የሀገራችን የእቅድ አቅጣጫ ከሆኑ አበይት ጉዳዮች መሀል አንዱ የወደብ ባለቤትነትን ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ሀገራዊ መሻት በተከበረው ምክር ቤት ፊት ለሕዝብ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ንቅናቄዎች ተደርገዋል፡፡ እንደመንግስት ጥያቄው ተገቢ እና አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በምክንያትና ውጤት በታገዘ ሂደት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሳል ውይይት ተደርጓል፡፡
የወደብ ጉዳይን በተመለከተ እጅግ ዋጋ ያለውና በሁሉም ዘንድ እንደአስታራቂ የሚነሳው ጉዳይ ውይይት የቀደመበት የአብሮ መልማት አቅጣጫ ነው፡፡ እንደመንግስት ያነሳነው ጥያቄ አብሮ የማደግን መርህ የተከተለ እና የእርስ በርስ ትስስርን የሚያጎለብት መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። በስፋት እንደተገለፀው አሁን ባለንበት ወቅታዊ ሁኔታ የወደብ ጥያቄ በብዙ መልኩ አስፈላጊ ነው። ሰፊና የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትነታችን፣ በየእለቱ የሚጨምር የሕዝብ ቁጥርና አብሮ ከሚመጣው የሕዝብ ፍላጎት፣ እንዲሁም በቀጣናው ካለን ተጽዕኖ ፈጣሪነት አኳያ አስፈላጊነቱ ብዙም፣ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡
ይህንን ተጨባጭ እውነታ ታሳቢ ባደረገ መንገድም መንግስት ከሱማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡ ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት ማንንም የማይጎዳ በተቃራኒው የንግድና የኢኮኖሚ፣ የደህንነትና የዲፕሎማሲውን ሂደት የሚያቀላጥፍ፤ አብሮ ማደግን መሰረጥ ያደረገ እንደሆነም ይታመናል፡፡
የትብብር ሰነዱ በብዙ ጥናት የተደገፈ በእርስ በርስ ጉርብትናና በአብሮ ማደግ መርህ የተቃኘ መሆኑ የታመነ ቢሆንም በሶማሊያ መንግስት በኩል የግጭት ምንጭ ለማድረግ አላስፈላጊ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብቷል፡፡ ኢትዮጵያና ሱማሊያ በብዙ መንገድ የተሳሰሩ፣ የተጎራበቱ ሀገራት ናቸው፡፡ ካላቸው ቅርበትና ጥምረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚነሱ ማናቸውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች የሁለቱን ሀገራት ወንድማማችነት ከማጠንከር ባለፈ ለግጭት በር የሚከፍቱ መሆን የለባቸውም፡፡
በተፈጥሮ ጸጋ ተጋግዞና ተመካክሮ አብሮ መልማት፣ አብሮ ማደግ እየተቻለ ለግጭት መንገድ በሚከፍት፤ ለንትርክና ላልተገባ ድርጊት ለሚያጋልጥ ሁኔታ ሀገራቱን ለክተት ተገቢ አይደለም፤ ማንንም ሊጠቅም የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ የቀደሙ የትብብር እና የጉርብትና ግንኙነቶችን ከማጥቆር ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።
በሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ሀሳብ ለጋራ መድከም፤ጦርነትን በሚሽር የትብብር ማዕቀፍ ውስጥ መሳተፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ወንድማማችነት በሚያስቀጥል፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበራዊ ተሳትፎ ባለው የትብብር መንፈስ ውስጥ መቆም ወሳኝ ነው፤ ኢትዮጵያ ያነሳችውም የባሕር በር ጥያቄም ከዚህ አኳያ የተቃኘ ነው፡፡
ኃላፊነት እንደሚሰማው ጎረቤት የኢትዮጵያ መንግስት እና ሕዝብ ለሱማሊያ ብዙ ውለታ ውሏል ነው፡፡ ጎረቤት የሚለው ቃል ተለምዷዊ ስለሆነ ተራ ይመስላል እንጂ እጅግ ዋጋ ያለው ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሉአላዊነት የግዛት መከበር ቅድሚያ ሰጥታ ወታደር በማዋጣት፣ የሰላም ሀሳብ በማቅረብ፣ አስታራቂና አሸማጋይ ሆኖ በመግባት አጋርነቷን ስታሳይ ቆይታለች፡፡
ወዳጅነቷም ለበርካታ ዓመታት በሰላም ማስከበር ስም ወታደሮቿን በመላ የሕይወት መስዋእት ስትከፍል ቆይታላች፡፡ ሀገሪቱ ከአክራሪዎች እና አሸባሪዎች ጥቃት መታደግ የሚያስችሉ ወታደራዊ ስምሪቶችን ወስዳ በጥናት ሰርታለች። ይህ የሶማሊያ ሕዝብ የእለት ተዕለት የምስክርነት ቃል ነው።
በእርግጥ እንደሀገር አይደለም እንደግለሰብ ጉርብትና የላቀ ዋጋ ያለው ነው፡፡ ከጉርብትና ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችም በመከባበርና አብሮነትን ሊያስቀጥል በሚችል መንገድ በትብብር መስራትን ይጠይቃል፡፡ ከባሕር በር ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄም ሆነ በሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በዚህ የትብብር መንፈስ ስር የሚንጸባረቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ አብሮ ከመስራት ባለፈ በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ታሪክ ኖሯት አያውቅም፡፡ የመጣንባቸው ዘመኖች በመካፈልና በማካፈል የሚጠሩ የጉርብትና ዘመኖች ናቸው። ፍትህና ሚዛናዊነት መለያዋ ነው። ቆርሶ ተጋርቶ መብላት እንጂ ራስ ወዳድነትን መገለጫዋ አይደለም።
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያንና የሱማሊ ያን የቆየ ወዳጅነት በማስታወስ ለአብሮ ማደግ ቅድሚያ በመስጠት ሰላም ተኮር መልዕክቶችን ማስተላለፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊያ አሁን ባሉበት የኢኮኖሚ እና የሕዝብ ጥያቄ ከሰላም ውጪ ሌላ ነገር የማያስፈልጋቸው ናቸው። ወንድማማችነትን ባስታወሰ በአብሮ ማደግ መርህ መግባባት ቢቻል የወደብ ጥያቄ ይሄን ለግጭት ምክንያት የሚሆን አልነበረም፡፡
ከፍ ብዬ ለማንሳት እንደሞከርኩት የሚሻለው የተሻለውን መምረጥ ነው፡፡ የተሻለው ደግሞ በውይይትና በመከባበር የጋራ ተጠቃሚነትን መፍጠር ነው፡፡ በርሃብና በኋላ ቀርነት ለሚታወቀው ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ግጭት ሳይሆን ልማት ነው የሚያስፈልገው፡፡ የግጭት እሳቤዎች በቀደሙት ዘመናት ሀገራቱን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈሉን ቆም ብሎ ማሰብም አስተዋይነት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ከመሆኑ አንጻር፤ በምንም መልኩ ቢቃኝ ተገቢነቱ ያለው የሁሉንም ጎረቤት ሀገራት ይሁንታ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተደረሰበት የመግባቢያ ስምምነትም በቀጠናው አዲስ የትብብር የታሪክ ምእራፍ የሚከፍት ነው።
ስምምነቱ የሶማሊያን መንግስት ለማስቆጣት ሆነ ወደ አልተገባ መንገድ እንዲሄድ የሚያስገድድ አልነበረም። በተለይም ጥያቄው በአደባባይ ወደብ ላላቸው ጎረቤት ሀገራት የተደረገ ከመሆኑ አኳያ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ይቻል ነበር።በሀገራቱ መካከል የነበረውን በመስዋዕትነት የታተመ ወዳጅነት በተሻለ መንገድ ማስቀጠል ይቻል ነበር።
የሶማሊያ መንግስት ስምምነቱን ከመቃወም ጀምሮ ሌሎች /በጉዳዩ የማይመለከታቸው ኃይሎች በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ የሄዱበት የተሳሳተ መንገድ፤ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር የሚያደርግ፤ የአካባቢውን ሕዝቦች የሰላም እና የልማት ጥያቄ የሚፈታተን ትልቅ ተግዳሮት ነው። በተለይም በሶማሊያ ሕዝብን ቀጣይ ሰላም ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ ስለመሆን መገመት አይከብድም።
እንዲህ አይነቱ ያልተገባ አካሄድ፤ ቀጠናው እንዳይረጋጋ ለሚፈልጉ ኃይሎች እንደ ትልቅ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው። የጥፋት እጆቻቸውን እንዲያስረዝሙ እድል የሚፈጥር ነው። ይህ ደግሞ ለሀገራቱ ሕዝቦች “ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ“ ከመሆን ባለፈ ሊያስገኝላቸው የሚችል ጠቀሜታ አይኖርም። አዋጪው መንገድ የቀደመውን ወንድማማችነትን ማስቀደም፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በዋጀ የእርስ በርስ ቁርኝት ጠብ ጫሪ አካሄዶችን መግታት ነው፡፡
የሁለቱ ሕዝቦች የታሪክና የጉርብትና ታሪክ የጠነከረና በቀላሉ የማይላላ እንዳይደለ ብዙ ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንደባሕር በር ያሉ ሕዝባዊ ጥያቄዎች በብስለት ከታዩ ለመለያየት ሰበብ ከመሆን ይልቅ ለአንድነት ጉልበት የመሆናቸው እውነታ ያመዝናል፡፡ ይህን በሰከነ መንፈስ ማየት ተገቢ ነው።
ከዚህ ውጪ በሶማሊያ በኩል እየታየ ያለው የጠብ ጫሪነት እንቅስቃሴ በድሀ ሀገርና ሕዝብ ላይ ሌላ መከራን ከማወጅ ባለፈ ለማንም ፋይዳ የሌለው መሆኑ ሳይዘገይ ለማወቅ መጣር መልካም ነው፡፡ ሀገሪቱ ከግብጽና ከመሰል ሀገራት ጋር እያደረገችው ያለው ጠብ ጫሪ ወዳጅነት ከጥፋት ውጪ ለሀገራቱ ሕዝቦች የሚያመጣው አንዳች በጎ ነገር አይኖርም፡፡
የአብሮነትን ጎዳና ማቅናት እንጂ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል የጥፋት መንገድ ነገር መጎንጎን ዋጋ የለውም፡፡ ስለፍቅር መቧደን እንጂ ስለጠብ መቧደን ለማንም አይበጅም፡፡ ስለሰላም መመካከር እንጂ ጥፋት መመካከር ትርፉ ኪሳራ ነው፡፡ አዋጪና አትራፊ በሆነ ስምምነት አብሮ መስራት እንጂ የቀጠናውን ሰላም በሚረብሽ ሁኔታ ዘራፍ ማለት የትም አያደርስም፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ ሃሳብ የጋራ ብልጽግና ላይ ቢያተኩሩ ነው የሚሻላቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብን የወደብ ፍላጎት መረዳት ቀዳሚው ነው፡፡ የሀገሪቱ የወደብ ጥያቄ ከሞራል ሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ተጠያቂ መሆን መገንዘብ፤ ለጥያቄው ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። በጉዳዩ ዙሪያ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡
በየትኛውም ጉዳይ ላይ ውይይትን አስቀድሞ አብሮነትን ማስቀጠል ትርፉ በምንም የሚሰላ አይደለም፡፡ ሶማሊያ ልትይዘው የሚገባው አቋምም ይሄ ነው፡፡ የራስን ጥቅም ሳያስነኩ ለወዳጅነት ቅድሚያ መስጠት እጅግ የላቀ የዲፕሎማሲ መርህ ነው፡፡ መከባበርና መቻቻል ካለ ሁሉም ተፈጥሮ በቂያችን ነው፡፡
በየትኛውም ሁኔታ ቢታይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በመከባበር መርህ ተያይዘው ማደግን ካልመረጡ በዛቻና በሰጣ ገባ ማደግ እንዳይችሉ ሆነው የተጎራበቱ ናቸው፡፡ ከኢኮኖሚ ባለፈ የሁለቱ ሀገራት የባህልና የማህበራዊ ትስስር በቀላሉ እንዳይላላ በመሆን አንዳቸው ለአንዳቸው ወሳኝ እንደሆኑ የሚያስረዳ ነው፡፡ ይሄ ወሳኝ ጉርብትና ባልተገባ እሰጣ ገባ እንዳይላላ መከባበርን ባስቀደመ የወንድማማችነት ስሜት ሊታይ ይገባል፡፡
በተለያየ መድረክ ላይ እንደተንጸባረቀው የኢትዮጵያ ፍላጎት አብሮ ማደግ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ፍላጎት አልነበረም ወደፊትም አይኖርም። በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዝነው አቋም ይሄ ነበር። በባሕር በር ላይም በዚህ አቋም ስር ነን፡፡ የኢትዮጵያ ስልጣኔ አብሮ በማደግ የሚያምን ነው፡፡ ታሪካችን፣ ሀገረ መንግስታችን ሲጸናና ሲመሰረት ጎናችን ያሉን በማጤን ነው፡፡ ስለሆነም ጥያቄአችን ክፋትና ራስወዳድነት የሌለው እንደሆነ ከማንነታችን የሚታወቅ ነው፡፡
ወንድም ከወንድሙ አብሮ ሲሰራ እንጂ ሲቃቃር ደስ አይልም፡፡ ከየትኛው ሀገር በላይ ሶማሊያ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ በነዚህ ሁለት ሕዝቦች መሀል የልማት፣ የእድገት፣ የሰላም፣ አብሮ የማደግ እንጂ የጠብ እቅድ ትርፋማ አይሆንም፡፡ በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራስወዳድነት የማያውቅ ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡ ነውር አዋቂ ይሉኝታ የሚገዛው ዘመናዊነትን ከባህልና ከስርዐት ጋር አቻችሎ የሚኖር ነው፡፡ ለአብሮነት ቅድሚያ የሚሰጥ በትብብር የሚያምን መልካም ጎረቤት ነው፡፡
በፍቅር ስም፣ በወንድማማችነት ግብር ከማንም ጋር አብረን ልንሰራ የበረታን ነን፡፡ በጀመርናቸው ለሕዝብ ቅድሚያ በሚሰጡ ጉዳዮች ላይ በጋራ መርህ ለጋራ መስራት ሲወርድ ሲዋረድ ይዘነው የመጣነው መከበሪያ ስማችን ነው፡፡ ለውጥ በውህደት የሚፈጠር የትብብር መንፈስ እንጂ እኔን ብቻ ይድላኝ በሚል አስተሳሰብ የሚወለድ አይደለም። በወንድማማችነት መንፈስ ከሚበልጠው ወደሚበልጠው በመሄድ ድህነታችንን ታሪክ ለማድረግ ለእኛም ለሱማሊያም ያለን እድል ተጋግዞ መስራት ብቻ ነው፡፡ አበቃሁ፡፡
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም