታሰብ፣ እኔ ግንባታውን ገና ለማሳያ የሚሆን አይነት ነው ብዩ አስባለሁ። ሰፊው የአዲስ አበባ ጉዳይ ገና እንደመሆኑ፣ ክልሎችም ወደ ልማቱ እንደመግባታቸው ሲታይ የኮሪደር ልማቱ ገና ብዙ ሥራዎች እንደሚጠብቁት አስባለሁ፡፡

እስመለአለም

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You