የዛሬው የወቅታዊ እንግዳችን የኦሮሚያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሶ ቢቂላ ናቸው። በክልሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከል ስራ ምን ላይ ይገኛል? የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ጋር ተያይዞ ምን ተሰርቷል? የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እንዴት ነበር? በተያዘው በጀት ዓመት ምን ለመስራት ታቅዷል? በሚሉ እና ሌሎች ቢሮው በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- የቢሮው ዋና ዋና ኃላፊነቶች ምንድናቸው?
አቶ አራርሶ፡- እንደሚታወቀው ቢሮው በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ፣ በስራ እድል ፈጠራ እና በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ላይ ይሰራል። በማሕበራዊ ጥበቃ ከአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይም ስራዎችን ያከናውናል። በተጨማሪም ኢንዱስትሪ ግንኙነት እና ሰላም ላይ የተለያየ ተግባራትን ያከናውናል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ምን አይነት ስራ እየተሰራ ነው?
አቶ አራርሶ፡– ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በ2016 በጀት ዓመት ከክልል እስከ ወረዳ ኮሚቴ በማቋቋም ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል። ከጎረቤት ክልሎች ጋር ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ከሶማሌ ክልል እና ከሌሎች ክልሎች ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው።
ይህ ጉዳይ ተቀናጅቶ መስራት የሚጠይቅ ነው። በተለይም ሀገር ውስጥ ያሉ ደላሎች እስከ ጎረቤት ሀገራት ድረስ በመሄድ መዋቅራቸውን እየዘረጉ ነው። ይህን መዋቅር ለመከታተል ከጸጥታ አካላት ጋር መስራት አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት እየሰራን ነው። ባለፈው ዓመት የተዋቀረው ኮሚቴ እስከ ወረዳ ነበር፤ በ2017 በጀት ዓመት እስከ ቀበሌ በማድረስ ወጣቶች ላይ ለመስራት እቅድ ተይዟል።
ሕገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር መፍትሄ የሚሆነው የመጀመሪያው ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ነው። ሁለተኛው በሕጋዊ መንገድ አስፈላጊው መረጃ ተሟልቶላቸው እንዲሄዱ ማድረግ ነው። ሕገወጥ ዝውውሩን ለመቆጣጠር ድንበር መዝጋት አይቻልም።
እንደ ክልል ችግሩን ለመቆጣጠር እንዲያስችል ለወጣቶች ግንዛቤ መፍጠር፣ በሀገር ውስጥ የስራ እድል መፍጠር እና በሕጋዊ መንገድ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲያገኙ ለማድረግ ከባለፈው ዓመት በበለጠ መልኩ ለመስራት እቅድ ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡- በአካባቢው ለሕገወጥ ስደት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በክልሉ ችግሩ የሚበዛው የት የት አካባቢ ነው?
አቶ አራርሶ፡– ወጣቶች ውጭ ሀገር በመሄድ በቀላሉ ስራ ይገኛል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው።
በኦሮሚያ ክልል የት አካባቢ ነው ችግሩ የሚበዛው የሚለውን ስንመለከት፤ ከዚህ በፊት ኦሮሚያ ውስጥ ስድስት ዞኖች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ወደ ስምንት ከፍ ብለዋል። ችግሩ በሁሉም ዞኖች አለ። ነገር ግን ጅማ፣ በሁለቱ ሐረርጌ እና አርሲ ዞኖች ከፍ ይላል።
በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ ስራ በመሰራቱ ችግሩ እየቀነሰ መጥቷል። የተሻለ ነገር ቢኖርም አሁንም መስራት ያስፈልጋል። ወጣቶች ግንዛቤ አግኝተው በሀገር ወስጥ ስራ እንዲያገኙ ማድረግ ዋናው ነገር ነው። ሁለተኛው በሕጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ማድረግ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከሁሉም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እስከ ፌደራል ድረስ ቅንጀት ያስፈልጋል።
እዲስ ዘመን፡- በክልሉ የስራ እድል ፈጠራ እና በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ምን አይነት ስራ ተሰርቷል? የተገኘው ውጤትስ ምን ይመስላል?
አቶ አራርሶ፡- የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። የኢሉአባቦራ ዞን ብቻ ብንወስድ ከ250 ሺ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው በግብርና ስራ ተሰማርተው እየሰሩ ነው። በባሌ በኩልም እንደዚሁ በግብርና ተሰማርተው እየሰሩ ያሉ አሉ።
በግብርና የተደራጁ ወጣቶች የተሰማሩት በተለያየ የግብርና ስራ ላይ ነው። በሩዝ፣ በሻይ ፣ በቡና በአትክልትና ፍራፍሬ እና በመሳሰሉት ላይ ነው።
በኢንዱስትሪ ዘርፍም ባለፈው በጀት ዓመት አራት ሺ 65 ወጣቶች በሸገር ከተማ በስራ እንዲሰማሩ ተደርጓል። በተመሳሳይ በቢሾፍቱ ከተማ አንድ ሺ 600 የሚሆኑ ወጣቶች ስራ አግኝተዋል። በአጠቃላይ በክልሉ በሀገር ወስጥ ስራ እንደሚገኝ በማመን በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በግንባታ ስራ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
ሌላው የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በተመለከተ ባለፈው ዓመት በርካታ ሰዎች እንዲሄዱ ተደርጓል። በ2017 ዓ.ም በርካታ ወጣቶችን ለመላክ ጥረት እየተደረገ ነው። ከባለፈው የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በግብርና የተሰማሩ ወጣቶች የሚሰሩት ማሳ ተሰጥቷቸው ነው ወይስ ከአልሚዎች ዘንድ ተቀጥረው ነው?
አቶ አራርሶ፡- አንዳንድ ቦታ ላይ ወጣቶቹ ተደራጅተው መሬት ይሰጣል። ጅማ ላይ የተደረገው እንደዚያ ነው። ግብርና ሲባል ከብት እርባታ፣ ዶሮ እርባታ እና ሌሎች የአርብቶ አደር ስራዎችን ስለሚያካትት በእነዚህ ዘርፎች የተሰማሩም አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩት ምን ላይ እየሰሩ ነው?
አቶ አራርሶ፡- ፋብሪካዎቹ በዚህ ዘርፍ የወሰዱት ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ የተማሩ ተማሪዎችን ነው። ወጣቶች ትምህርት ተምረው ከተመረቁ በኋላ ቀበሌ ውስጥ ዝም ብለው ያለ ስራ ይቀመጣሉ። ይህን ነገር ከቢሾፍቱ እና ሸገር ከተማ ጋር ተወያይተን፤ ኮሚቴ አቋቁመን በስራ እንዲሰማሩ ተደርጓል።
እነዚህ ወጣቶች ስራ አጥተው ቁጭ የሚሉ ከሆነ በኋላ ለሕገውጥ ዝውውር ይዳረጋሉ። ችግሩ እንዳይፈጠር ቀድሞ በከተማ ደረጃ በመወያየት መፍትሄ ለማስቀመት ተፈልጎ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የስራ እድል የተፈጠረላቸው ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቁ ብቻ ነው? ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውንም ያካትታል?
አቶ አራርሶ፡– የስራ እድሉ የተፈጠረው ከ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርት ያቋረጡ እና ላልተማሩም ጭምር ነው። እነዚህ በስፋት ነው የስራ እድል ያገኙት በግብርና እና በግንባታ ስራ ላይ ነው። በ2016 ዓ.ም ‘አፍሪካ ሆልዲንግ’ ከሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ከክልሉ ከተለያዩ ዞኖች 24 ሴቶችን ለአምስት ወራት በማሰልጠን በድርጅቱ በኩል ስራ አግኘተዋል።
ከስራ ፈጠራ ጋር ተያይዞ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ምን ማድረግ እንዳለብን ተወያይተን በጋራ እንሰራለን። የአፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ በቀጣይም አብሮን ለመስራት እቅድ አለው። ስለዚህም በ2017 በጀት ዓመት በጋራ እንሰራለን ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስራ አጦቹን የምታደራጁት እራሳቸው መጥተው ሲያመለክቱ ነው? ወይስ ወጣቶቹ ዘንድ ለመድረስ የራሳችሁ አሰራር አለ?
አቶ አራርሶ፡- በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ የሚደረጉት ወደ ወጣቶቹ ለመድረስ የራሳችን መዋቅር ስላለን በዛ መዋቅር በኩል ነው። እነሱ ብቻ በሚያመለክቱት አይደለም። በተለይ በግንባታ ስራ ላይ የሚደረገው እንደዚያ ነው፤ ሰው ፍላጎት ኖሮት ከተደራጀ ስራ አያጣም።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት በተመለከተ ምን አይነት ስራ ተሰርቷል? በተሰሩ ስራዎች ምን አይነት ለውጥ ተስተውሏል?
አቶ አራርሶ፡- አሁን ላይ ያለው ለውጥ የተሻለ የሚባል ነው። ከዚህ በፊት ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ ችግር ነበር፤ በኤጀንሲዎች እና በወጣቶች መሀከል ያለው ትስስር ጥሩ አልነበረም። ያለውን ችግር ለመፍታት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመወያየት በኦንላይ እንዲሆን ተደርጓል። ስለዚህ አሁን ላይ ሂደቱ አይዘገይም።
ከዚህ በፊት ማስረጃዎችን ለማሟላት ከፍተኛ ችግር ነበር። አሁንም ችግሮች ቢኖሩም ከበፊቱ አንጻር ችግሩ የቀነሰበት ሁኔታ ነው ያለው። በዘንድሮ በጀት ዓመት ጠንክረን በመስራት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር እየተወያየን ነው።
የስራ ስምሪቱ ከ2015 ዓ.ም ይልቅ በ2016 የተሻለ ነው። ከዚህ የበለጠ ውጤት በዘንድሮ ዓመት እንዴት ማምጣት አለብን በሚሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተን ስምምነት ላይ ደርሰናል። ከሀገራችን ስፋትና ከሕዝቡ ብዛት አንጻር ስንመለከት አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት ዓመት በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ምን ያህል ሰዎች ላካችሁ? ለስራ የሚላኩትስ ስልጠናቸው ምን ምን ያካተተ ነው?
አቶ አራርሶ፡- እንደ ኦሮሚያ ክልል የላክነው ከ295 ሺ በላይ ወጣቶችን ነው። ስልጠና ይሰጣል። በተለይ ወደ መካከለኛው ምስራቅ፤ ዮርዳኖስ፣ ሳዑዲ አረቢያ በአብዛኛው የሚሄዱት ሴቶች ናቸው። ለእነዚህ ሴቶች ስልጠናው የሚሰጣቸው ከቤት አያያዝ እና ከቤት ውስጥ ስራዎች ጋር ተያይዞ ነው።
በክልሉ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ለሚሄዱ ወጣቶች ስልጠና የሚሰጡ አምስት ኮሌጆች አሉ ። በኮሌጆቹ ብዙ ስራ እየተሰራ ነው፤ ከዚህ በፊት ስልጠና ወስደው የሄዱ አሉ። አሁንም ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ሰልጣኞች አሉ። ስልጠናው ሁሌም ቀጣይነት ያለው ነው።
ስልጠናውን ከዚህ በፊት ውጭ ሀገራት ቆይተው የሚመጡም ይሰለጥናሉ። ነባሮቹ ልምድ ያላቸው ስለሆነ ለእነሱ የሚሰጠው ስልጠና እና አዲስ ለሚሄዱት የሚሰጠው የስልጠና አይነት የተለያየ ነው። ለሶስት ወር፣ ለአንድ ወር እና ለ15 ቀናት የሚወስዱ አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ለስራ ከሄዱ በኋላ ስለ ደህንነታቸው እና ከገንዘብ ጋር ተያይዞ ባሉ ጉዳዮች የሚደረገው ክትትል ምን ይመስላል?
አቶ አራርሶ፡- ስራዎች የሚሰሩት በኤጀንሲዎች በኩል ነው። ዜጎች ከሄዱ በኋላ የት እንደተቀጠሩ፣ የገንዘብ ሁኔታ እና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በየ ሀገሩ ባሉት ኤምባሲዎች በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክትትል ያደርጋል እኛም ክትትል እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- በስራ ስምሪት ሂደቱ የተወሰኑ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸውልኛል፤ እነዚህ ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ አራርሶ፡- ያለው ችግር ፓስፖርት ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ቶሎ የማግኘት ሁኔታ አለ። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የመዘግየት ሁኔታ አለ። ለዚህ ደግሞ ወጣቶቹ መመላለስ ግድ ይላቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሊዘገይ የቻለበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ አራርሶ፡- እንደሚታወቀው ሀገራችን ሰፊ ናት። ፓስፖርት የሚሰጠው በፌደራል ደረጃ አዲስ አበባ ከተማ ነው። ነገር ግን ሰዎቹ የሚመጡት ከዞን ስለሆነ ርቀት አለ። በአንዴ ሲመጡ ፓስፖርት ለማግኘት ከአንድ ሳምንት እስከ አንድ ወር የሚቆዩ አሉ። ያለውን ክፍተት እንዴት መሙላት እንደሚቻል ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር ውይይት እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ የፓስፖርት ምዝገባ በኦንላይ ነው። ሰራተኞቹ ወደ አዲስ አባባ መምጣት የሚጠበቅባቸው ለጤና ምርመራ ብቻ እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲገልጽ ነበር። የሚቆዩት የቴክኖሎጂ ተደራሽነት ያለመሆን ችግር ነው? ወይስ ከምን አንጻር ነው?
አቶ አራርሶ፡- በኦንላይን የሚለቀቀው አጠቃላይ ማስረጃቸው ከተሟላ በኋላ ለስራ ስምሪቱ የተመረጡ ሰዎች ስም ነው። ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ የሚጠይቁት በአካል ቢሮ ሄደው ነው። የኦንላይን ስራው ገና ጅማሬ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለፓስፖርት የሚመዘገቡት አዲስ አበባ ሄደው ነው?
አቶ አራርሶ፡- አዎ!
አዲስ ዘመን፡- ፓስፖርት ለማግኘት በኦንላይ ምዝገባ ተደርጎ፤ ቀነ ቀጠሮ ይሰጣል። አንድ ሰው በዚያ መሰረት ነው የሚሄደው፤ ይህ ነገር ተደራሽ አልሆነም?
አቶ አራርሶ፡– የስራ ስምሪትን በተመለከተ የኦንላይ ምዝገባው አሁን ጅማሮ ላይ ነው። ከዚህ በፊት ኤጀንሲዎች እስከ ዞን ነው ያሉት። አሁን ኤጀንሲዎቹ ተመልሰው ሁሉም ነገር አዲስ አበባ ብቻ ሆነ። ለስራ የሚሄዱት ሁሉንም ማስረጃ አሟልተው ካጠናቀቁ በኋላ በኦንላይን የሚለቀቀው። ይህን ያህል ሰው ከኦሮሚያ ክልል፣ ከዚህ ዞን እና ከተማ የሚል ዝርዝር በኦንላይን ይለቀቃል።
አዲስ ዘመን፡- ለምንድን ነው ኤጀንሲዎቹ ከዞን ተነስተው አዲስ አበባ ብቻ እንዲሆኑ የተደረገው?
አቶ አራርሶ፡- ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ብቻ ነው የሚያውቀው፤ እኛ ከዚህ በፊት ዞን የነበሩት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን እንጂ፤ በምን ምክንያት እንደሆነ አላወቅንም።
በ2014 ዓ.ም ችግር ባለበት አካባቢ ኤጀንሲዎቹ መሆን እንዳለባቸው በመነጋገር፤ እንደዛ እንዲሆን ተደርጎ ነበር። በዛ መሰረት ከፌደራል ፈቃድ አግኝተው ወደ እኛ ይመጣሉ፤ እኛ ደግሞ ወደ ዞን እንመድባቸዋለን። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ቢሾፍቱ፤ አዳማ፤ ነቀምት እና ሻሸመኔ ላይ ነበር።
አሁን ሁሉም ነገር ኦንላይን ስላደረጉት አዲስ አበባ እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ነገር ለስራ ጥሩ ነው፤ ግን ችግር ያለበት ቦታ ኢጀንሲዎቹ ካሉ አዲስ አበባ ሳይሄዱ እዛው ችግሩ ይፈታል። እንደ ቢሮ እንደዛ ነው የምናስበው። ሀሳባችን እንደዛ መሆኑን ለስራና ክህሎት ሚኒስቴር አሳውቀን እየተወያዩበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምን ምላሽ ተሰጠ?
አቶ አራርሶ፡- ገና እየጠበቅን ነው። ኤጀንሲዎቹ እስከ ዞን ወይም ወረዳ ድረስ መምጣት አለባቸው እንጂ ወጣቶቹ አዲስ አበባ እንዲመላለሱ ማድረግ እና አንድ ቀን አዲስ አበባ ከተማ ማደር በጣም ከባድ ነው። እስከ ወረዳ ካልተቻለ እስከ ዞን ድረስ እንኳን ቢሆን ለወጣቶቻችን መፍትሄ ይሰጣል ብለን እናምናለን።
ዞን ላይ ቢሮ ከከፈትን በኋላ እንደገና ዘግተን ወደ አዲስ አበባ ተመልሰናል። ይሄ ነገር እንዴት ነው እያሉ እየጠየቁ ነው የሚል ጥያቄ ከኤጀንሲዎቹ በኩል እየተነሳ ነው። ይሄ ነገር መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር እየተወያየን ነው። መፍትሄ ይገኛል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ለስራ የሚሄዱ ዜጎች መጀመሪያ አዲስ አበባ የሚሄዱት በእናንተ በኩል ተመዝግበው ነው?
አቶ አራርሶ፡- እኛ ከኤጀንሲዎች ጋር ተነጋግረን ለወጣቶች የሚያስፈልገው ስልጠና በኮሌጆች ይሰጣል። ከዛ በኋላ ኤጀንሲዎቹ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ከኢሚግሬሽን ጋር ተነጋግረው ወጣቶቹ እንዲሄዱ ይደረጋል። አስተባባሪ ስላለን የሚሄዱትን መረጃ በዛ በኩል እናገኛለን። ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር እንደዛ ነበር። አሁን በኦንላይን ስለተደረገ እኛ ሳናውቅ ነው የሚሄዱት።
አዲስ ዘመን፡- ፓስፖርት የሚያወጡት ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ ነው?
አቶ አራርሶ፡- በፊት የነበረው ዞን ላይ በኤጀንሲዎች በኩል ምዝገባ ጨርሰው፤ ፓስፖርት ይጨርሳሉ። ከጨረሱ በኋላ በኮሌጅ ደረጃ አስፈላጊው ማብራሪያ ተሰጥቷቸው ይሄዳሉ። ፓስፖርቱን ከዛ በኋላ ነው የሚያገኙት። አሁን የተለወጠው እሱ ነው።
አዲስ ዘመን ፡- በ2016 በጀት ዓመት ለምን ያህል ወጣቶች የስራ እድል ተፈጠረ?
አቶ አራርሶ፡– በኢንዱስትሪ ላይ በሸገር ከተማ አራት ሺ 65 የስራ እድል ተፈጥሯል፤ አንድ ሺ 65 የተፈጠረው ደግሞ ቢሾፍቱ ከተማ ላይ ነው። ጠቅላላ በኢንዱስትሪ አካባቢ አምስት ሺ አካባቢ የስራ እድል ተፈጥሯል። በግብርና ዘርፍ በከብት እርባታ፣ በዶሮ እርባታ፣ በሩዝ ምርት፣ በሻይ ቅጠል ስራ እና በሌሎች የግብርና ስራ አጠቃላይ እንደ ኦሮሚያ ክልል 350 ሺ የሚሆን የስራ እድል ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፡- ከአረጋውያን ጋር ተያይዞ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አራርሶ፡– ከአረጋውያን አያያዝ ጋር ተያይዞ ብዙ ስራ ሰርተናል። በቢሾፍቱ ከተማ ከ200 በላይ አረጋውያን በቀን ምሳ እንዲያገኙ ተደርጓል። ሌላው በቢሾፍቱ አረጋውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ማእከል ከዚህ በፊት የተሰራ ነበር አሁን ደግሞ ተጨማሪ ተሰርቷል።
አዲስ ዘመን፡- ማእከሉ ምን አይነት ጥቅም የሚሰጥ ነው?
አቶ አራርሶ፡- ማእከሉ አረጋውያን ያላቸውን የሕይወት ልምድ ለወጣቶች እንዲያካፍሉ እና ለራሳቸውም ገቢ እንዲያገኙ እንደ “ካፍቴሪያ” አይነት ነገር ነው። ተሰርቶ ተጠናቋል፤ ግን ወደ ስራ አልገባም። ወደፊት እሱን ማስፋፋት አለብን ብለን እንደ ክልል እቅድ ይዘናል።
በዚህ ሁኔታ ገቢ ያገኛሉ፤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያን ማህበሩ ተጠቃሚ ያደርጋል። እራሳቸውን ችለው እንደማህበር ይንቀሳቀሳሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ማእከሉን በሌሎች ክልሎች የማስፋፋት እንቅስቃሴው ምን ይመስላል?
አቶ አራርሶ፡– ሸገር ከተማ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ እየተሰራ ነው። የግንባታው ሂደት 75 ከመቶ ደርሷል። ለሌላው አርሲ፣ ሰሜን ሸዋ እና ቦቆጂ ከተማ ላይ መሬት አግኝተን እየሰራን ነው የሚገኘው። ማእከሉን ለማስፋፋት በዘንድሮ ዓመት እቅድ ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡- ማእከሉ ምን ምን ያሟላ ነው? ስራውን ለመስራትስ ያነሳሳችሁ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ አራርሶ፡– ቤተ መጻህፍት አለው፤ ለተለያዩ ዝግጅቶች አከራይተው እንዲጠቀሙ አዳራሽም ያለው ሲሆን፣ አልፎ አልፎ ሌሎች ገቢ ማግኛ ስራዎችም ይሰራሉ ማለት ነው።
ይህን ለማድረግ ያነሳሳን ሁልጊዜ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ከመለመን በእንደዚህ አይነት መልኩ መስራት አለብን በሚል ነው፤ የጀመርነው ኮሚቴ አቋቁመን ነው። የተጀመረው በ2013 ዓ.ም ሲሆን፣ አሁንም የሚቀጥል ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመገንባት ረገድ ምን ተሰርቷል?
አቶ አራርሶ፡- አቅም የሌላቸው አረጋውያንን ቤት ማደስና መስራት በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት የተገነባው ከ68 ሺ በላይ ነው።
እንደ ኦሮሚያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ከ28 ሺ በላይ ቤት ተገንብቷል። ነገር ግን አጠቃላይ እንደክልል የተገነቡና የታደሱ ቤቶች ቁጥር ከ68 ሺ በላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የቤት ግንባታው የተገነባው ከየት በተገኘ ገንዘብ ነው? እነማን ናቸው የተሳተፉት?
አቶ አራርሶ፡– ግንባታው የተደረገው በሕብረተሰብ ተሳትፎ ነው። እንደ ቢሮ ከቀበሌ እስከ ክልል የተደራጀ አፎሻ ወይም እድር አለ። ከዚህ በፊት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ብቻ ነበር የእድር አደረጃጀቱ፤ አሁን እስከ ክልል ሊደርስ ችሏል። በዛ እድር ገንዘብ ይቆጥባሉ፤ ከዛ ደግሞ ለአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ያደርጋሉ።
አዲስ ዘመን፡- ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት ምን ምን ተግባራትን ለማከናወን እቅድ ይዟል?
አቶ አራርሶ፡- ሕገ ወጥ ዝውውርን ለመከላከል ባለፈው በጀት ዓመት ከክልል እስከ ወረዳ ነው ኮሚቴ ያቋቋምነው። ዘንድሮ በክልሉ ሕገወጥ ዝውውርን ለመቆጣጠር እስከ ቀበሌ ኮሚቴ ተዋቅሮ ይሰራል። ወጣቶች ሀገር ውስጥ ስራ እንዲያገኙ እና በሕጋዊ መንገድ እንዲሄዱ በቋሚነት ለመስራት አቅደናል።
ሌላው በኢንዱስትሪ ግንኙነት እና ከሰላም ጋር ተያይዞ ነው። እንደ ሀገር ዝቅተኛ የክፍያ ጣራ የለም። ምርታማነትን ለመጨመር አሰሪና ሰራተኛ ተስማምተው መስራት ይኖርባቸዋል። አሰሪው ሰራተኛውን እንደቤተሰብ ማየትና አስፈላጊውን የደህንነት እቃዎች ማሟላት አለበት። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከኢንዱስሪዎች ጋር በየጊዜው ውይይት እናደርጋለን። በተያዘው ዓመትም አጠናክረን እንቀጥላለን።
ባለፈው ዓመት በክልሉ 10 ኢንዱስትሪዎች ላይ ሰርተን ነበር። አሁን እሱን በማስፋፋት ወደ ተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ተደራሽ ለመሆን ነው። እሱን ወደ ሸገር እና አዳማ ከተማ አስፋፍተን በአሰሪ እና ሰራተኛ መሃል ያለውን ቅራኔ በውይይት መፍታት አለብን ብለን ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡- 10 ኢንዲስትሪዎች በምን ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው? በኢንዱስትሪዎቹ የተሰራው ስራ ምንድን ነው?
አቶ አራርሶ፡– የቆርቆሮ፣ የልብስ፣ የውሃ፣ የዱቄት፣ የዳቦን ጨምሮ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች የደመወዝ ጭማሪ በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚነሳ ጥያቄ አለ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከፌደራል ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ከመጠበቅ እኛ እራሳችን ተወያይተን መፍትሄ ማምጣት አለብን ብለን ይዘናል። ባለፈው ዓመት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ያለው ችግር ተፈትቷል።
አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ አራርሶ፡- የደመወዝ ጥያቄ ነው፤ በሀገራችን ዝቅተኛ የደመወዝ ጣራ አልተወሰነም። በዚህ ምክንያት በአንድ ቦታ የተነሳው ጥያቄ መልስ ሲያገኝ በሌላ ቦታ ጥያቄ ይነሳል።
ሌላው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ነው። አሁንም አልፎ አልፎ በምስራቅ በኩልና በሞያሌ በኩል ሰው ይወጣል። ይህን ነገር በአንዴ ማቆም አይቻልም። ችግሩን ለመፍታት ከሕግና ከጸጥታ አካላት ጋር እየሰራን ነው። በክልሉ ያሉ ወጣቶች ብዙ ስለሆኑ አንዱ ስራ ሲያገኝ፣ አንዱ በሕጋዊ መንገድ የመሄድ እድሉን ሲያገኝ፤ አንዳንዱ የማያገኝበት ሁኔታ ስላለ፤ አልፎ አልፎ ይህ ችግር ይከሰታል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ አራርሶ፡- ሕዝባችን ከተረጅነት መላቀቅ አለበት ብለን ማህበራዊ ጉዳይም ስለሚመለከተን እየሰራን ነው። ዜጋው ሁልጊዜ ሀገር ውስጥ ስራ ማግኘት ይቻላል ብሎ ማመን አለበት። ሰው በራሱ የሚተማመን ከሆነ ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መጥተው ያቀዱትን ማሳካት ይቻላል።
ስለዚህ ወጣቶች በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ወደ ውጭ ሀገራት ለመሄድ ከፈለጉም በሕጋዊ መንገድ መሄድ እንዳለባቸው መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመስግናለን፡፡
አቶ አራርሶ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም