አዲስ አበባ፡- የዓለም ሀገሮች 24 ሰዓት ዓይናቸውን የማይነቅሉበትን ቀይ ባሕርን በሸሸነው ቁጥር የሀገራችን ሕልውና እየተቃወሰ ይሔዳል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ አቶ ዳኛው ገብሩ አስታወቁ፡፡
አቶ ዳኛው በተለይ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ መውጫ ኮሪደር እፈልጋለሁ ስትል የባህር በር ብቻ ሳይሆን ህልውናዋንም ጭምር ለማስጠበቅ በማሰብ ነው፡፡ ቀይ ባሕር የባህር በር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ አጋጣሚ በስህተት ያጣችውን ቀይ ባሕር በሸሸነው ቁጥር የሀገራችን ህልውና እየተቃወሰ ይሄዳል፡፡
የታሪክ ምሁሩ አቶ ዳኛው ገብሩ እንዳሉት፤ ቀይ ባሕር ጥንትም ቢሆን የተወሰነው ክፍል የኢትዮጵያ ይዞታ እንደነበር ይታወቃል። ቀይ ባሕርን ያጣነው አለአግባብ ነው። ሰዎች የባህር በር ጉዳይን ከሸቀጥ ጋር ቢያመሳስሉትም፤ ይህ በጣም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። እኛን ጨምሮ ዓለም በቀይ ባሕር ላይ ያለው ፍላጎት የባህር በር ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ ጭምር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቀይ ባሕር በርካታ ጸጋዎች ያሉት ነው፡፡ ከጤና ጥቅም አንስቶ እስከ ትራንስፖርት ድረስ ባለው አገልግሎቱ ከፍ ያለ ፋይዳ አለው ያሉት አቶ ዳኛው፤ አንደኛ ዓለም ተጠቃሚ የሚሆነው ሸቀጦችን እና ጥሬ ሀብቶችን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ለማጓጓዝ ርካሽ የሚባለው የውሃ ላይ ትራንስፖርት ነው፡፡ የዓለም ሸቀጥና ጥሬ ሀብት በውሃ ላይ መጓጓዝ ካለበት ደግሞ ዋናው ማዕከሉ ቀይ ባሕር ነው ብለዋል፡፡
አካባቢው ብዙ ጸጋ ባለበት በእስያ እና በአፍሪካ እንዲሁም በአውሮፓ መካከል ያለ ስትራቴጂክ ቦታ ነው ሲሉ አቶ ዳኛው ገልጸዋል፡፡ የታሪክ ምሁሩ እንደገለጹት፤ ለአፍታም ቢሆን እንኳ ከቀይ ባሕር ላይ ዓይናቸውን መንቀል የማይፈልጉ ሀገሮች ዋና ፍላጎታቸው የባህር በር አይደለም። ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለወታደራዊ አቅም ስትራቴጂክ ቦታ የመፈልግና የመያዝ ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ቀይ ባሕር ላይ በመራኮት ላይ ያሉ ሀገሮች የባህር በር የሞላቸው ናቸው፡፡
እኛ ሸቀጦቻችንና ጥሬ ሀብቶቻችን በሰላም በባህሩ ላይ እንዲተላለፉ ባለቤት በመሆን ጥቅማችንን ማስከበር መቻል አለብን ያሉት አቶ ዳኛው፣ ቀይ ባሕርን ከመሸሽ ይልቅ ልንጋፈጥ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የትኛውም ሀገር እኛን እንዳይተነኩሰን የራሳችንን ኃይል ቀይ ባሕር ላይ መፍጠር መቻል ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ቀይ ባሕር ከባህር በር በዘለለ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም ቀይ ባሕር ላይ መውጫ ኮሪደር ያስፈልገናል በሚል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የወሰዱት አቋም ወሳኝ ነው፡፡
ስለቀይ ባሕር በር ስናነሳ መሽኮርመም የሚያዋጣ አይሆንም፡፡ ባለቤቶች ነን፤ ያሉት የታሪክ ምሁሩ፤ ጥያቄው ሲነሳ መላ ኢትዮጵያዊ ሊተባበር ይገባል። ምክንያቱም ቀይ ባሕር ላይ ድርሻ የማይኖረን ከሆነ ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በታኅሳስ ወር 2016 ዓ.ም ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ማካሔዷ የሚታወስ ነው፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም