ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ በምግብ ራሷን በመቻል ለዓለም ተምሳሌት እንደምትሆን አገልግሎቱ አስታወቀ

አዲስ አበባ፡– በአጭር ጊዜ በምግብ ራሳችንን በመቻል ለዓለም ተምሳሌት ሀገር እንሆናለን ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ፤ አሁን የታዩ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል ከምግብ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀን ራሳችንን መቻል ሉዓላዊነታችንን የተሟላና የፀና ያደርገዋል ብሏል።

በአባቶቻችን ተጠብቆ የቆየ ሉዓላዊነታችን በጀግኖች አርሶ አደሮቻችን፣ በየእርከኑ ባሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ላብ ሉዓላዊነታችን ፀንቶ ይቀጥላል ሲል ገልጾ፤ በአጭር ጊዜ በምግብ ራሳችንን በመቻልም ለዓለም ተምሳሌት ሀገር እንሆናለን ሲል አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በውጭ ወራሪዎችና ጠላቶች የሚቃጡባትን ጥቃቶች በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷ ተከብሮ፣ የነፃነት ተምሳሌት ሆና ኖራለች ያለው አገልግሎቱ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔዎች ባለቤት፣ በተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገች፣ የሰው ልጅ እና የቡና መገኛ፣ በቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ናት ብሏል።

መግለጫው እንዳለው፤ በአባቶቻችን ደምና አጥንት ተጠብቆና ተከብሮ የኖረው ሉዓላዊነታችን በላባችን ማፅናት ባለመቻላችን በስንዴ ልመና እና እርዳታ ነፃነታችን ተሸራርፏል፡፡ ሕዝቡን ለመመገብ የሌለውን እጅ የሚጠብቅ ነፃነቱና ሉዓላዊነቱ የተሟላ አይሆንም፡፡

በመሆኑም ይህንን የእርዳታ ጥገኝነት ሁኔታን ለመቀየር፣ “በደም የተጠበቀውን ሉዓላዊነት በላባችን እናፀናል” በሚል ቁርጠኛ አቋምና ርዕይ በምግብ ራስን ለመቻል ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ተጀምሯል ሲል አስታውሷል፡፡ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል በልዩ ትኩረት መስራት ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ጠቁሟል።

ቁርጠኝነት በተሞላበት የመንግሥት አቅጣጫን በመከተል ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተደረገው ርብርብ ሀገራችን ስንዴን ከመሸመት ወጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጭምር ችላለች ብሏል፡፡ በዘርፉ በተመዘገበው ውጤት እውቅናና ሽልማትም ተችሯታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምግብ ራስን ለመቻል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጿል።

ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የበጋ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋትና መሰል ስኬታማ ንቅናቄዎች በምግብ ራስን ለመቻል የተደረጉ ጥረቶች ማሳያዎች መሆናቸውን አመላክቷል።

በመስኖ በሚለማ የበጋ ስንዴ ምርት አስደናቂ እመርታ በማስመዝገብ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት በእጅጉ በመቀነስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪን ማዳን እንደተቻለ ተጠቁሟል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ራስን ከመቻል ባሻገር እንደ አቮካዶ ያሉ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ጀምረናል ሲል አገልግሎቱ ጠቅሷል።

በግብርናው ዘርፍም ቴክኖሎጂና ሌሎች ዘመኑን የዋጁ ግብዓቶችን መጠቀም መጀመራችን ይበልጥ መደላድልን ፈጥሯል፡፡ ለዚህ አመቺ መደላድል ለመፍጠርም የግብርና ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበት የሕግ ማሻሻያ በለውጡ ማግሥት ተደርጓል ብሏል፡፡

እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችም በበርካታ ቢሊዮን ብር የመንግሥት ድጎማ ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከዓለማችን በግብርና ምርት ፈጣን ለውጥ ካመጡ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች ሲል አንስቷል።

አሁን የታዩ አበረታች ውጤቶች በማስቀጠል ከምግብ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀን ራሳችንን መቻል ሉዓላዊነታችንን የተሟላና የፀና ያደርገዋል ያለው አገልግሎቱ፤ በአባቶቻችን ተጠብቆ የቆየ ሉዓላዊነታችን በጀግኖች አርሶ አደሮቻችን፣ በየእርከኑ ባሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ላብ ሉዓላዊነታችን ፀንቶ ይቀጥላል ሲል አስታውቋል።

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ከረሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤን የማስተናገዷ አንዱ ምሥጢርም በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስመዘገበችው ስኬት መሆኑን ገልጿል። ጉባኤው በርካታ ተሞክሮዎች የቀረቡበት፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ አብነት ተደርጋ የተወሰደችበት፣ መሰል ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ የመሠረተ ልማትና የመስተንግዶ ባህል አቅሟና ልምዷ በእጅጉ ማደጉን ያሳየችበት ሆኖም በስኬት መጠናቀቁን አገልግሎቱ አመላክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You